
16/05/2025
በRCFS ፕሮጀክት የሚሰሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች የማህበረሰቡን የዘመናት የመሰረተ ልማት ጥያቄ የሚፈታ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የማኔጅመንትና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በፕሮጀክቱ የሚሰሩ የመንገድ ዲዛይኖች በአማካሪ መሀንዲሶች ቀርበው ግምገማ ተደርጎበታል።
ፕሮጀክቱ ለሚያሰራቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች በአማካሪ መሀንዲሶች የቀረቡ የዲዛይን ስራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ቤሌማ አማካሪ ፣ ኤች ቲ ስኩዌር እና ጦና አማካሪ በተባሉ ድርጅቶች የዲዛይን ስራው እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በዳውሮ ዞን የባሌ - ሹታ 11.96 ኪሎ ሜትር ፣ በኮንታ ዞን የደልባ - አልፋ የ12.1 ኪሎ ሜትር ፣ በካፋ ዞን የካካ - ሜጫ 26 ኪሎ ሜትር ፣ በቤንች ሸኮ ዞን የኩካ - ማሀ 9.7 ኪሎ ሜትር ፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን የባቹማ - ኮላይ 10 ኪሎ ሜትር የመንገድ ስራዎች፣ ሸካ ዞን የኪ ወረዳ ኩብቶ - ባሆመንደራሻ 8.6 ኪ.ሜ መንገድ እና ስትራክቼር
የዲዛይንና የስትራክቸር ስራዎች ቀርበው ተገምግመዋል።
አማካሪ መሀንዲሶቹ በመጀመሪያው የግምገማ መድረክ አስተያየቶችን እንደ ግብዓት በመጠቀም የዲዛይና የስትራክቸር ስራዎችን አዘጋጅቸው መቅረባቸውን ገልጸዋል።
የቢሮው መሀንዲሶችና ባለድርሻ አካላት በሰጡት የግምገማ አስተያየት በመጀመሪያው ዙር የተሰጡ አስተያየቶች በአብዛኛው ተካተውና ተሻሽለው መቅረባቸውን ገልጸዋል። የካካ - ሜጫ መንገድ የቆረጣ ስራዎች ፣ የመረጃ ለቀማ ጥራት ፣ የድንጋይና ጠጠር ማምረቻ ቦታ መረጣዎች እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት የመንገድ ስራዎቹ የህብረተሰቡን የመንገድ ተደራሽነት የሚያሰፋ ፣ ጊዜ ፣ ወጪና ድካምን የሚቀንሱ ይሆናሉ ብለዋል።
የመንገድ ስራዎች ከተደራሽነታቸው ባሻገር ኢኮኖሚካል አዋጭነታቸው ሊረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ ፋጂዮ የዲዛይን ስራዎችም እነዚህ ጉዳዮች ያካተቸ ሊሆን ይገባል ብለዋል። አማካሪ መሀንዲሶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስራዎችን አጠናቀው ለማቅረብ የወሰዱት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የተነሱ ጥቃቅን አስተያየቶችን በማረም ወደ ጨረታ ሂደት እንደሚገባም ኃላፊው ገልጸዋል።