
11/06/2025
“የቡና ግብይት ችግሮችን በመለየት ለመፍትሔዎቹ መስራት ይገባል” - አቶ አስራት መኩሪያ
የቡናን የግብይት ሰንሰለት ችግሮች በጥናት በመለየት መፍትሔዎችን ለማምጣት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን አስገነዘበ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ
በዘርፉ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ያመላከታቸውን ችግሮች በመቅረፍ ቡና ለክልሉና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በጥናቱ መሠረት የቡና ግብይት ችግሮችን በመለየት ለመፍትሔዎቹ መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለሥልጣን በኤፍ ኤስአርፒ (FSRP) ፕሮጀክት የበጀት ድጋፍ በቡና እሴት ሰንሰለት ዙሪያ በተደረገ ጥናት ውጤት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል።
የዳሰሳ ጥናቱን የክልሉ ኤፍኤስአርፒ (FSRP) ባለሙያ ዶክተር ሀብታሙ ገብረሥላሴ አቅርበዋል።
በክልሉ በስድስት ከፍተኛ ቡና አምራች ወረዳዎች፣ አርሶ-አደሮች፣ አዘጋጆችና አቅራቢዎች የተካተቱበት ጥናት ምንም እንኳን ከ560 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ልማት ሽፋን ቢኖርም ምርታማነቱ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
በክልሉ የቡና ምርታማነት በአማካይ 6.8 ኩንታል በሄክታር ብቻ ስለመሆኑ አብራርተው ፤ ብዙ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።
ክልሉ በዓመት 54 ሺህ 795 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን ቡና ምርት ገበያ 18 በመቶ እየሸፈነ ሲሆን ፤ ይህም ካለው እምቅ አቅም አንፃር ብዙ የሚቀረው ነው ተብሏል።
በጥናቱ እንደተገለፀው ፤ ከአምራች አርሶ-አደሮች መካከል 54 በመቶዎቹ ብቻ ለህጋዊ አቅራቢ ነጋዴ ምርቱን ይሸጣሉ።
በመሆኑም በህገ-ወጦችና በደላሎች ዋጋ ተወስኖ የሚወጣውን ቡና መግታት የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት መስራትና መፍትሔ መቀየስ እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል።
እንደ ክልል 445 የቡና ኢንዱስትሪዎችና 245 ቡና አልሚ ባለሀብቶች መኖራቸውም ተብራርቷል።
በምክክሩም የቡና አልሚ ባለሀብቶች፣ አቅራቢዎች፣ ባለሙያዎችና የዘርፉ አመራሮች ተስትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ፍቅሩ በላይ
ፎቶ፡ በረከት ገብረኪዳን