
25/09/2025
አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ በመመረቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች በቀጣናው ብሎም በዓለም አቀፍ የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
አንቶኒዮ ጉተሬዝ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ በመመረቁ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
በተጨማሪም በቅርቡ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጉባዔን በስኬት ማስተናገዷን አስታውሰው፥ ለዚህም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ ፕሬዚዳንት ታዬ ከ80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን አፍሪካን በኤሌክትሪክ ለማዳረስ ዓላማ ያደረገው“ተልዕኮ 300" ኢነርጂ ኢኒሼቲቭ ላይ ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ ተልዕኮውን መቀላቀሏ እያካሄደችው ያለውን የኢነርጂ ማሻሻያ የሚያጠናክር ዕውቅና በመሆኑ ትልቅ ምዕራፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ጥር ወር በታንዛኒያ በተዘጋጀው “ተልዕኮ 300” ኢነርጂ ኢኒሼቲቭ ስብሰባ ላይ ቡድኑ ውስጥ እንድትካተት ማመልከቷ ይታወሳል፡፡
አሁን ላይም ለአባልነት የሚያበቃትን ስትራቴጂና የትግበራ የጊዜ ሰሌዳዎችን በማዘጋጀት ቁርጠኝነቷን በድጋሚ ለማረጋገጥ የገባችውን ቃል በተግባር አረጋግጣ ኢኒሼቲቩን ተቀላቅላለች፡፡