15/04/2023
ካርቱም ውስጥ ምን እየሆነ ነው ?
በሱዳን በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና በተጽእኖ ፈጣሪ ነው በሚባለው " ፈጥኖ ደራሽ ሚሊሻ " መካከል በካርቱም ውጊያ ተቀስቅሶ ከተማው በቶክስ እየተናወጠ ነው።
ዛሬ በመዲናዋ ከፍተኛ የተኩስ እና ፍንዳታ ተሰምቷል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የካርቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ተቆጣጥሪያለሁ ያለ ሲሆን፤ የብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያን ለመቆጣጠር የተኩስ ልውውጥ እየደረገ መሆኑን ከሰዓታት በፊት አሳውቋል።
ፍጥጫው እንዴት ጀመረ ?
በሁለቱ ኃይሎች መካከል ለተፈጠረው ፍጥጫ ምክንያት በወታደራዊ አስተዳደር ስር የቆየችውን ሱዳን ወደ ሲቪል መንግሥት ለማሻገር በቀረበው ሃሳብ የተነሳ ነው።
ሄምቲ በሚለው ቅጽል ስማቸው በሚታወቁት በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ወደ አገሪቱ ጦር ስለሚቀላቀልበት ሁኔታ አንዲሁም ኃይሉን ማን ይመረዋል በሚለው አለመግባባት ተፈጥሮ ባለፉት ቀናት ውጥረት ሰፍኖ ነበር።
ሁለቱ አካላት ምን አሉ ?
ዛሬ የተኩስ ድምጽ መሰማት የጀመረው በማዕከላዊ ካርቱም ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ነበር።
(አርኤስኤፍ) የሚባለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ምን አለ ?
በዋና ከተማዋ በስተደቡብ ከሚገኙት ካምፖቹ መካከል አንዱ ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረበት ገልጿል።
የሱዳን ጦር ሠራዊት ምን አለ ?
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች የጦር ኃይሉን ዋና መ/ቤት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተዋጊዎች በካርቱም እና በሌሎች የሱዳን ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ የጦር ሠራዊት ካምፖች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ብላል።
ግጭቶች እየተካሄዱ መሆኑ የገለፀው ጦሩ ፤ ሠራዊቱ አገሪቱን የመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብሏል።
ሱዳን ...
ከሁለት ዓመት በፊት በሱዳን ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ የጦር ጄኔራሎች ሉዓላዊ ምክር ቤት የሚባል አካል አቋቁመው አገሪቱን እየመሩ ይገኛሉ።
አርኤስኤፍ የተባለው ፈጥኖ ደራሽ ሚሊሻ በኃያሉ ጄኔራል እና የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራ ነው።
የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት የሆኑት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን ደግሞ የአገሪቱን ጦር ኃይል ይመራሉ።
ሱዳንን ወደ ሲቪል መንግሥት ለማሸጋገር የቀረበው ዕቅድ የአርኤስኤፍ ኃይሎችን ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጋር በማዋሃድ የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ከስምምነት ሳይደረስበት ቆይቷል።
አርኤስኤፍ ውህደቱ በአስር ዓመታት እንዲዘገይ ፍላጎት ያለው ሲሆን፣ የአገሪቱ ሠራዊት ግን በሁለት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ይፈልጋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ውጥረት በተካረረበት ጊዜ አርኤስኤፍ ኃይሎቹን ሐሙስ ዕለት ሜሮዌ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ኃይሎች አቅራቢያ አሰማርቷል።
ጄኔራል ቡርሃን በሚቋቋመው ሲቪል መንግሥት ውስጥ የሚመሠረተውን የተዋሃደ የአገሪቱን ጦር ማን መምራት አለበት በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ከጄኔራል ዳጋሎ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።
(ቢቢሲ)