24/09/2025
#የህግ ግምት ምንድነው ? በዚህ ረገድ የተሰጡ የሰበር ውሳኔዎች ምን ይላሉ?
========================================
#ሕግ አውጪው ለግምት መነሻ ከሚሆኑ የተወሰኑ ፍሬ ጉዳዮች በመነሳት አንድ ድርጊት ተፈፅሟል ወይም አልተፈፀመም ብሎ የሚደርስበትን መደምደሚያ በሕግ የሚደነግጋቸው ሁኔታዎች
የሕግ ግምቶች ዳኞች አንድን ፍሬ ጉዳይ የተፈፀመ ወይም ያልተፈፀመ መሆኑን በማስረጃ በማረጋገጥ ረገድ የሚገጥማቸውን ክፍተት በመሙላትና የማስረዳት ሸክም ያለበትን ወገን ጫናውን በማቃለል በኩል የላቀ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑ ይታመናል፡፡
#ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይም የሕግ (የህሊና) ግምት ዓይነተኛ ዓላማ የማስረዳት ሸክም ያለበትን ወገን ጫና የማቃለል፣ ውሳኔ ሠጪ አካልንም ተገቢና ግልፅ ሆኖ የሚታይ የጠራ ማስረጃ ካላገኘ ወደ ውሳኔ በአፋጣኝ እና በቀላሉ እንዲደርስ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሠጥ መሆኑ ይታመናል፡፡ የሕግ ግምት ለዳኞች የሕሊና ሚዛን እድል የማይሰጥ ዳኞች የነገሩን ሁኔታ በማየት ሲፈልጉ የሚጠቀሙበት፣ ከነገሩ ሁኔታ አንፃር አስፈላጊ ሆኖ ካላገኙት የሚተውት ፈቃጅ የሆነ የሕግ ግምት አይደለም፡፡ በአንጻሩ የህግ ግምት ድንጋጌ የሚሸፍነው ጉዳይ ባጋጠማቸው ጊዜ ዳኞች ያለምርጫ ሊከተሉትና ሊፈፅሙት የሚገባና አስገዳጅነት ያለው ነው፡፡
#ሰ/መ/ቁ. 29181 ቅጽ 10
#በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2024 የሰፈረው የሕግ ግምት ተፈፃሚ የሚሆነው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? እንዲሁም ተከሣሽ ቀርቦ የቀረበበትን ክስ ባልካደበት ሁኔታ ተፈፃሚ ይሆናል ወይስ አይሆንም? የሚለው ነጥብም ከዚሁ ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ የሕግ ግምት አፈፃፀም የስረነገር (Substantive) ሕግ እና የስነ ሥርዓት (Procedural) ህግ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን ከላይ የተነሱትን ነጥቦች በአግባቡ ለመመለስ የኢትዮጵያ ሕግ በሁለቱም ረገድ ያለውን ዝርዝር ድንጋጌ መመልከትና መረዳት ያስፈልጋል፡፡
#በኢትዮጵያ የስረነገር ሕጎች በርካታ የሕግ ግምቶች ያሉ ሲሆን በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2024 የሰፈረው ግምት ስለ ውሎች ማስረጃ በሚመለከተው ክፍል የሚገኝ ሲሆን በውል የሚጠየቅ ገንዘብ እንደተከፈለ ከሚያስቆጥሩ የሕሊና ግምቶች አንዱ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ እዳው እንዲከፈል ከሚገባበት ቀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ሳይከፈሉ የቀሩ በአንቀጹ ተዘርዝረው የተቀመጡትን እዳዎች እንደተከፈሉ ይቆጠራል፡፡
በዚህ ግምት ከሚሸፈኑ እዳዎች መካከል ለቤት ኪራይ የሚከፈል እዳ አንዱ ነው፡፡ (ቁ. 2024/መ) የሕግ ግምቶች መሠረታዊ ውጤት የማስረዳት ሸክምን ከአንዱ ወገን ወደሌላው እንዲሻገር ማድረግ ቢሆንም የማስረዳት ሸክሙ የዞረበት ወገን የሕግ ግምቱን ማፍረስ የሚችልበት የሕግ ሁኔታ ይለያያል፡፡ አንዳንድ የህግ ግምቶች የግምቱ ተጠቃሚ ያልሆነው ወገን ማንኛውንም ዓይነት ማስረጃ በማቅረብ የሚያፈርሳቸው ሲሆኑ (Rebutable Presumption) ሌሎች የሕግ ግምቶች ደግሞ ማንኛውም ዓይነት ማስረጃ በማቅረብ ማፍረስን የማይፈቅዱ (Irrefutable Presumption) ናቸው፡፡
#የፍትሐብሔር ሕጉ ከ2020 – 2024 ያሰፈራቸውን የህግ ግምቶች ለማፍረስ ማንኛውንም ዓይነት ማስረጃ ማቅረብ የማይቻል ስለመሆኑ ከሕጉ አንቀጽ 2026(1) ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይኸው ድንጋጌ ‘’ከዚህ በላይ ባሉት ቁጥሮች ላይ ለተገለጠው የሕሊና ግምት መቃወሚያ የሚሆን ማንኛውም ዓይነት ማስረጃ ለመቀበል አይቻልም‘’ በማለት በሕጉ የሰፈሩትን ግምቶች ለማፍረስ አንደኛው ወገን ማንኛውንም ዓይነት ማስረጃ ማቅረብ እንደማይፈቅዱለት በመርህ ደረጃ በግልጽ አስፍሯል፡፡
#ይህ አጠቃላይ መርህ ቢኖርም አንዱ ወገን ይህን አስገዳጅ የህግ ግምት ማፍረስ የሚችለው ሌላው ወገን መሀላ እንዲፈጽምለት በመጠየቅ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መልክ ሌላው ወገን መሃላ እንዲወርድለት በመጠየቅ የማስረዳት ሸክሙን ለመወጣት የሚሻ ወገን የፍትሐብሐር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 83 በሚያዘው መሠረት ይህን ማስረጃውን ክሱን በሚያቀርብበት ወቅት እንዲጠቅስ ይጠበቅበታል፡፡
#በውል ሕግ የሰፈሩት እነዚህ ድንጋጌዎች የስረ ነገር ሕግ ክፍሎች በመሆናቸው ፍርድ ቤቶች ሊከተሉዋቸው የሚገባ አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች የማስረጃን አቀራረብ የሚመለከቱ ከመሆናቸው በስተቀር እንደማንኛውም ሌላ የውል ሕግ ድንጋጌዎች በባለጉዳዮች ቢጠቀሱም ባይጠቀሱም ፍርድ ቤቱ አግባብነት ባለበት ሁኔታ ሁሉ ተፈፃሚ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ባለጉዳዮች ለጉዳያቸው አግባብነት ያለውን ፍሬነገርና የሚጠይቁትን ዳኝነት ከመግለጽ አልፈው በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ተፈፃሚ የሚሆነውን ወይም የማይሆነውን ድንጋጌ እንዲጠቅሱ አይጠበቅባቸውም፡፡ በመሆኑም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2024 የተጠቀሰውን የሕግ ድንጋጌ ተፈፃሚ ለማድረግ የሚያበቃ ፍሬ ነገር የቀረበለት መሆኑን የተረዳ ፍ/ቤት በዚሁ ድንጋጌ መሠረት የሚሸፈነውን ፍሬ ነገር እንደተረጋገጠ የመቁጠር ግዴታ አለበት፡፡
#የሕግ ግምቶችን አስመልክቶ በፍትሐብሔር ሕጉ የሰፈረው ይህ መሠረተ ሃሣብ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉም በተመሣሣይ መንገድ ተደንግጎ የምናገኘው ነው፡፡ በዚሁ ሕግ መሠረት ማንኛውም ተከሣሽ በመርህ ደረጃ ለፍርድ ቤቱ በሚያቀርበው መልስ ክስ የቀረበበትን ነገር በግልጽና በዝርዝር ማስተባበል ይጠበቅበታል፡፡ በክስ አቤቱታ ላይ የቀረበ ማንኛውም ነገር በግልጽ ካልተካደ እንደታመነ ሊቆጠር እንደሚችልም ይደነግጋል፡፡ ይህ አባባል አጠቃላይ የፍትሐብሔር መደበኛ ሙግት አካሄድን የሚመለከት ቢሆንም ተከሣሹ የሕግ ግምት ተጠቃሚ ሲሆን በግምቱ የሚሸፈነውን ፍሬ ነገር በሚመለከት ይህ ግዴታ እንደሚወርድለት የሕጉ አንቀጽ 89 በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ድንጋጌ ‘’አስቀድሞ በአንደኛው ወገን አቤቱታ ወይም ሙግት በግልጽ የተካደ ጉዳይ ካልሆነ በቀር አንዱ ወገን ተከራካሪ ህጋዊ በሆነ ግምት የሚደገፍበትን ነገር ወይም ሌላው ወገን ማስረጃ እንዲያቀርብ ተገቢ የሆነበትን ጉዳይ ሌላው ወገን በአቤቱታው ውስጥ መጥቀስ አይገባውም’’ በማለት የሕግ ግምት ተጠቃሚ የሆነ ተሟጋች በሚያቀርበው መልስ በህግ ግምት የተሸፈነውን ፍሬ ነገር በግልጽ የመካድ ግዴታ እንደሌለበት ያመለክታል፡፡
በመሆኑም አንድ ተከሣሽ በሕግ ግምት የተሸፈነውን ፍሬ ነገር በማስመልከት በመልሱ በግልጽና በዝርዝር መካድ አይጠበቅበትም፡፡ በመሆኑም በህግ ግምት የተሸፈነን ጉዳይ በማስመልከት ማንኛውም ፍርድ ቤት ቢሆን ተከሣሹ በግልጽ ስላልካደ እንዳመነ ይቆጠራል በማለት ፍርድ ሊሰጥ አይችልም፡፡
#ይህ መሰረተ ሃሣብ በፍትሐብሔር ሕጉ ካለው መሠረተ ሃሣብ ጋር ተመሳሳይ እና የሚጣጣም ነው፡፡ የሕግ ግምትን አስመልክቶ ያለው የሕግ ማእቀፍ ይህ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሣኔ ይህንኑ መሠረት ያደረገ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ተከሣሹ የሕግ ግምት ተጠቃሚ በሚሆንበት ወቅት የሚከተሉት ሂደትና የሚሰጡት ውሣኔም በሌሎች በመደበኛ የሙግት ሂደት ከሚተከሉዋቸው የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ደንቦች የተለዩ መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም የቀረበላቸው ፍሬ ነገር በህግ ግምት እስከተሸፈነ ድረስ ፍርድ ቤቶች ተከሣሽ ካደም አልካደ የሕግ ግምቱን ተፈፃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተከሣሹ በሌለበት ጉዳዩ እንዲቀጥል መደረጉም አስገዳጅ በሆኑት የሕግ አንቀጾች አፈጻጸም ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡ ተከሳሹ ፍርድ ቤት ቢቀርብም በግልጽ እንዲክድ የማይገደደውን ፍሬ ነገር ጉዳዩ እርሱ በሌለበት በመቀጠሉ እንዳመነ የሚቆጠርበት በቂ ሕግ ምክንያት የለም፡፡
#ሰ/መ/ቁ. 17068 ቅጽ 1
#የይርጋ ሕግ አንድ ፍርድ ቤት የቀረበለትን ጉዳይ ፍሬ ነገር መመርመር ሳያስፈልገው አንድን ክስ ውድቅ የሚያደርግበት ሥርዓት ሲሆን የሕግ ግምት ግን ጉዳዩ ፍርድ ቤት ቀርቦ በተከራካሪዎች መካከል የቀረበው ማስረጃ ሲመዘን ተፈጻሚ የሚሆን ደንብ ነው፡፡ በመሆኑም አልፎ አልፎ የውጤት መመሳሰል የሚያጋጥም ቢሆንም የሕግ ግምትን ተፈጻሚ ለማድረግ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ፍሬ ነገርና አግባብነት ያለውን ሕግ እንዲመረምር የግድ የሚል ሲሆን ይርጋ ግን ጊዜውን በመቁጠር ብቻ ክሱ በፍሬ ነገር ደረጃ እንዳይሰማ የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ ከ2020-2024 ባሉት ድንጋጌዎች የተለያዩ የህግ ግምቶች አስቀምጧል፡፡ እነዚህ የሕግ ግምቶችን እንደብዙዎቹ የህግ ግምቶች አንድ ክስ ለችሎት ቀርቦ በሚታይበት ወቅት የማስረዳት ሸክም ያለበት ማነው? በሕግ የሰፈረውን ግምት ማፍረስ የሚቻለው እንዴት ነው? ወ.ዘ.ተ. የሚሉትን ማስረጃን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች እንጂ አንድ ጉዳይ በጊዜ ማለፍ ምክንያት ክስ እንዳይቀርብበት የሚከለክሉ የይርጋ ደንቦች አይደሉም፡፡
#ሰ/መ/ቁ. 15992 ቅጽ 1