
03/09/2025
የኦቻ ዋና ዳይሬክተር በደብረብርሀን የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝተው በሀዘን አለቀሱ፡፡ የተመድ የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ወይንም ኦቻ የኦፐሬሽን ዳይሬክተር ኤደም ዎሶርኑ በደብረብርሀን ተገኝተው ተፈናቃዮችን መጎብኘታቸውን ገለፁ፡፡
ከ22 ሺ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙበት በዚህ የተፈናቃዮች መንደር ውስጥ ያለውን ችግር መመልከታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የተፈናቃዮቹ መኖሪያ ድንኳን በውሀ መጥለቅለቁንና መጨቅየቱን መታዘባቸውን የገለፁት ዳይሬክተሯ ‹‹ጭቃው ወደውስጥ ለመግባት እንኳ አስቸግሮኝ ነበር›› ብለዋል፡፡
እነዚህ በግጭትና በጦርነት የተነሳ የተፈናቀሉ ሰዎች ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለፉትን አራት አመታት መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ በአንድ መጋዘን ውስጥ 1900 ሰዎች እርስ በእርስ ተደራርበው እንደሚኖሩ ያስታወቁት ዳይሬክተሯ በሲሚንቶው ወለል ላይ ያለምንም ብርድ ልብስ ሲተኙ ማየታቸውንም አስረድተዋል፡፡ የተፈናቃዮቹ ኑሮ እንዳሳዘናቸውና እንዳስለቀሳቸውም አስታውቀዋል፡፡
የሚመለከታቸው አካላት በትብብር እነዚህን ሰዎች ከዚህ ስቃይ ማውጣትና ህይወታቸውን መቀየር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ዘሀበሻ በተደጋጋሚ የደብረ ብርሀን ተፈናቃዮችን ስቃይ ሲዘግብና መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
ዘ ሀበሻ