18/10/2025
የኮሌራ በሽታ መከላከያ መንገዶች:-
ሁልጊዜ ውሃን አፍልቶ እና አቀዝቅዞ መጠጣት ወይም በውሃ ማከሚያ ኬሚካል የታከመ ውሃ መጠቀም፤ ምግብን በሚገባ አብስሎ በትኩስነቱ መመገብ፤የምግብ እቃዎችን በንጹህ ወይም በኬሚካል በታከመ ውሃ ማጠብ እና መጠቀም ፣ መጸዳጃ ቤትን አዘጋጅቶ በአግባቡ መጠቀም፤ እጅን በሚከተሉት ወሳኝ ጊዜያት በንጹህ ውሃና በሳሙና ሳሙና ከሌለ በአመድ በሚገባ መታጠብ
• ከመጸዳጃ ቤት መልስ፣
• ምግብ ከማዘጋጀት በፊት
• ምግብ ከማቅረብ በፊት፣
• ምግብ ከመመገብ በፊት፣
• ሕጻናትን ካጸዳዱ በኃላ፣
• ሕጻናትን ጡት ከማጥባት በፊት ፣
• በበሽታው ለተያዙ ሰዎች እንክብካቤ ካደረጉ በኃላ፣
• በበሽታው የሞቱ ሰዎችን አስክሬን በድንገት ከነኩ፤
• ማንኛውንም ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻን ውሃንና አካባቢን እንዳይበክል በአግባቡ በተመደበለት ስፍራ ማስወገድ፣
• በኮሌራ በሽታ የታመመን ሰው ልብስ በፈላ ውሃ መቀቀል ወይም በበረኪናና በልብስ ማጽጃ ሳሙና ዘፍዝፎ ማጠብ፣
• በበሽታው የተያዘን ሰው በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም በመዉሰድ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ ማድረግ ናቸው።
የግልና የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ ዝንቦች እንዳይራቡ ያድርጉ፣ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ በተመደበለት ስፍራ ያስወግዱ፤ ሽንት ቤት በመገንባት በአግባቡ ይጠቀሙ እንዲሁም በንጽህና ይያዙ፣ በተቅማጥና ተውከት የተነካካ እቃን፣ ወለልና መሬትን ከማጽዳትዎ በፊት በረኪና በማፍሰስ ብክለትን ይከላከሉ።
የበሽታ ምልክት ሲታይ መከናወን ያለባቸው ተግባራት:-
- በሽታው የሰውነትን ፈሣሽና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን በብዛት ከሰውነት የሚያስወጣ ስለሆነ የሚከተሉትን እርምጃዎች በፍጥነት በመውሰድ እንዲተኩ ያድርጉ።
- በመጀመሪያ ቤት ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውም ንጽህናው የተጠበቀ ፈሣሽ የሚችሉትን ያህል ይጠጡ።
-ህይወት አድን ንጥረ ነገር ወይም ኦ.አር.ኤስ በቤት ውስጥ ካለ አንድ ፓኬት ተፈልቶ በቀዘቀዘ አንድ ሊትር ውሃ በመበጥበጥ ይጠጡ ፤ የተበጠበጠ ኦ.አር.ኤስን መጠቀም የሚቻለው በተበጠበጠ በ24 ሰዓት ውስጥ ነው።
- ኦ.አር.ኤስ በቤት ውስጥ ከሌለ 8 የሻይ ማንኪያ ስኳር እና ግማሽ የሻይ ማንኪያ ጨው በአንድ ሊትር ንጹህ ውሃ በመበጥበጥ ባስቀመጥዎ ቁጥር ይጠጡ።
#አብክመጤናቢሮ