Gebeyehu Dereus - ገበየሁ ድረስ

Gebeyehu Dereus -  ገበየሁ ድረስ የግል እይታየና ወቅታዊ የሆኑ ሀገራዊና አለማ ቀፋዊ መረጃዎች

15/07/2024
“ እንደዚህ ነው ክህነት ዘመንን መቀደስ   በደምና በአጥንት  ጽኑ ሀገር ማውረስ”[ዝክረ ታሪክ - አቡነ ጴጥሮስ] ስለ ፍቅሯ ሞተዋልና ምድሯ ጴጥሮስ ጴጥሮስ ትላለች፣ ስለ ክብሯ መስዋዕት ኾ...
29/07/2023

“ እንደዚህ ነው ክህነት ዘመንን መቀደስ
በደምና በአጥንት ጽኑ ሀገር ማውረስ”

[ዝክረ ታሪክ - አቡነ ጴጥሮስ]

ስለ ፍቅሯ ሞተዋልና ምድሯ ጴጥሮስ ጴጥሮስ ትላለች፣ ስለ ክብሯ መስዋዕት ኾነዋልና ስማቸውን እየደጋገመች ትጠራለች፣ ጴጥሮስ ሰማዕት እያለች ታከብራለች፣ ቃል ኪዳናቸውን ትጠብቃለች፣ ለልጆቿ ታስተምራለች፣ በማይጠፋ ቀለም፣ በማያረጅ ብራና ቀርጻ አስቀምጣለች፣ ዓመታት አልፈው ዓመታት ሲከተሉ ትዘክራቸዋለች፡፡

ኢትዮጵያን አብዝተው ወደዷት፣ ታላቅነቷን በጠላቶቿ ፊት መሰከሩላት፣ ነጻነቷን በደማቸው አጸኑላት፣ በገዳዮቻቸው ፊት እውነቷን ተናገሩላት፣ በሞት ፊት ኾነው ትውልድ ሁሉ ይጠብቃት ዘንድ ቃል ኪዳን አኖሩላት፣ እርሷን የሚክደውን ካዱት፣ እርሷን የሚወደውን ወደዱት፣ በቀና ልባቸው፣ አምላክ በመረጠው ብጽዕናቸው መረቁት፡፡ ሃይማኖታቸውን በርትተው ጠበቋት፣ ትዕዛዛቷን አከበሩላት፣ አክብረውም አስከበሩላት፡፡

የሀገር ፍቅራቸው ሞትን አስንቋቸዋል፣ የጥይት አረርን አስረስቷቸዋል፡፡ በሀገራቸው እና በሃይማኖታቸው የመጣባቸውን ጠላት ፊት ለፊት ታገሉት፣ ባሩድ የሚተፋ ጠመንጃ ይዞ እያስፈራራቸው ናቁት፣ መሳደድም ቢኾን፣ መሰቃየትም ቢኾን፣ መጠማትም ቢኾን፣ መራብም ቢኾን፣ መታሰርና መገረፍም ቢኾን፣ ሞትም ቢኾን ሃይማኖታቸውን፣ ሀገራቸውን እና ነጻነታቸውን ከመጠበቅ እንደማያቆማቸው ነገሩት፡፡

ጠላቶቻቸው ገድለው ነጻነታቸውን፣ ሃይማኖታቸውን እና ሀገራቸውን አሳጣናቸው ሲሉ እርሳቸው ግን በሞታቸው አሸነፏቸው፣ በቃል ኪዳናቸው ድል መቷቸው፣ እረኛውን ገደልን በጎችን በተናቸው ሲሉ እርሳቸው ግን በሞታቸው በጎቻቸውን ሰበሰቧቸው፣ በቃል ኪዳናቸው አንድ አደረጓቸው፣ ከዳር እስከ ዳር አሰባሰቧቸው፣ በቃል ኪዳን፣ በግዝት አስረው ለሀገራቸው ነጻነት አስነሷቸው፡፡ በሞታቸው ገዳዮችን ድል መትተዋል፣ እስከ ሞት ድረስ በታመነው የሀገር ፍቅራቸው ነጻነትን አምጥተዋል፣ ሕዝብን አንድ አድርገዋል፡፡ አርበኞችን በእልህና በወኔ አስነስተዋል፡፡

“ ለአረበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው
አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው” የተባለውም ለዚያ ነው፡፡

አምላክ የመረጣቸው ብጹዕ ናቸው፡፡ ትውልድ ሁሉ የሚወዳቸው፣ የሚመካባቸው ሰማዕት ናቸው፡፡ መስቀል ኃይልነ፣ መስቀል ጽንዕነ፣ መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል መድኃኒትነ ነፍስነ እያሉ መስቀል ብቻ ጨብጠው ከጠላት ጋር የተዋጉ አርበኛም ናቸው፡፡ ረቂቁን የሚያነጥሩ፣ ምስጢር የሚያሜሰጥሩ ሊቅ ናቸው፡፡ ከበጎቻቸው በፊት የሚቀድሙ፣ ስለ ፍቅር ለመስዋዕት የቀረቡ ጀግና ታማኝ እረኛም ናቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፡፡

ዓድዋ ላይ እንደ ዱቄት የተበተነችው፣ በኃያል ክንድ የደቀቀችው፣ ከሮም ተጉዛ በኢትዮጵያ ተራራዎች ለኢትዮጵያ የሰገደችው፣ ፎክራ መጥታ አልቅሳ የተመለሰችው፣ ንቃ መጥታ የተዋረደችው፣ ክብር አዋርዳለሁ፣ ነጻነት እገፍፋለሁ፣ ሀገር አሳጣለሁ ስትል በብርቱ ጀግኖች የተዋረደችው ኢጣልያ ከአርባ ዓመታት በኋላ ለበቀል መጥታ ነበር፡፡ በአምባላጌ፣ በመቀሌና በዓድዋ ላይ ደማቸው የፈሰሰባትን፣ አጥንታቸው የተከሰከሰባትን ልጆቿ ደም ልትመልስላቸው፣ የጣለችውን ክብሯን ልታነሳው፣ ውርደቷን ልትክሰው ዳግም ከሮም ተነስታ ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡

በዚያ ዘመን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አባ ዳኛው ምኒልክ አልፈው፣ አባ ጠቅል ኃይለ ሥላሴ ነግሰዋል፡፡ አባ ጠቅል ኃይለ ሥላሴ ለዙፋን ያበቃቸውን አምላካቸውን እያመሰገኑ ከአባቶቻቸው የተረከቧትን ሀገር ነጻነቷን፣ ክብሯን እና ታሪኳን ጠብቀው ለማኖር ደፋ ቀና ላይ ናቸው፡፡ ኢጣልያ ግን በአባ ዳኛው ዘመን የደረሰባትን ሽንፈት በእርሳቸው ዘመን ልታካክስ ሀገራቸውን ወጋችባቸው፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም አልደረስንባችሁም፣ አትድረሱብን፣ ተውን አሏቸው፡፡ ኢጣልያ አሻፈረኝ አለች፡፡ ሀገራቸውንም ወረረች፡፡
ንጉሡ ያቀረቡት የሰላምና የፍቅር ጥሪ ሰሚ አጣ፡፡ በኃይል የመጣውን ወራሪ በኃይል ለመመለስ የሀገራቸውን ጀግኖች ሰበሰቡ፡፡ እሳቸውም ዘመቱ፡፡ እርሳቸው ወደ ማይጨው ሲዘምቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም አብረው ዘምተው ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው የሀገራቸውን ጀግኖች በጸሎት እያበረቱ፣ አምላካቸው ሀገራቸውን እንዲጠብቅላቸው እየተማጸኑ ነበር ወደ ማይጨው ያቀኑት፡፡ ጠላት አብያተክርስቲያናትን እያቃጠለ፣ ካህናትን እየገደለ፣ ምዕመናንን በመርዝ እያሰቃየ ነበርና እረኛው እኔም ለበጎቼና ለሀገሬ እዘምታለሁ ብለው ዘመቱ፡፡

ኢጣልያ ለአርባ ዓመታት የተዘጋጀችበት፣ መርዝና የዘመኑ መሣሪያዎችን የታጠቀችበት ጦርነት ነበርና እንደ ዓድዋው ዘመን ሁሉ በቶሎ ድል መምታት አልተቻለም፡፡ ጦርነቱ ጊዜ ይወስድ ነበር፡፡ ንጉሡ ወደ ዙፋናቸው መቀመጫ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖችም በዱር በገደሉ ከጠላት ጋር መፋለማቸውን ቀጠሉ፡፡ ጦርነቱ በዱር በገደሉ ቀጠለ፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም ሀገራቸውን ላለማስደፈር የሚዋደቁትን ጀግኖች ያበረታቷቸዋል፣ ያለ ድካም ይጸልዩላቸዋል፡፡

ጦርነት ቀጠለ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያና የኢጣልያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከማይጨው ከተመለሱ በኋላ ሚያዚያ 24 ቀን ደብረ ሊባኖስ ገቡ፡፡ ከዚያም ኾነው የሰላሌን አርበኞች በስብከት ያነቃቁ ጀመር፡፡ በዚህም ለኢጣልያ የገቡና በኢጣልያ አገዛዝ ያመኑ የኢትዮጵያ ቀሳውስት አቡነ ጴጥሮስ ለኢጣልያ እንዲገቡና በኢጣልያ ላይ የሚነዙትን አጉል ስብከት እንዲተዉ በደብዳቤም በቃልም ይመክሯቸው ጀመር፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ግን ማንኛውንም ልመና አልተቀበሉትም ብለዋል፡፡

የእሳቸው ሃሳብና ተግባር እውነት ነበር እንጂ አጉል አልነበረምና እንዲያስተዋቸው ለሚጠይቃቸው ሁሉ ጀሮ አልሰጡትም፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች በየቀኑ የዙፋን መቀመጫዋን አዲስ አበባን ለማስለቀቅ ይዋጋሉ፡፡ የኢጣልያ ሠራዊትም ይሸበራል፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ፓትሪክ ሮበርትስንን ጠቅሰው ሲጽፉ “ ኢትዮጵያውያኖች የሚያስገርምና ከባድ ውጊያም አደረጉ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተጠጉ ሲሄዱም ጥቅጥቅ ካለው ደን ውስጥ ሲገቡ የኢጣልያ ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት አደረሱባቸው፡፡ ሁለት ቀን ሙሉ በጀግንነት ተዋግተው ኢትዮጵያውያኖቹ ይዘውት የነበረውን ቦታ ትተው ሲመለሱ ጳጳሱ አቡነ ጴጥሮስ ተማረኩ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ከተማዋ ድረስ ከአርበኞቹ ጋር አብረው የመጡ ናቸው፡፡ የተያዙትም በጦርነቱ ውስጥ ነው” ብሏል በማለት ጽፈዋል፡፡

ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጽሐፍ ደግሞ “ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አርበኞች ከአዲስ አበባ ሲመለሱ እሳቸው ግን የአዲስ አበባ ከተማን ትተው ለመሄድ አልፈቀዱም፡፡ በመኾኑም ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርጋለሁ ካልኾነ ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ ብለው ከአርበኞች ተነጥለው በአዲስ አበባ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላ ከተማዋ ባሰማራቸው በርካታ ባንዳዎች መካከል ብፁዕነታቸው እንዳሰቡት ሊንቀሳቀሱ አልቻሉም፡፡ በዚሁ በከተማም ተሰውሬ መኖር አልፈልግም ወደገጠርም ፊቴን አልመልስም በማለት ለኢጣልያ እንደራሴ እጃቸውን ሰጡ፡፡ የኢጣልያ እንደራሴም ወዲያው ለግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸው ” ብለዋል፡፡ የኢጣልያ እንደራሴ የነበሩትም ኢትዮጵያዊ ሰው ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽሽቶች እጅ ከገቡ በኋላ ሞት ተፈረደባቸው፡፡ ብፁዕ ኾነው ሳለ እንደ በደለኛ ሞት ተፈረደባቸው፣ ሃይማኖት ጠባቂ፣ የሀገር ፍቅር አዋቂ ኾነው ሳለ ይገደሉ ተባሉ፡፡ ሀገሬን አትንኩ፣ ሃይማኖቴን አትዳፈሩ ባሉ እንደ ሀጥያተኛ ተቆጠሩ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የኮሪየር ዴላ ሤራ ጋዜጠኛ የነበረውን ፓጃሊን ጠቅሰው ሲጽፉ “ በጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ እንዲገደሉ ፈረደ፡፡ ይህ ሲሰማ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ሽብር ተፈጠረ፡፡ ጉዳዮም በጋዜጣ እንዳይወጣ ፋሽሽቶች ታላቅ ቁጥጥር አደረጉ” ብለዋል፡፡

ፍርዱ ተፈረደ፡፡ ጳጳሱ ከሞት ደጅ፣ ከገዳዮች ፊት ቆሙ፡፡ ከሳሾቻቸውና ፈራጆቻቸው ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጽሐፍ “ ካህናቱም ኾኑ የቤተክህነት ባለስልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣልያን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ኾኑ ? ሲል ጠየቃቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስም መለሱ፡፡ አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኀላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ” ማለታቸው ተጽፏል፡፡

አቡነ ጴጥሮስ ወደ መግደያው ሥፍራ ተወሰዱ፡፡ እጅግ የከበረውን፣ ትውልድን ከትውልድ ጋር የሚያስተሳስረውን፣ ዘመናትን አልፎ የሚሰማውን ቃል ከአንደበታቸው አወጡ፡፡ “ ከሚገደሉበት ሥፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ፡፡ በሕዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፡፡ ፋሽሽቶች ያገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው የኢጣልያ ፋሽሽት ነው፡፡ አረማዊ የኾነው የፋሽሽት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፡፡ በጎ ለመሥራት እውነተኛ ለመፍረድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሞታችሁ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪየ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን” አሉ፡፡

አቡነ ጴጥሮስን ገድለው ክብር ማግኘት የሚሹ ገዳዮች ለመግደል አኮበኮቡ፡፡ ከአቡነ ጴጥሮስ ሃያ እርምጃ ያክል ርቀው በርከክ አሉ፡፡ በአስተኳሹ ትዕዛዝም ተኮሱ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ጀርባቸው ላይ ተተኮሰባቸውና ከመሬት ላይ ወደቁ፡፡ አልሞቱም ነበርና በድጋሜ በሦስት ጥይት ራሳቸውን ተመትተው ተገደሉ፡፡ ታላቁ አባት በሰማዕትነት ያረፉባት ቀንም ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ነበረች፡፡ ታማኙ እረኛ በጽኑ እምነት አለፉ፡፡ የእርሳቸውን ሞት የሰሙ ሁሉ አባታችን እያሉ አለቀሱ፡፡ አርበኞችም የታላቁ አባት መስዋዕትነት ወኔ እየኾናቸው ለነጻነት ለመሞት ቆረጡ፡፡

“ እንደዚህ ነው ክህነት ዘመንን መቀደስ
በደምና በአጥንት ጽኑ ሀገር ማውረስ” በደምና በአጥንታቸው ጽኑ ሀገር አወረሱ፡፡ በጽኑ ታማኝነታቸው አርበኞችን አጸኑ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸው፣ ለሀገራቸው፣ ለሠንደቃቸው፣ ለነጻነታቸው፣ ለክብራቸው እንዲዋደቁ አደረጓቸው፡፡ በሞታቸው ጠላትን ድል መቱት፡፡ በታማኝነታቸው ዘመንን ቀደሱት፡፡ ዘመንን የቀደሱ፣ ጽኑ ሀገር ያወረሱ አባት ሆይ ክብር ይገባዎታል፡፡

መረጃው የአማራ ሚድያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ነው

ምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያና ሸበል በረንታ ወረዳ  በበጀት አመቱ ዜጎችን ከዐይነስውርነት በመታደግ  በክልል ደረጃ በተካሄደ ውድድር 1ኛ በመውጣታቸዉ የዋን...
27/07/2023

ምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያና ሸበል በረንታ ወረዳ በበጀት አመቱ ዜጎችን ከዐይነስውርነት በመታደግ በክልል ደረጃ በተካሄደ ውድድር 1ኛ በመውጣታቸዉ የዋንጫና የቁሳቁስ ተሸላሚ ሆኑ፡፡

ዞኑ አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ የሆነው በአንድ ዓመት ውስጥ 13ሽ 874 ሰዎችን ከዓይነ ስውርነት በመታደጉ በክልል ደረጃ በተካሄደ ውድድር 1ኛ በመውጣቱ ነው፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን ሽልማት የተበረከተለት ትራኮማን በመከላከልና መቆጣጠር ሥራው የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ለመገምገምና በቀጣይም በሽታውን ለማስወገድ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር በተካሄደበት የማጠቃለያ ስነ ስርዓት ላይ ነው፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው የትራኮማ በሽታን ከዞኑ ነጻ በማድረግ ዜጎችን ከዓይነ ስውርነት ለመታደግ ሌትና ቀን የሰሩ አካላትን አመስግነዋል፡፡ አቶ አብርሃም በመልእክታቸው ይህ ተግባር ተወዳድሮ አንደኛ ከመውጣት በላይ በዓይነ ስውርነት የሚሰቃዩ ዜጎችን ቀዶ ጥገና በማድረግ ከአይነ ስውርነት በመታደግ ብርሃን እንዲያገኙ ማድረግ የሚሰጠው የህሌና እርካታ ይበልጣል ብለዋል፡፡

በዚህ ስራ የተሳተፉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች አስተዳደሩ በእጅጉ ያመሰግናል ያሉት አቶ አብርሃም በቀጣይ ትራኮማን ለማስወገድ ለምንሰራው ስራ ሁሉም አካል ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለስራችን መሳካት በጤናው ዘርፍ ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች በተጨማሪ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ ነበር ያሉት የምስራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት በበጀት አመቱ በተደረገ ርብርብ 13ሽ 874 ሰዎችን ከዓይነ ስውርነት መታደግ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ስራ በርካቶች እንዲሳተፉበት አድርገናል ያሉት አቶ መልካሙ የታካሚ ልየታ በሚካሄድበት ወቅት ከፍተኛ እርብርብ ያደረጉ የምስራቅ ጎጃም ህዝብ፣የመንግስት ሰራተኛ፣ጤና ባለሞያዎች፣በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና አጋሮች ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው በቀጣይ በሽታው የዞኑ ህዝብ የጤና ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው ትግል የሚጠበቅብንን እንድንወጣ በማለት ጠንካራ ጥሪ አቅርበዋል።

✅ምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር 1ኛ በመውጣት
✔ ዋንጫና ሰርተፍኬት
✅ ምስራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ 1ኛ በመውጣት
✔ ዲስክቶፕ ኮምፒዩተር፣ ✔ ኤልሲዲ✔፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን
✅ ሸበል በረንታ ወረዳ 1ኛ በመውጣት
✔ ዲስክቶፕ ኮምፒዩተር፣
✔ ኤልሲዲ✔፣
✔ ፎቶ ኮፒ ማሽን፣
✔ ሰርተፍኬት ተሸላሚ ሲሆኑ ከዞኑ

✅ 3 ትምህርት ቤቶች እያንዳንዳቸው ሰርትፍኬትና 2000 ሊትር የሚይዝ ሮቶ እና 4 የዓይን ቆብ ቀዶ ህክምና ባለሞያዎች ከ16-12ሽ ብር ሽልማት ተበርክቷል፡፡

በግንደወይን ከተማ አስተዳደር  ጤና ጣቢያ አንዲት እናት 3 ሴት ልጆችን በሰላም ተገላገለች።******************************በምስራቅ ጎጃም ዞን በግንደወይን ከተማ አስተዳደር ...
26/07/2023

በግንደወይን ከተማ አስተዳደር ጤና ጣቢያ አንዲት እናት 3 ሴት ልጆችን በሰላም ተገላገለች።
******************************

በምስራቅ ጎጃም ዞን በግንደወይን ከተማ አስተዳደር አንዲት እናት 3 ሴት ልጆችን በሰላም መገላገሏ ተገለፀ።

ወይዘሮ እናቴነሽ ይፍሩ በግንደወይን ከተማ አስተዳደር የ02 ቀበሌ ነዋሪ ስትሆን በቀን 19/11/2015 ዓ/ም 3 ሴት ልጆችን በግንደወይን ጤና ጣቢያ በሰላም ተገላግላለች።

የጤና ጣቢያው አዋላጅ ባለሙያ አቶ ዘለቀ ቸኳል እንደገለፁት የተወለዱት ህፃኖች አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ እንዳሉ ገልፀው ለተወሰነ ስዓት ማሞቂያ ክላስ መግባት ስላለባቸው ወደ ሞጣ ሆስፒታል እንደሚላኩ ተናግረዋል
ያለው የጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ነው።

እንኳን ደስ አላችሁ እንበላቸውከ20 በላይ የመንገሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ነው።በዛሬው ዕለት በርካታ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ይገኛሉ።...
20/07/2023

እንኳን ደስ አላችሁ እንበላቸው

ከ20 በላይ የመንገሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ነው።

በዛሬው ዕለት በርካታ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ይገኛሉ።

ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ/ም ፦

- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ (ነቀምቴ ካምፓስ)
- ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ (በዋናው ግቢ)
- አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ (ዋናው ግቢ)
- ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ
- ጂንካ ዩኒቨርሲቲ
- ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
- ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ
- ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ
- ሰመራ ዩኒቨርሲቲ
- ዲላ ዩኒቨርሲቲ
- እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ
- ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ (በዋናው ግቢ)
- መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ
- ቀብሪ ድሃር ዩኒቨርሲቲ
- ወራቤ ዩኒቨርሲቲ
- ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ
- ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ
- መቱ ዩኒቨርሲቲ
- አምቦ ዩኒቨርሲቲ
- ወልድያ ዩኒቨርሲቲ
- ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ
- ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ
- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
- አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ይገኛሉ።

ተመራቂዎች እና መላው ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ !!

 ❤‼️ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ለፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ ለማሰባሰብ የተዘጋጀው ታላቅ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
02/07/2023

❤‼️

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ለፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ ለማሰባሰብ የተዘጋጀው ታላቅ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

“የቅዱሳን መኖሪያ፣ የዕውቀትና የጥበብ መፍለቂያ–ርእሰ አድባራት ወ ገዳማት ጣና  ቅዱስ ቂርቆስ”*********** ዓይኔ የተቀደሰውን ሥፍራ አየች፣ እግሬ በተቀደሰው ሥፍራ ተመላለሰች፣ አፍን...
02/07/2023

“የቅዱሳን መኖሪያ፣ የዕውቀትና የጥበብ መፍለቂያ–ርእሰ አድባራት ወ ገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ”
***********
ዓይኔ የተቀደሰውን ሥፍራ አየች፣ እግሬ በተቀደሰው ሥፍራ ተመላለሰች፣ አፍንጫዬ እፁብ የሚያሰኘውን ማዕዛ አሸተተች፣ ጀሮዬ የከበረውን ታሪክ ሰማች፣ እጄ ቅዱሱን ሥፍራ ዳበሰች፣ ልቤ ሀሴትን አደረገች፣ አብዝታም ተደሰተች፡፡

ቅዱሳን የኖሩበት፣ የሚኖሩበት፣ ጻድቃን የሚመላለሱበት፣ ደጋጎች የሚጠለሉበት፣ በማዕልትና በሌሊት ያለማቋረጥ ምልጅና ጸሎት የሚደረስበት፣ ስብሐተ እግዚአብሔር የማይታጎልበት፣ ምስጢራት የሚነገሩበት፣ ጥበብ የሚመነጭበት፣ ታሪክ የመላበት ታላቅ ሥፍራ፡፡ ዓለምን የናቋት፣ አንይሽም ያሏት አበው ስጋቸውን አድክመው፣ መንፈሳቸውን አጠንክረው፣ በበዓት ተወስነው በዚያ ሥፍራ ይኖሩበታል፡፡
ውኃ በውኃ ላይ ባለፈበት፣ አድባራትና ገዳማት በመሉበት፣ ስውር ቤተ መቅደስ ባለበት፣ ደናግላን በሚኖሩበት፣ ቅዱሳን በሚከትሙበት፣ ባሕታውያን በሚመላለሱበት፣ ስውራን በዓታቸውን ዘግተው በሚጸልዩበት፣ ለምድር በረከትና ረድኤት በሚለምኑበት፣ የሰውና የመላእክት ኅብረት በማይለይበት፣ ቅዱስ መንፈስ በሚረብበት በምስጢራዊ ሐይቅ አንደበት ችሎ የማይናገራቸው፣ ጀሮ ችሎ የማይሰማቸው፣ ልብ ሆኖለት የማይመረምራቸው ከተዋቡበት የተዋቡ፣ ከተመረጡት የተመረጡ እጹብ የሚያሰኙ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሥፍራዎች መልተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ በሚነገርበት፣ ስርዓተ ክህነት እና ስርዓተ መንግሥት በጸናበት ሥፍራ ተገኝቻለሁ፡፡ ይህ ሥፍራ የቅዱሳን መኖሪያ፣ የበረከት ማደሪያ፣ የእውቀትና የጥበብ መፍለቂያ ነው፡፡ ትናንት ጥበብ ተቀድቶበታል፣ ዛሬም ይቀዳበታል፣ ነገም ይቀዳበታል፣ ጥበብን የሚሹ ሁሉ ይጠጡበታል፣ በጥበብም ይረኩበታል፡፡ ታላቁ ሥፍራ ርዕሰ አድባራት ወ ገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ፡፡ በዚህ ስፍራ ተመርምሮ ያልተደረሰባቸው፣ ታሪክ ነግሮ ያልጨረሳቸው፣ ሕዝብ ሁሉ የሚደነቅባቸው እና ይሰማቸው ዘንድ የሚጓጓላቸው ምስጢራት መልተዋል፡፡

እድል ቀንቶኝ፣ በተቀደሰው ሥፍራ ተገኝቼ፣ ከሊቁ እግር ሥር ተቀምጬ የከበረውን ታሪክ ሰምቻለሁ፡፡ በገዳሙ የአራቱ ጉባኤያት መምህር ርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን እጅግ የበዛውን፣ እንደ ሐይቁ የሰፋውን ታሪክ ነግረውኛል፡፡ ዳሩ ያን ሁሉ ታሪክ እጽፈው ዘንድ ብዕሬ አቅም የላትም፣ ልቡናዬም ያን ሁሉ አትችልም፡፡ እንደ ሐይቅ ከሰፋው ታሪክ ጥቂቱን ጻፍኩ እንጂ፡፡
ታሪኩ ከብሉይ ዘመን ጀምሮ ይመዘዛል፡፡ ቀደምት ታሪክ ያላቸው ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት ርዕሰ አድባራት ወ ገዳማት የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የብሉይ ኪዳን መሠረት ያለው፣ ቀደምት ታሪክ የመላበት ነውና ርዕሰ አድባራት ወገዳማት የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሲተረጉሙበት፣ ትምህርት ሲሰጥበት፣ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲፈጽምበት፣ የኦሪት መስዋዕት ሲሰዋበት፣ ስርዓተ ኦሪት ሲቀርብት የኖረ ታላቅ ገዳም ነው ጣና ቅዱስ ቂርቆስ፡፡

ይህ ስፍራ አስቀድሞ ደብረ ሳሂል ሳፍ ጽዮን ይባል ነበር፡፡ ደብረ ሳሂል ማለት የይቅርታ የጽዮን ተራራ ማለት ነው፡፡ ይህም የተባለው የደኅንነት መስዋኢት እየቀረበ ይቅርታ ይሰጥበት ስለነበር ነው፡፡ ዛሬም ድረስ መሰዋዊው አለ፡፡ ዘመናት አለፉ፡፡ ሌላ ዘመንም መጣ፡፡ በዚያ አካባቢ ቸነፈር በዛ፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ አንድ የበቁ ባሕታዊም ታቦተ ቂርቆስን ብታመጡ ቸነፈሩ ይርቃል፣ መቅሰፍቱም ይቆምላችኋል አሉ፡፡ የተባለውንም አደረጉ፡፡ የቅዱስ ቂርቆስ ታቦትም መጣ፡፡ ይህም ታቦት በቅዱስ አትናቲዮስ እጅ የተባረከ ነው፡፡ ረሃቡና ቸነፈሩ ጠፋ፡፡ ያንም ቃል ኪዳን በዚያች ምድር ጸንቶ ይኖራል፡፡ ስሙም ቂርቆስ እየተባለ ይጠራ ጀመር፡፡
ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ሲናገሩ ቤተ ክርስቲያን ትንቢት፣ ኦሪት፣ ታቦት፣ ሐዲስ፣ መስቀል፣ ታሪክ፣ ዘመነ አበው፣ ዘመነ ወንጌል፣ ዘመነ ሊቃውንት፣ ዘመነ መነኮሳት፣ ዘመነ ሰማዕታት ያላት እርሷ እንደ አሮን ልብስ ናት ይሏታል፡፡ ቤተክርስቲያን እውነተኛይቱ ሮማን ናት፡፡ ኢትዮጵያም የአሮንን ልብስ ትመስላለች፣ የሮማንም ወርቅም ያላት፡፡ ሁሉ ያላት ናት፣ ኢትዮጵያ ትክክለኛይቱ ሮማን ናት ይሏታል፡፡

ጣና ቅዱስ ቂርቆስም እንደ ሮማን ብዙ ጸጋ አለው፡፡ ጣዖታት የሚወድቁላት፣ ሕዝብ የሚሰግድላት፣ ትዕዛዝ የጸናባት፣ አምላክ የሰጣት ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ያረፈችበት ነውና፡፡ በአሥራ ሁለት ሺህ ሌዋዊያን በሊቀ ካህናቱ አዛሪያስ መሪነት የመጣችው ታቦተ ጽዮን የተቀመጠችበት፡፡ እግዜአብሔር በእጆቹ ትዕዛዘቱን የጻፈባት፣ በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጣት፣ ሙሴ አርባ ቀን ጾሞ የተቀበላት፣ በወርቅ የተለበጠችው፣ ለምድርም የተሰጠችው፣ ኪሩቤል የሚጋርዷት፣ የስርዬት መክደኛ ያላት ጽላተ ሙሴ በዚያ ሥፍራ አርፋች፡፡
አሮን የቀደሰባት፣ አሮን ያጠነባት፣ ሳሜኤል ያመሰገነባት፣ ዳዊት የዘመረባት፣ ነብያት ታምራትን ያደረጉባት፣ ሕዝብ ሁሉ የሰገደላት፣ የሚሰግድላት፣ ጣዖታት በፍርሃት የሚወድቁላትና ከምድረ ገጽ የሚጠፉላት፣ ጎሊያድን የቀጠቀጠችው፣ ዮርዳኖስን የከፈለችው፣ በሕብስትና በጎሞር የታጀበችው እውነተኛይቱ ታቦት ታቦተ ጽዮን በዚያ ሥፍራ አርፋለች፡፡

ሊቀ ካህናቱ የሚቀድሱባት፣ ምስጋናና ውዳሴ የሚያቀርቡባት፣ እግዚአብሔር ተገልጦ ለእስራኤል በረከት የሚሰጥባት፣ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ተቀምጣ የነበረችው፣ ለሰሎሞን ኃይልና ብርታት የሆነችው፣ ጥበብና ሞገስን የቸረችው፣ የመወደድና የመከበር ግርማ የሰጠችው፣ ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ታቦተ ጽዮን በርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቂርቆስ ገዳም አርፋለች፡፡

ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ያለቀሱላት፣ የግብጽ ጣዖታት የወዳደቁላት፣ ሕዝብ ሁሉ የሚሰግድላት፣ ሰሎሞን ከእርሱ በራቀች ጊዜ ያለቀሰላት፣ የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ያነቡላት፣ ቀዳማዊ ምኒልክ ከእርሱ ጋር መሆኗን ባወቀ ጊዜ አብዝቶ የተደሰተባት ታቦተ ጽዮን በዚህ ቅዱስ ሥፍራ አርፋለች፡፡
ጣና ቂርቆስ፣ መርጦለ ማርያም፣ ተድባበ ማርያም እና አክሱም ጽዮን ማርያም አያሌ ታሪክ የሚቀዳባቸው፣ የጸና ሃይማኖት ያለባቸው፣ የኢትዮጵያ አንድነት የሚመነጭባቸው ናቸውም ይሏቸዋል አባ፡፡ እነዚህ ጥንታዊን አብያተክርስቲያናት የከበረ ታሪክ የመላባቸው ርዕሰ አድባራት ወገዳማት የሚል ስያሜ ያላቸው ጥንታውያን ናቸው፡፡ በቀደመው ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሲነግሥ የአራቱ ገዳማት ወ አድባራት መሪዎች ተገኝተው ካልጸለዩ በስተቀር አይነግስም ነበር፡፡ እነኚህ ታላላቅ ርዕሰ አድባራትና ወ ወገዳማት በትረ መንግሥት አስጨብጠው፣ በልብሰ መንግሥት አስጊጠው፣ ለንግሥና የተገባውን ቅባት ቀብተው እና እጅግ ያማረውንና የተወደደውን ዘውድ ደፍተው ያነግሡታል፡፡ መነኮሳቱና ካህናቱ ለንጉሡ ይጸልዩለታል፣ ደሃ እንዳይበድል፣ ፍርድ እንዳያጓድል፣ ትዕዛዛትን እንዳይሽር፣ ከፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳይዝል ይጸልዩለታል፡፡ በጸሎታቸው ያበረቱታል፣ በምክራቸው እና በተግሳጻቸው በመልካሙ ጎዳና ያስጉዙታል፡፡

ንጉሡም በአምላክ ፈቃድ የተቀባውን የንግሥና ፈቃድ እያሰበ በምድር መልካሙን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ይታትራል፣ በቤተ መቅደስ እየተገኘ አምላኩን ያመሰግናል፣ ለጌታውም የተገባውን ያደርጋል፡፡ የአበውን ቃልና ተግሳጽም ያከብራል፡፡ ጣና ቂርቆስ የኢትዮጵያ ጥንታዊነት የሚገለጥበት፣ ስርዓተ መንግሥትም፣ ስርዓተ ክህነትም የሚጸናበት፣ የሐዲስ ኪዳን መሠረት የሚነሳበት ከከበሩት የከበረ፣ ከተመረጡት የተመረጠ ቅዱስ ስፍራ ነው፡፡

ዘመነ ብሉይ ፍጻሜው ቀረበ፡ ነብያት የተነበዩለት፣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ እንደሚወለድ አስቀድመው የተናገሩለት፣ አድማና ልጆቹ በተስፋ የሚጠብቁት፣ ሰማይና ምድር የማይወስኑት፣ ዘመናት የማይቆጠሩለት፣ አፍላጋትና ቀላያት በእፍኙ የማይሞሉት የጌታ መወለጃ ጊዜ ቀረበ፡፡ ጊዜው በደረሰ ጊዜም በድንግልና ከጸናች፣ ከፍጥረታት ሁሉ ከላቀችና ከተወደደች፣ በሀሳቧም፣ በስገዋም፣ በነብሷም ንጽሒት እና ብጽሒት ከሆነች እመቤት ተወለደ፡፡

በተወለደም ጊዜ ሄሮድስ የተባለ ንጉሥ ሕጸናትን ይገድል ነበርና ማርያም ልጇን ይዛ ተሰደደች፡፡ ወደ ኢትዮጵያም መጣች፡፡ በምድረ ኢትዮጵያም በብዙ ሥፍራዎች ተቀመጠች፡፡ እርሷ የተቀመጠችባቸውና ያረፈችባቸው ሥፍራዎችም የተባረኩ የተቀደሱ ናቸው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በኢትዮጵያ ብዙ ሥፍራዎች ተቀምጣለች ኡደቷን የጨረሰችው ግን በጣና ቂርቆስ ነው ይላሉ አባ፡፡ ጣና ቂርቆስ የመጀመሪያው የሐዲስ ኪዳን ቅዱስ ቤተሰብ ማረፊያ ነውም ይላሉ፡፡ የአንድነት ምልክት ነው፡፡
በዚያች ቅድስት ምድር የተቀደሰችው እመቤት ለሦስት ወር ከአሥር ቀናት ተቀምጣበታለች፡፡ ያቺ ምድር የተቀደሰች ናት፡፡ ያቺ ምድር በበረከት የተመላች ናት፡፡ ያቺ ምድር በቅዱሳን የተከበበች፣ ያቺ ምድር በታሪክ የከበረች፣ ያቺ ምድር ሃይማኖትን ጠብቃ የኖረች ናት፡፡

ዘመኑ ደረሰ፡፡ ሄሮድስ ሞቷልና ተመለሱ የሚል ቃል መጣ፡፡ ጌታም እናቱን እንሂድ ባላት ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም ኢየሩሳሌም ሀገሬ ናት ነገር ግን ከእነ ልጄ አሰድዳኛለች፣ የዚህች ሀገር ሰዎች ደግሞ አያውቁኝም ያለ ሀገር ሀገር ሰጥተው ያኖሩኛል፣ ስለዚህ የምኖረው በዚህች ሀገር ነው፣ የዚህች ሀገር ሰዎች እግዚአብሔርን ይፈራሉ አለችው፡፡ ስለ ጽድቅ የሚደንግጥ ብጹዕ ነው፡፡ እንደተባለ ኢትዮጵያዊያን ልባቸው ሩህሩህ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ዘር አይመርጡም፣ ሀገር አይመርጡም ማንም ሰው ሲመጣ ይቀባለሉ፡፡
ልጇም ይሄን በሰማ ጊዜ እዛ ሄጄ የዓለምን ድኅነት እፈጽማለሁ፡፡ ይህችን ሀገር ከወደድሻት የአንቺ እርስት አድርጌ እሰጥሻለሁ አላት፡፡ አንቺም እነርሱን ትወጂያለሽ፣ እነርሱም በአንቺ ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ አላት፡፡ ጌታ እናቱ ማርያምን አንቺም የኢትዮጵያ እናት ሁኚ፣ ኢትዮጵያም የአንቺ ልጅ ትሁን አላት፡፡ ያን ቅዱስ ሥፍራ በየቀኑ እየመጣሽ ትጎበኝዋለሽ በማለት ቃል ገባላት፡፡ የከበረው ቃል ኪዳንም በዚያ ሥፍራ ተፈጸመ፡፡ ይህም ቃል ኪዳን እስከ ዘመነ ምጽዕት ድረስ ጸንቶ ይኖራል ይላሉ፡፡ አምላክ የወደደውን ስም ኢትዮጵያዊያን ሁልጊዜም ይጠሩታል፤ ይወዱታል፡፡ ማርያም ማርያም ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ሳያውቁ ተቀበሏት፣ ሲያውቋት የመበረከት ምንጭ ሆነቻቸው ነው ያሉኝ አባ፡፡ ኢትዮጵያ ለምን ለብቻ ተመረጠች? ለምንስ ለማርያም የአስራት ሀገር ተደርጋ ተሰጠች አድሎ አይሆንም ወይ? ለሚሉ ይላሉ አባ እንደ ሥራዋ የተሰጣት በረከት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በሥራ ቀድመናል፣ ኢየሩሳሌም የገፋችውን ኢትዮጵያ አመለከችው፣ ኢየሩሳሌም አሳደደችው፣ ኢትዮጵያ አስተናገደችው፣ይህች ሀገር ሽልማት ይገባታልና ታላቋን ሽልማት ማርያምን ሸለማት ይላሉ አባ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እነኋት እናትህ ብሎ ለዮሐንስ ከመስጠቱ አስቀድሞ ለኢትዮጵያ በሁለት ዓመቱ ሰጥቷል ነው ያሉኝ፡፡
ጊዜው ደረሰ፡፡ ጌታ የዓለምን መዳን ይፈጽም ዘንድ ወደ እስራኤል ሊመለስ ነው፡፡ ጸሐነ በደመና፣ በደመና ጫናት እንደተባለ፤ ማርያምም በደመና ተጭና ወደ እስራኤል ሄደች፡፡ ይህም ሥፍራ ጣና ተባለ፡፡ ይህ ሁሉ ታሪክ የተፈጸመበትም ጣና ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ነው፡፡ ምህረት ለሚያደርጉ ለኢትዮጵያውያን የምህረት እናት ተሰጣቸው፡፡ እርሷ እናታቸው፣ እነርሱም የአስራት ልጆቿ ሆኑ፡፡
በምድራዊ ዓለም የታሪክ አባት የሚባለው ሄሮዳተስ ኢትዮጵያውያን ሩህሩዎች፣ ከመንገድ ዳር ድንኳን ተክለው የሚያበሉ፣ ሰውነታቸውን የሚያድስ የጠራ ተፈጥሯዊ ውኃ ያላቸው፣ ጨዋታ አዋቂዎች፣ ስርዓት ጠባቂዎች፣ ገራግሮች ናቸው ብሏል ይላሉ አባ፡፡ እግዚአብሔርን የሚያከበሩ፣ በትዕዛዙም የሚኖሩ፣ ማርያምም ሕግ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ናቸው ያለቻቸው ናቸው ኢትዮጵያውያን፡፡ ዛሬስ በእግዚአብሔር ፊት የተወደዱት ኢትዮጵያውያን አሉን? ይሄም ይቅር በሄሮዳተስ አገላለጽ ልክ የሚሆን ኢትዮጵያዊ ዛሬ አለን? ብለው ይጠይቃሉ ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን፡፡

ይህን ቅዱስ ሥፍራ ክፉዎች አልረገጡትም፣ አይረግጡትምም፣ ለምን ካሉ የሚጠብቀው ሃያል፣ የሚጠብቀው እሳተ ነበልባል፣ የሚጠብቀው የማይሞከርና የማይቻል ነውና፡፡ ይህ ታላቅ ስፍራ ለኢትዮጵያ ብዙ ነገር ነው፡፡ ስርዓተ መንግሥት፣ እና ስርዓተ ክህነት የጸናበት ነውና፡፡

የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መስቀላቸው፣ ካባቸው በዚያ ሥፍራ ይገኛል፡፡ ታሪክ አጥፊዎች አልደፈሩትም፣ አይደፍሩትም፤ ሕንጻው አርጅቶ ታድሶ ያውቃል እንጂ ሃይማኖት የሌለው አጥፍቶት አያውቅም ይላሉ አባ፡፡
ዜማን ከመላእክት ተምሮ፣ አክሱምን በዜማ ቀድሶ፣ አንቀጸ ብርሃንን አድርሶ ቅዱስ ያሬድ ወደጣና መጣ፡፡ በዚያም ሆኖ ድጓውን ጻፈ፡፡ እርሱ የጻፈው ድጓ ዛሬም አለ፡፡ መስቀሉና ካባውም አለ፡፡ እርሱ ቀለም የበጠበጠባቸው ድንጋዮች ዛሬም አሉ፡፡ መምህር ኤስድሮስ ሦስት መቶ መጻሕፍትን በቃላቸው ያጠኑበት ስፍራም ነው ርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቂርቆስ፡፡ ማርያም ቁጭ ብላ የጸለየችበት፣ ቆማም የጸለየችበት፣ እጅግ የተወደዱት የእግሮቿ ኮቴ ያለበት፣ የአህያዋ ሰኮና በዓለት ላይ የሚገኝበት፣ የኢትዮጵያ ካርታ ከዓለት ላይ ተቀርጾ የሚገኝበት፣ የኦሪት መሰዊያ ዛሬም ድረስ ያለበት ሥፍራ ነው ጣና ቅዱስ ቂርቆስ፡፡ በዚህ ሥፍራ ታቦተ ጽዮንን ያመጣት የካህኑ የአዛርያስ መቃብርም ይገኛል፡፡

የማይጠወልግ ጌጥ፣ የማይረግፍ ፈርጥ ነው፡፡ በዚያ ገዳም ውስጥ የእኛ እንጂ የእኔ የሚባል የለም፡፡ የግል ሀብትና ንብረት የለም፡፡ ክርስትና አንድነት ነው፣ ሃይማኖት አንድነት ነው፣ አንድነት ከሌለ ኃይል የለም፣ ሞት ማለት መለየት ነው፡፡ የጥፋት ልዩነትን የሚወድ ሰው ካለ ሞቷል ማለት ነው፣ መለያየትን ካመጣ መሞት፣ መጥፋት ነው፣ አንድነት ማለት መኖር ማለት ነው ይላሉ አባ፡፡ በዚያች ሥፍራ ሰው ሁሉ የራሱን ፈቃድ ለእግዚአብሔር ፈቃድ አስገዝቶ ይኖራል፡፡

ሂዱ ቅዱሱን ምድር እዩት፣ ቅዱሱን ሥፍራ ዳብሱት፣ እጅግ የከበረውን ታሪክ ስሙት፣ ከማዕዛዎች ሁሉ የላቀውን ማዕዛ አሽትቱበት፣ መልካሙን ነገር ተመልከቱት፡፡ በዚያ ሥፍራ አለቶች ሳይቀር ታሪክን ይነግራሉ፣ ሃይማኖትን ያስተምራሉ፣ ቀደምትነትን ይመሰክራሉ፡፡


አማራ ሚድያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ)

በፈጣን የዕድገት ግስጋሴ ላይ እየተጓዘች የምትገኘዋ ውቢቱ ሞጣ ከተማን በጥቂቱ*****  የሞጣ ከተማ አስተዳደር በምስራቅ ጎጃም መስተዳደር ዞን ከሚገኙ 17 ወረዳዎችና 8 የከተማ አስተዳደሮች...
15/06/2023

በፈጣን የዕድገት ግስጋሴ ላይ እየተጓዘች የምትገኘዋ ውቢቱ ሞጣ ከተማን በጥቂቱ
*****
የሞጣ ከተማ አስተዳደር በምስራቅ ጎጃም መስተዳደር ዞን ከሚገኙ 17 ወረዳዎችና 8 የከተማ አስተዳደሮች አንዷ ስትሆን በአራቱም አቅጣጫዎች ከ2 እጁ እነሴ ወረዳ ጋር ትዋሰናለች፡፡

የሞጣ ከተማ አስተዳደር ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ባህርዳር 120 ኪ.ሜ፣ ከዞኑ ዋና ከተማ ደ/ማርቆስ 202 ኪ.ሜ፣ ከሃገራችን መዲና አዲስ አበባ 370 ኪ.ሜ ርቀት የምትገኝ ሲሆን በመሰራት ላይ ያለው የኮምቦልቻ ግንዶይወን የአስፓልት መንገድ ፣ ተጠናቆ ስራውን የጀመረው የደብረ ማርቆስ ዲጐጺዮን ሞጣ ጠጠር መንገድ፣ በተጨማሪም በቅርቡ ስራዉን የሚጀምረው የሞጣ ጃራጋዶ ደብረታቦር እና ከአዲስ አበባ ሞጣ ባህርዳር የሚገነቡ የአስፓልት መንገድ ግንባታዎች ከተማዋን አቋርጠው የሚሄዱ የትራንስፖርት አውታሮች ናቸው ።


የሞጣ ከተማ ስያሜን ስንመለከት ሁለት አይነት አመለካከቶች ይነሳሉ፡፡ የመጀመሪያው አመለካከት “አባ ሞፃ” ከሚባል መነኩሴ ስም የተወሰደ ነው የሚል ሲሆን ይኸውም መነኩሴ የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከመደበሩ በፊት የነበረና በቤተክርስቲያኑ የተቀበረ የመጀመሪያው ሰው ነው የሚል ነው፡፡

በብዛት ተቀባይነት ያለው አመለካከት ደግሞ የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አሰሪ ከሆነችው ከንግስት ምንትዋብ ልጅ ከልዕልት ወለተ እስራኤል ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ልዕልቲቱ ቤተክርስቲያን ማሰራት ትወድ ስለነበር አባቶች እሷ ከሞተች ማካካሻ ይሆናል ተብሎ የተሰጣት በመሆኑ ከዚያ የመጣ ስያሜ ነው ይላሉ፡፡

ልዕልት ወለተ እስራኤል የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ከደበርሽ ከተማዋ ታድጋለች ያንች ህይወት ግን ያልፋል ነገር ግን መድሃኒያለም ቤተክርስቲያንን ከደበርሽ እድሜሽ ይረዝማል ከተማዋ ግን አታድግም የሚል ራዕይ አይታ ስለነበር ከተማዋ ብታድግና የእኔ ህይወት ቢያልፍ ይመረጣል በማለት የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ደበረች ከዚያም በኋላ ህይወቷ እንዳለፈና ከተማዋም ለእርሷ ማካካሻ እንዲሆን ተብሎ ከ1747 ዓ.ም ጀምሮ ስያሜዋን ያገኘች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ለኑሮ ብሎም ለስራ ሞቹ የአየር ንብረት ያላት በአሁኑ ሰዓት እጅግ በፈጣን የእድገት ግስጋሴ ላይ በምትገኘዋ ውቢቱ ሞጣ ከተማ ባለሀብቶች ቦታ ወስደው በመረጡት የኢንቨስትመንት አማራጮች ቢሰማሩ በአጭር ጊዜ እርሳቸውን ብሎም የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላሉ። እናም ልማታዊ ባለሀብቶች በርካቶች ሰርተው ያተረፉባትን የፍቅር፣የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነቸው መጣ ከተማን ምርጫችሁ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

"እንደ ኢትዮጵያዊነታችን የበጀት፤ እንደ አማራነታችን ደግሞ የማንነት ጥያቄያችን ምላሽ ይሰጠን" ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ
14/06/2023

"እንደ ኢትዮጵያዊነታችን የበጀት፤ እንደ አማራነታችን ደግሞ የማንነት ጥያቄያችን ምላሽ ይሰጠን" ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

3 ሰው መጫን የምትችል ባጃጅ የሰራው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ጌታቸው አባተ *******በምስራቅ ጐጃም ዞን በሸበል በረንታ ወረዳ በየዕድውኃ ከተማ የበረንታ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሲሆን 3 ሳ...
25/05/2023

3 ሰው መጫን የምትችል ባጃጅ የሰራው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ጌታቸው አባተ
*******
በምስራቅ ጐጃም ዞን በሸበል በረንታ ወረዳ በየዕድውኃ ከተማ የበረንታ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሲሆን 3 ሳይክሎችን እና ሌሎችን የወዳደቁ ብረታ ብረቶችን በመጠቀም ነጃጅ አልባ የሆነች ባጃጅ መስራት ችሏል፡፡

በምስራቅ ጐጃም ዞን በደብረ ማርቆስ ከተማ በተካሄደው የፈጠራ ስራ ውድድር ከ17 ወረዳዎች 2ኛ መዉጣት ችሏል፡፡

ወደፊት የወዳደቁ የሞተር እና የመኪና ዕቃዎችን ማግኘት ከቻለ ኢንጅን/ሞተር በመጠቀም ከባጃጅ የተሻለ መኪና መስራት እንደሚችል ገልጿል፡፡

ባጃጁ በነዳጅ እንዳይሰራ የሆነዉ የሞተር ግብዓት ችግር በማጋጠሙ ወደ ሳይክል ፔዳል በመቀየር የተሰራ ነዉ፡፡ የኋላ እና የፊት ረዥም፣ አጭር መብራት፣ ክላክስ/ጥሩንባ/ ፣የዕቃ መጫኛ ያላት ሲሆን የመብራት፣ ክላክስ/ጥሩንባው /በባትሪ ድንጋይ የሚሰራ ነው፡፡

ተማሪ ጌታቸው አባተ ሌሎች ትናንሽ የሆኑ የድንቃ ድንቅ የፈጠራ ስራዎች ያሉት ሲሆን ትላልቅ የፈጠራ ስራዎች ለመስራት የግብዓት ችግር ያለበት መሆኑን ተናግሯዋል፡፡

በፈጠራ ስራዉ የዕድዉኃ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ እና የበረንታ 2ኛ ደረጃ መምህራኖች ድጋፍ እንዳደረጉለት ገልጻል ሲል የዘገበዉ የሸበል በረንታ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ነዉ፡፡

23/05/2023

Address

Debra Markos

Telephone

+251986610875

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Gebeyehu Dereus - ገበየሁ ድረስ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Gebeyehu Dereus - ገበየሁ ድረስ:

Share