15/02/2024
እውነተኛ ገጠመኝ
ጥበብ ጥንትም ነበረ፣ ዛሬም አለ፣ ነገም ይኖራል። እውነታው ሰው ጥበብን በተፈጥሮ ሰውኛ ባህሪው ያለምንም ውጫዊ ነገር መፍጠርና መጠቀም እየቻለ በየዋህነት፣ ባለማወቅ፣ ለሌላ ነገር ሙከራና አዋቂ ሰው ፍለጋ ሲንከራተት መታየቱ ነው። ሄዶ፣ ሄዶ እውነታውን አረጋግጦ እርሱም ካመጣው ለውጥ እራሱንም ወገኑንም ማስተማር እና መቀየር ሲችል ተፈጥሯዊ ለውጦችን፣ የገጠመውን፣ ያጣውን፣ የጠፋበትን በውስጡ አምቆ ይዞት ይሞታል።
አዲስ ነገር የለም። የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው። ይህን እንድፅፍ ያበረታታኝን ነገር ልንገራችሁ። ወደ ገጠር ሄጄ ነበር። በዚያ አካባቢ ስላለው እውነተኛ አሁናዊ ሁኔታዎችን አውጥተን አውርደን ስንጫወት አንድ ነገር ሰማሁ።
በአሁኑ ሰዓት ሁሉን ነገር ማድረግ እንችላለን የሚሉ አጭበርባሪዎች በዝተዋል። በእየ ከተማው፣ በድህረ ገፆች ላይ፣ በእየ ግድግዳውና እንጨቶች ላይ ማስታወቂያ በመለጠፍ የሰው ንብረት ይቃርማሉ። ልክ ሸረሪት ለማጥመድ እንደምትጥለው መረብ አይነት። የእርሷስ ተፈጥሯዊ ባህሪዋ ነው። በሰው ሰውኛው እንዴት እንዲህ በፈጣሪ አምሳል ተፈጥሮ። እናም አንዳንድ የዋሆች ሠላማቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ማንነታቸውን እያጡ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ የገጠር ልጅ ብር የሚያባዛ እንዳለ ይነገረውና ጥበቡን ለመጠቀም ፈልጎ አለ በተባለበት ቦታ ይሄዳል። እንደደረሰም ፍላጎቱን ያስረዳዋል። ጥቂት ብሮችን ይቀበለውና ባለሙያ ነኝ ባዩም ፈጥኖ ወረቀቶቹን በብር ቅርፆ ቆራርጦ ጥበቡን አሳይቶ ብር አስመስሎ ይልከዋል፣ ተመልሶ እንደሚመጣም እርግጠኛ ነበር።
አላዋቂው በጣም ደስ አለው። በአይኑ ድግምት ደግሞ ወረቀቱን ብር አስመስሎ እንደሰጠው አላወቀም ነበር። ቀጠለና የዋሁ ሰውዬ የመኖሪያ ቤቱን በ250,000.00 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሽህ) ብር ሸጦ ቢያባዛው ብዙ እንደሚሆን በማሰብ በድጋሚ ወደ ጥበበኛው ቤት ሚስቱን አሸክሞ ሄደ።
ተገናኙና ብሩን አስረከቡ። አባዛሁት አለና ለጊዜው 30,000.00 (ሰላሳ ሽህ) ብር ሰጥቶ እስከምጨርስ ተዝናንታችሁ ኑ ብሎ ወደ ከተማ ላካቸው። እነርሱም አንድም ሳያስቀሩ ተዝናኑበት። ከዛም ወደ ጥበበኛው ደወሉ። ባለቤቱ ነኝ ያለች ሴት አነሳችው ስራ ላይ ስለሆነ ነው ጠብቁት ይደውልልላችኋል አለች። ብዙ ጠበቁ አልደወለም መሸ። ደወሉ ስልኩ አይጠራም፣ ተዘግቷል። ግራ ገባቸው። ቤታቸው ተሽጧል፣ ማረፊያ የላቸውም፣ በእጃቸው ብር የለም ወደ ቀያቸው መመለሻ የላቸውም። ማደሪያ፣ መመገቢያ የላቸውም። ቀኑ ጨለመባቸው። ጣታቸውን ወደ ጥበበኛው ሰውየ የጠቆማቸው ላይ በማድረግ ለመገዳደል ወስነው ተጣሉ። ገላጋይ ገብቶ ለማስታረቅም ተቸገረ። ከዚህ አይነት መሸወድ ያድነን።
በነገራችን ላይ ይህን ድርጊት ከአሁን በፊት በእውነተኛ ገጠመኝነት አውቀዋለሁ። ልዩነቱ እዚህ ጋር የተሸወደው ባለሀብት ነው። 30,000.00 (ሰላሳ ሽህ) ብር ወስዶ (60,000.00) ስድሳ ሽህ አድርጎ አመጣ። ይህ ከሆነማ ብሎ 500,000.00 (አምስት መቶ ሽህ) ብር ይዞ ሄደ። ጥበበኛው ሁሉንም ብር ይዞ ተሰወረ። ባለሀብቱ አበደ፣ ዘለለ፣ ዘለለ፣ ፈረጠ ብሩን ማግኘት አልቻለም። የቤቱን ሀብት እየሸጠ እቁቡን መጣል ቀጠለ። የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።
ምክር፥
ከአላዋቂ የሰው ንብረት ዘራፊዎች እራሳችሁን ጠብቁ።