08/03/2026
በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ሳይንት ወረዳ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ላይ በደረሰ ጥቃት አገልጋዮችና ምዕመናን ተገደሉ 😥
በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት፣ በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ በተሰነዘረ ጥቃት በርካታ ዜጎች ተገደሉ።
በክልሉ በደቡብ ወሎ ዞን፣ ሳይንት ወረዳ በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ አምስት የቤተክርስቲያኗ አገልጋዮች መገደላቸው ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም ከ26 በላይ በሚሆኑ የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
ጥቃቱ የደረሰው በወረዳው በሚገኘው የነገሥት አትሮንሰ ማርያም ገዳም ውስጥ፣ የዕለቱ ቅዳሴ ከተጠናቀቀ ከደቂቃዎች በኋላ የቤተክርስቲያኑ አባቶች እና ምዕመናን ወደ ደጀ ሰላም እያመሩ በነበሩበት ወቅት መሆኑ ተነግሯል። በተተኮሰው በዚህ ከባድ መሳሪያም የቀድሞ የገዳሙ አስተዳዳሪ፣ ሦስት ዲያቆናት እና አንድ አቃቤ መገደላቸው ታውቋል።
ለጥቃቱ እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም። ይሁን እንጂ፣ የቤተክርስቲያኑ ምዕመናን ከባድ መሳሪያውን የተኮሱት የመንግሥት ኃይሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል። በአንጻሩ፣ የመንግሥት ምንጮች ጥቃቱን "ጽንፈኛ" ሲሉ በሚጠሯቸው የፋኖ ታጣቂዎች እንደተፈጸመ አድርገው ከሰዋል ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ የአካባቢው የመንግሥት አመራሮች የሰጡት ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ የለም።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው ትናንት ቅዳሜ፣ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ሲሆን፣ ገዳሙ በአካባቢው ከሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ታሪካዊ ገዳማት መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።