25/10/2022
በኦሮሞ ነጻነት ጦር ታጣቂዎች የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በርካቶች ተገደሉ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሽዋ ዞን ተገደው የወጡ ሰላማዊ ዜጎች በተገኙበት የታጣቂዎች የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በምዕራብ ሸዋ በዞን በምትገኘው ጮቢ ወረዳ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ያሰለጠናቸውን ታጣቂዎች እያስመረቀ ሳለ ነበር የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መፈጸሙ የተነገረው።
ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰማው የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ሰላማዊ ዜጎች በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዲገኙ አስገድዶ የምርቃት ስነ-ስርዓቱ እየተካሄደ በሚገኝበት ወቅት ነው።
በዚህ ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን እና የታጣቂ ቡድኑ አባላትን ጨምሮ እስከ 70 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ120 ያላነሱ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት ታጣቂ ቡድኑ ላይ ያነጣጠር የአየር ጥቃቶችን በምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ሲፈጽም ቆይቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ትናንት በትዊተር ገጻቸው ላይ ከጥቅምት 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ቢያንስ 6 የሰው አልባ አውሮፕለን ጥቃቶች ተፈጽመዋል ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሜታ ወልቂጤ እና ጮቢ ወረዳዎች የተገደሉ 'ሰላማዊ ሰዎች ከ150 በላይ ናቸው' ይላሉ።
ኦዳ ተርቢ በጮቢ ጨምሮ 150 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ይበሉ እንጂ በወረዳው የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው የታጣቂ ቡድኑ የምርቃት ስነ-ስርዓት እየተካሄደ ሳለ ስለመሆኑም ይሁን በእነዚህ የአየር ጥቃቶች የተገደሉ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ስለመኖራቸው ያሉት ነገር የለም።
የአየር ጥቃቶቹን በተመለከተ ቢቢሲ የጮቢ ወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ የአካባቢው ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ መረጃ ካለው ተጠይቆ ተፈጽመዋል የተባሉ የአየር ጥቃቶችን በተመለከተ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።