29/08/2025
ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ልታስመርቅ ነው
ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. የአፍሪካ መሪዎች እና ሌሎች የተጋበዙ እንግዶች በሚገኙበት እንደሚመረቅ በኬንያ የኢትዮጵያ ምክትል አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ተናገሩ።
ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት በአፍሪካ ግዙፉ እንደሆነ የተነገረለት ሕዳሴ ግድብ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው ሲካሄድ ቆይቷል።
አምባሳደር ደመቀ ሐሙስ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም. ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ የሕዳሴ ግድብ ሴፕቴምበር 9 [ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም.] በይፋ ምረቃው እንደሚካሄድ አመልክተዋል።
በአምስት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ከአስር ዓመታት በላይ ፈጅቶ የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪው አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በይፋ እንደሚመረቅ አስታውቆ ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረው መጋቢት 24/2003 ዓ.ም. ሲሆን አጠቃላይ ግንባታው 14 ዓመታትን ወስዷል። ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን "በጨለማ ነው የሚኖሩት" ያሉት አምባሳደሩ እነዚህ ሕዝቦች የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታልሞ ግድቡ መገንባቱን ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገንዘብ ማዋጣቱን ያመለከቱት አምባሳደሩ "የነበሩ በርካታ መሰናክሎች" ታልፈው ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ምረቃው እንሚካሄድ ገልጸዋል።
አምባሳደር ደመቀ ኢትዮጵያ ትርፍ የኤሌትሪክ ኃይል ማምረት በመጀመሯ ለጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ መሸጥ መጀመሯንም አስታውሰዋል።
በዚህም የተነሳ ከጎረቤት አገራት ጋር በኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት መተሳሰር ተችሏል ያሉት በማለት፣ ይህም ወደ በፖለቲካዊ ትስስር አንደሚያመራም ተናግረዋል።
የሕዳሴውን ግድብ ተጠናቅቆ ሲመረቅ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የምታከብረው "የአባይ ተፋሰስ አገራት እንዲሁም ቀሪው የአፍሪካ አገራት በጋራ የሚያከብሩት ይሆናል" ሲሉም አክለዋል።
በቅርቡ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ይመረቃል መባሉን ተከትሎ ግብፅ "የዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ መልኩ በምሥራቃዊ ናይል ተፋሰስ የሚደረግ የተናጠል እርምጃን" እንደማትቀበል ለበርካታ አፍሪካ አገራት አሳውቃለች።
14 ዓመታትን የፈጀው እና አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪን የጠየቀው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር ሙሌት ተጠናቆ ምረቃው ጳጉሜ 4 /2017 ዓ.ም. ጥሪ የተደረገላቸው አገራት መሪዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ምክትል አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ አረጋግጠዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጅምሩ እንዲሁም የተካሄዱ አምስት ውሃ ሙሌቶችን በጽኑ ያወገዙት የግብፅ ፕሬዝዳንት፣ ከላይኛው የናይል ተፋሰስ አገራት አንዷ ከሆነችው የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር።
ፕሬዝዳንት ሲሲ "በድጋሚ ለግብፃውያን ማረጋገጥ የምፈልገው 105 ሚሊዮን ዜጎቻችን እና 10 ሚሊዮን የሚሆኑ በአገራችን ያሉ እንግዶቻችን በሕይወት የሚያቆየው ውሃ እንዲነካ ፈጽሞ እንደማንፈቅድ ነው" ብለዋል።
አምባሳደር ደመቀ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ "በአሁኑ ወቅት ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም" ያሉ ሲሆን፣ ግብፅ ታሪካዊ መብት የምትለው "አክትሞለታል" ካሉ በኋላ "ያለው አማራጭ ወደ ትብብር መምጣት ብቻ ነው" ብለዋል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት መሠረት አድርጋ ታሪካዊ ተጠቃሚነቷን በማስጠበቅ የወንዙን ውሃ በበላይነት የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት በመጥቀስ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትቃ