
02/08/2025
የነዳጅ ግብይት ከ50 በመቶ በታች በዲጂታል በፈፀሙ 20 ማደያዎች ላይ ክስ ተመሰረተ፤
ዱራሜ፣ ሐምሌ/2017 ዓ.ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በክልሉ የነዳጅ ግብይትን በህጋዊ መንገድ በማይፈፅሙ አካላት ላይ በሚወሰድ ህጋዊ እርምጃ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንደገለፁት፤ ተቋሙ የነዳጅ ግብይትን በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲከናወኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይቶች በማድረግ በህገ-ወጦች ላይም ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አውስተዋል።
የፌዴራል ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን በመጋቢት ወር ባደረገው ኢንስፔክሽን መሰረት 22 ባለማደያዎች ከ50 በመቶ በታች ግብይት በመፈፀማቸው ከስህተታቸው እንዲማሩ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ኃላፊው ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ ባለስልጣኑ በግንቦት ወር በድጋሚ ባደረገው ማጣራት 20 ማደያዎች ከ 50 በመቶ በታች የነዳጅ ግብይት በዲጂታል መፈፀማቸውን በመግለፅ በአዋጁ መሰረት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማሳሰቡን አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።
በመሆኑም በክልሉ የነዳጅ ግብይት ከ50 በመቶ በታች በዲጂታል ግብይት በፈፀሙ 20 ማደያዎች ላይ በፌደራል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1363/2017 አንቀፅ 25 ንዑስ አንቀፅ 10 መሰረት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ክስ መመስረቱን አብራርተዋል።
የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ሽያጭ በማይፈፅሙ አካላት ላይ በአዋጁ መሰረት ከ2 ዓመት ያልበለጠ እስራትና የ300 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚያስቀጣ ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
አቶ ዳንኤል በህጋዊ መንገድ ግብይታቸውን የሚፈፅሙ አካላት እራሳቸውን ከህገ-ወጥ አሰራር በመጠበቅ ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ክስ የተመሰረተባቸው ባለማደያዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።