28/09/2025
የዳንሻ ከተማ የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር ከ 272 ሺ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ1,005 ተማሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ዳንሻ፦መስከረም 18/2018 ዓ.ም በአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ስቲት ሁመራ ዞን በዳንሻ ከተማ አስተዳደር የዳንሻ ከተማ የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር " ማንም ተማሪ በደብተር እጦት ከትምህርት ገበታ መቅረት የለበትም " በማለት ለ 1,005 ተማሪዎች ከ 272,828 ብር ወጪ በማድረግ የመማርያ ደብተርና እስክርቢቶ ድጋፍ አድርገዋል ።
የቁሳቁስ ድጋፍ በተደረገበት ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መ/ር አብዱልዋሀብ ማሞ እንዳሉት " በማህበሩ ወጣቶች በተጨባጭ የሚታዩ የቤት ጥገናና እድሳት፣የአረጋውያን እና የአቅመ ደካማ አረጋውያን ድጋፍ እና ልዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች እየሰሩ ይገኛሉ ፤
እሄ ደግሞ ሌሎች ወጣቶች እንደ አርአያነት በመውሰድ የማህበሩ አባል በመሆን በጎ ስራዎች መስራት አለብን " ያሉ ሲሆን " ወላጆች የትምሀርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው እና መላው ተማሪዎቻችን ጠንከር ያለ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ የወጣቶቹ በጎ ተግባር ወደ ፍሬ ለመቀየር ሁላችንም ሀላፊነት ልንወስድ ይገባናል " ሲሉ አሳስበዋል ።
የዳንሻ ከተማ የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር ሊቀ መንበር አቶ አባስ ጌታቸው " የአቅመ ደካማ አረጋውያን ቤት ለማደስ እና ለመስራት ከጎናችን ሆነው ልዩ ልዩ ድጋፍ ሲያደርጉልን የነበሩ እና አሁንም በውጭ ሀገር ለሚገኙ እና በከተማችን ያሉ ወንድምቻችን ለተማሪዎች የትምሀርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ከጎናችን ለሆኑት ሁሉ በማመስገን ፤
የተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ከማሟላት በተጨማሪ የተማሪዎች የትምሀርት ደረጃ ማሻሻል ጠንካራ ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል ።
ድጋፋ የዳንሻ ከተማ የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር፣ የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ እና ከትምህርት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከሀገር ወዳድ ዲያስፖራው፣ ከግለሰቦች እና ከተለያዩ ተቋማት የተሰባሰበ ሲሆን ለ1,005 ተማሪዎች ሙሉ ደብተርና 2 የእስክርቢቶ ድጋፍ ተደርጓል ።
መድረኩ ለማህበሩ ድጋፍ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት የእውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት በመስጠት ተጠናቋል ።