
23/07/2025
ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ተጨማሪ አባላትንና በጎ ፈቃደኞችን በማፍራትና ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጠየቀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በማህበሩ መርሆዎች እና ዓላማ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶር ዳንኤል አንጭሶ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በዜግነት፣ በሃይማኖት እና በፖለቲካ አመለካከት ሳይለይ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ዜጎች አፋጣኝ እርዳታ የሚያቀርብ ሰብአዊ ተቋም ነው።
የድርቅና የረሃብ አደጋዎችን ቀድሞ በመዘጋጀት እና በመከላከል ረገድም በየደረጃው ካሉ አጋር አካላት ጋር በትብብር የተጣለበትን ሰብዓዊ ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የአምቡላንስ አገልግሎት፣ የመድኃኒት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን የመንከባከብ ደም የማሰባሰብ መሰል ተግባራት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የድርሻውን ኃላፊነት እየተወጣ ያለ ማህበር ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ብሔራዊ ማህበሩንና የተለያዩ አካላትን በማስተባበር 1 መቶ 6 ሚሊዮን 7 መቶ 63 ሺህ 9 መቶ 15 ብር የሚገመት የተለያዩ እርዳታዎችን በማድረግ ማህበሩ ለወገን ደራሽ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።
ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነም አሳስበዋል።
ማህበሩ ለተጎጂዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የተረጋጋ ማህበረሰብ መገንባት እንዲችል የባለድርሻ አካላት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችንም በዝርዝር አቅርበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዕጩ ዶክተር መለሰ ዘውገ በበኩላቸው፤ ክልሉ ያለውን ፀጋዎች በመጠቀም በቁጭት ከተሰራ በዘርፉ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
በአስተሳሰብ ላይ ከተሰራ ተግባር ቀላል ነው ያሉት ዕጩ ዶክተር መለሰ፤ ለዚህም በጥንካሬም ሆነ በጉድለት የታዩ ተግባራትን ለባለድርሻ አካላት ግልፅ ማድረግ ለውጤታማነቱ አጋዥ እንደሆነም አስገንዝበዋል
ማህበሩ ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚሠራ በመሆኑ በቅንነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር በፈቃዱ ገብረ ሃና፤ የዞን ሴክተሮች የአባልነት ገቢ በተመለከተ የፋይናንስ አሰራር ስርዓትን በተከተለ መልኩ የሚጠበቀውን ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና የንግዱን ማህበረሰብ በማስተባበር ማህበሩን ለመደገፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በመድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በባለድርሻ አካላት በኩል ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል - ከሆሳዕና ጣቢያችን
በተጨማሪም የቪዲዮና ሌሎች መረጃዎቻችንን ለማግኘት የትክክለኛ አድራሻዎቻችን አባል በመሆን ይከታተሉ፡-
ዩቲዩብ- https://www.youtube.com/southradioandtelevisionagency
ቴሌግራም -https://t.me/southRadioAndTelevisionAgency
ዌብ ሳይት - https://srta.gov.et/
ትዊተር - https://twitter.com/SouthRadioandTv