
21/07/2025
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈሰ ቅዱስ ስም አሜን።
ሐምሌ 14 ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ዕረፍቱ ነው፡፡
➛ ዳግመኛም በዚሀች ዕለት የታላቁ አባ መቃርስና የሰማዕቱ የአሞንዮስ መታሰቢያቸው ሆነ፡፡
🔥 ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ
ትውልዱ ከኢየሩሳሌም ነው፡፡ የአባቱ ስም ክርስቶፎሮስ ነው ትርጓሜውም ‹‹ክርስቶስን የለበሰ›› ማለት ነው፡፡ አባቱም አማኝ ክርስቲያን ነበር፣ እናቱ ቴዎዶስያ ግን አስቀድማ ጣዖታትን ታመልክ ነበር፡፡ አባቱ በሞት ሲለየው እናቱ ከብዙ ገንዘብ ጋር ወደ አንጾኪያ ወሰደችው፡፡ በዚያም በእስክንድርያ ገዥ አድርጎ ይሾመው ዘንድ ልጇን ለከሃዲው ንጉሥ ለዲዮቅልጥያኖስ ከብዙ እጅ መንሻ ጋር ሰጠችው፡፡ ይኸውም አብሮኮሮንዮስ ከዲዮቅልጥያኖስ ጋር አብሮ አደግ ስለነበር አሁን በመስፍንነት ሾመው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም አብሮኮሮንዮስን ከሾመው በኋላ ‹‹ክርስቲያኖችን ሰብስበህ ግደል›› ብሎ አዘዘው፡፡
አብሮኮሮንዮስም በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ከተሾመ በኋላ ክርስቲያኖችን ሰብስቦ ለመግደል ከአንጾኪያ ከተማ እንደወጣ የሚያስፈራ ቃል ወደ እርሱ መጣና በስሙ ጠርቶት ‹‹ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ እንዳዘዘህ ብታደርግ አንተ በክፉ አሟሟት ትሞታለህ›› አለው፡፡ አብሮኮሮንዮስም እጅግ ደንግጦ ‹‹ራስህን ትገልጥልኝ ዘንድ ጌታዬ ሆይ እለምንሃለሁ›› አለው፡፡ ወዲያውም የብርሃን መስቀል ታየው፡፡ ዳግመኛም ‹‹እኔ በኢየሩሳሌም የተሰቀልኩ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ›› የሚል ቃል ሰማ፡፡ ይህንንም ከሰማ በኋላ ወደ አንጥረኛ ዘንድ ሄዶ በተመለከተው የብርሃን መስቀል ቅርጽ አድርጎ የወርቅ መስቀል አሠራ፡፡ ወደ እስክንድርያም ሲጓዝ በመንገድ ላይ ዐመፀኞች አረማውያን ሊገድሉት ሲሉ አሠርቶ በያዘው መስቀል ድል አደረጋቸው፡፡
እስክንድርያም ከደረሰ በኋላ እናቱ ‹‹በጦርነት ለረዱህና ላዳኑህ አማልክት መሥዋዕትን ሠዋ›› አለችው፡፡ ልጇ አብሮኮሮንዮስም ‹‹እኔስ አዳኝ በሆነ በመስቀሉ ኃይል ላዳነኝ ለእግዚአብሔር እሠዋለሁ›› አላት፡፡ እርሷም ወደ ዲዮቅልጥያኖስ መልእክት በመላክ ልጇ ክርስቲያን መሆኑን ነገረችው፡፡ ከሃዲውም ንጉሥ ጭፍሮቹን ልኮ ወደ ቂሣርያ ከተማ አስወሰደውና የቂሣርያውን ገዥ ስለ እርሱ እንዲመረምርና እንዲያሠቃየው አዘዘው፡፡
መኮንኑም ወደ እርሱ አቅርቦ በመረመረው ጊዜ አብሮኮሮንዮስ በጌታቸን ታመነ፡፡ መኮንኑም ለመሞት የሚያደርስ ብዙ ጽኑ ግርፋቶችን ከገረፈው በኋላ እሥር ቤት ውስጥ ጣለው፡፡ በዚያች ሌሊት ክብር ይግባውና ጌታችን በታላቅ ብርሃን ውስጥ ሆኖ ታየውና በቃሉ አጽናንቶት ሰማዕትነቱን በድል እንዲፈጽም ነገረው፡፡ ብርሃናዊ በሆኑ መለኮታዊ እጆቹም ዳስሶ ቁስሎቹን ሁሉ ፈወሰለት፡፡ ማሠሪያውንም ፈታለት፡፡ በማግሥቱም መኮንኑ አብሮኮሮንዮስ ሞቶ እንደሆነ እንዲያረጋግጡ ጭፍሮቹን ወደ እሥር ቤቱ ላካቸው፡፡ ከጽኑ ግርፋቱ የተነሣ አስቀድሞ የሞተ መስሎት ነበር፡፡ ጭፍሮቹም አብሮኮሮንዮስን ፍጹም ደህና ሆኖ ቢያገኙት እጅግ ተደንቀው ከእሥር ቤቱ በማውጣት በመኮንኑ ፊት አቆሙት፡፡ ንጉሡም ተደነቀ፡፡ በዚያ ያሉ ሁሉ ‹‹እኛ ሁላችን በአብሮኮሮንዮስ አምላክ አምነናል…›› እያሉ ጮሁ፡፡ ከእርሱም ጋር ሁለት የንጉሡ መኳንንትና ብዙ ሴቶች ነበሩ፡፡ ከሰማዕታቱም ውስጥ እናቱ ቅድስት ቴዎዶስያም ሌሎች ሴቶችና ወንዶች ሰማዕታትን አስከትላ ሰማዕትነቷን ፈጸመች፡፡ መኮንኑም የሁሉንም ራስ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጣቸውና ሐምሌ 6 ቀን የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጁ፡፡
ቅዱስ አብሮኮሮንዮስን ግን ሦስት ቀን በእሥር አቆዩት፡፡ መኮንኑም ከዚያ አውጥቶ ለአጣዖታቱ እንዲሠዋ በድጋሚ አዘዘው፡፡ ቅዱሱም ‹‹ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ አውቄያለሁ፣ ያንተ ጣዖታት ግን ከድንጋይና እንጨት በሰው እጅ የተሠሩ የማይጎዱ የማይጠቅሙ ራሳቸውንም ማዳን የማይችሉ ናቸው›› አለው፡፡ መኮንኑም እጅግ ተቆጥቶ ጎኖቹን በሰይፍ እንዲሰነጣጥቁት አዘዘ፡፡ አንዱም ጭፍራ እንደታዘዘው ጎኖቹን በሰይፍ ሊሰነጥቅ እጁን ሲዘረጋ ያንጊዜ እጁ ደረቀች፣ ወድቆም ሞተ፡፡ በዚህም ድጋሚ ተናደው በመሬት ላይ ጥለው በጽኑ ግርፋቶች ካሠቃዩት በኋላ ጎኖቹን በሰይፍ ሰንጥቀው በቁስሉ ውስጥ መጻጻ ጨመሩበትና እሥር ቤት ውስጥ ወረወሩት፡፡ በዚያም ሲሠቃይ ከቆየ ከሁለት ቀን በኋላ በጉድጓድ ውስጥ እሳት አንድደው በእሳቱ ውስጥ ወረወሩት፡፡ ጌታችንም አዳነውና ምንም እንዳልነካው ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ መኮንኑ ማሠቃየቱ በሰለቸው ጊዜ በመጨረሻ ራሱን በሰይፍ አስቆረጠውና የቅዱስ አብሮኮሮንዮስ የሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነ፡፡ 5 አክሊላትም ወርደውለታል፡፡ ጌታችንም ተገልጦለት ታላቅ ቃልኪዳን ከገባለት በኋላ ነፍሱን በክብር ተቀበላት፡፡ የቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን።
🔥 ሰማዕቱ አባ አሞንዮስ
ጨካኙ አርያኖስ የክርስቲያን ደም እንደውኃ እያፈሰሰ ወደ እስና አገር በደረሰ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው በአባ አሞንዮስ ሥር ተቀምጠው ሃይማኖትን ሲማሩ አገኛቸውና ሁሉንም ይዞ ገደላቸው፡፡ አባ አሞንዮስን ግን አሥሮ ወስዶ ለጣዖታቱ እንዲሰግዱና እንዲሠው አዘዛቸው፡፡ አባ አሞንዮስ ግን ‹‹ከንቱ የሆነ የእንቆቅልሽ ጨዋታህን ብላሽ የሆነ ነገርህንም መስማት አልወድም፣ የረከሱ ጣዖቶችህንም ማየት አልፈልግም›› ብለው ለመኮንኑ ለአርያኖስ መለሱለት፡፡ አርያኖስም በዚህ ጊዜ እጅግ በቁጣ ተመልቶ አባታችንን በሕይወት ሳሉ እሳት ውስጥ እንዲጣሉ አዘዘ፡፡ አባታችንም ወደ እሳቱ ውስጥ ከመጣላቸው በፊት እጅና እግራቸውን እንደታሰሩ ስለ አርያኖስ ጸለዩለት፡፡ ጸሎታቸውንም ከፈጸሙ በኋላ አርያኖስም ተመልሶ እርሱም ራሱ ሰማዕት እንደሚሆን በእርሱ ላይ ትንቢት ተናገሩ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ አሞንዮስ ወደ እሳቱ ተወርውረው ያማረ ሰማዕትነታቸውን በድል ፈጸሙ፡፡ የድል አክሊልንም ተቀዳጁ፡፡ ሥጋቸውንም እሳቱ ከነደደበት ቦታ ባወጡ ጊዜ የእሳቱ ነበልባል ምንም አልነካቸውም ነበር፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡
በአባ አሞንዮስም ትንቢት መሠረት ጨካኙ መኮንን አርያኖስም በመጨረሻ ዘመኑ በጌታችን አምኖ ሰማዕት ሆኖ በክብር አርፎ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀብሏል፡፡ የአባ አሞንዮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን።
🔥 ታላቁ መቃርስ
መቃርስ (መቃርዮስ) ማለት ‹‹ቅዱሱ ለእግዚአብሔር›› ማለት ነው፡፡ ከደቡባዊ ግብፅ ከተወደዱ ደጋግ ክርስቲኖች የተገኘ ታላቅ አባት ነው፡፡ አባታቸው አብርሃም እናታቸው ሣራ ይባላሉ፡፡ እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳሉት እንደ አብርሃምና ሣራ እጅግ ደጎች ነበሩ፡፡ ልጅ ግን አልነበራቸውምና በስለት መቃርስን ወለዱ፡፡ ሲያድጉም በግድ ያለፈቃዳቸው ሚስት አጋቧቸው፡፡ አባ መቃርስ ግን ወደ ሙሽራይቱ በገቡ ጊዜ ዐውቀው እንደታመሙ ሆነው ተኙ፡፡ ‹‹ከበሽታዬ ለጥቂት ጊዜ ጤና ባገኝ ወደ ገዳም ልሂድ›› ብለው ወደ አስቄጥስ በረሃ ሄዱ፡፡ መልአክም ተገልጦ ‹‹ይህች አስቄጥስ የአንተና የልጆችህ ርስት ናት›› አላቸው፡፡ ወደ ቤተሰባቸውም በተመለሱ ጊዜ ሙሽራ እጮኛቸው በድንግልና እንዳለች ሞታ ደረሱ፡፡ ከጥቂት ቀንም በኋላ እናትና አባታቸውም ዐረፉ፡፡ እርሳቸውም ንብረታቸውን ሁሉ ለድሆች መጽውተው ገዳም ገቡ፡፡ ሕዝቡም ደግነታቸውንና እውነተኛነታቸውን አይተው ትንሽ ማረፊያ ሠርተው ሌሎች እንዲያገለግሏቸው አደረጉ፡፡
ከዕለታትም በአንድ ቀን አንዲት ሴት ልጅ ከጎረምሳ አርግዛ ሳለ ጎረምሳው ‹‹አባትሽ ሲጠይቅሽ ከአባ መቃርስ አረገዝኩ በይ›› ብሎ መከራትና ለአባቷ እንደተባለችው ተናገረች፡፡ ‹‹አባ መቃርስ በግድ ደፍረውኝ አረገዝኩ›› አለች፡፡ የከተማው ሰውም አባ መቃርስን ከበዓታቸው አውጥተው ለሞት እስኪደርሱ ድረስ ደበደቧቸው፡፡ መላእክትም በሰው አምሳል ተገልጠው ዋስ ሆነው ለልጅቷም ምግቧን ሊሰጡ ተስማምተው ወደ በዓታቸው መለሷቸው፡፡ አባ መቃርስም ለራሳቸው ‹‹መቃርስ ሆይ እንግዲህ ባለ ሚስትና ባለ ልጅ ሆነሃልና ሌሊትና ቀን መሥራት ይገባሃል›› እያሉ ቅርጫቶችን እየሠፉ ለሚያገለግላቸው ልጅ እየሰጡት እርሱ ሸጦ እያመጣ ብዙውን ለዚያች በዝሙት ጸንሳ በሳቸው ላሳበበች ሴት ይሰጡ ጀመር፡፡ መውለጃዋም በደረሰ ጊዜ እስከ 4 ቀን ድረስ በጽኑ ሥቃይ ቆየች፡፡ እውነቱንም ተናግራ ንስሓ በገባች ጊዜ ወደ አባ መቃርስ ዘንድ አደረሷት፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ‹‹አባታችን ይቅር በሉን›› ብለው ከእግራቸው ላይ ሲወድቁ ይቅር ብለዋቸው ቀድሰው አቆረቧቸው፡፡
ከዚህ በኋላ መልአኩ ወስዶ አስቄጥስ ገዳም አደረሳቸው፡፡ የቅዱሳኑ የመክሲሞስና የዱማቴዎስ በዓት ወደ ሆነች ቦታም አስገብቶ በዚያ በልጆቻቸው ቦታ ላይ በዓታቸውን እንዲያጸኑ ነገራቸው፡፡ አባ መቃርስ ወደ አባ እንጦንስ ዘንድም በመሄድ በረከታቸውንና ምክራቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡ ሰይጣናትም በእርሳቸው ላይ የሚያደርሱትን ክፉ ነገር ሲመካከሩ ይሰሟቸው ነበር፡፡ በእሳት እያቃጠሉ ፈተኗቸው፣ የዝሙት መንፈስ እያመጡም ፈተኗቸው፣ በዚህም ትዕግስትን ቢያደርጉ በሌላም ዓለማዊ ክብርን መውደድን፣ ትዕቢትን፣ መመካትን፣ ታካችነትን፣ ስድብን፣ ሃይማኖት ማጣትን፣ ተስፋ መቁረጥን በልባቸው አሳደሩባቸው፡፡ በአጋንንት ምክንያት ይህም እንደሚመጣባቸው አባ እንጦንስ አስቀድመው ነግረዋቸው ነበር፡፡ ወደ አባ እንጦንስም በመሄድ በአጋንንቱ የደረሰባቸውን ፈተናና ጾር ነገሯቸው፡፡ አባ እንጦንስም አመንኩሰው እንዲጸኑ በመምከር ወደ በዓታቸው ሸኟቸው፡፡ አንድ እርኩስ መንፈስ ያደረበት ባሕታዊ አግኝቶ ትንሣኤ ሙታንን አላምንም ቢላቸው ሙት አስነሥትው አሳይተው አሳምነውታል፡፡ ሙቱንም አጥምቀው አመንኩሰውት 7 ዓመት በተጋድሎ ኖሮ በሰላም ዐረፈ፡፡
አባ መቃርስ በበረሃ ውስጥ ራቁታቸውን ጌታችን ከብርዱም ሆነ ከሙቀቱ እየጠበቃቸው 40 ዘመን የኖሩ ጻድቃንን አገኟቸውና ‹‹እንደ እናንተ እንድሆን ምን ላድርግ?›› ቢሏቸው ‹‹ወደ በዓትህ ተመልሰህ ስለ ኃጢአትህ አልቅስ አንተም እንደ እኛ ትሆናልህ›› አሏቸው፡፡ አባ መቃርስም የጻድቃኑን በረከታቸውን ተቀብለው ወደ በዓታቸው ተመልሰው ማልቀስ ጀመሩ፡፡ ጻዲቁ በመጨረሻ ነፍሳቸውን መላእክት ሲያሳርጓት ይፈትኗቸው የነበሩ አጋንንት ‹‹መቃርስ ሆይ አመለጥከን አሸነፍከን…›› እያሉ ሲጮኹ አባ መቃርስም ‹‹እስከ ዛሬ ገና ነኝ፣ በጌታዬ በቀኙ ልቁም በግራው አላወኩምና›› ብለው በትሕትና መለሱላቸው፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን።
ምንጭ፦ የሐምሌ 1️⃣4️⃣ ስንክሳር
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
🍃🍃🍃🍃🍃🍃🍃🍃🍃 🍃🍃🍃🍃
ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ
እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ
ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ
እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ
እም እለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን
ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን
ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን
ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን
እስከ አረጋዊ ልሒቅ እምንዑስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ
ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ
ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ
ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ
በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ
ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ
ወይፈኑ ለነ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ
እምይዜ ወእስከ ለዓለም አሜን።
ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀይቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውንና ያጻፈውንም የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን። አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼⁼
ከታች ያለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን ቤተሰብ ይሁኑ
Tᴇʟᴇɢʀᴀᴍ - https://t.me/Synaxarium
Fᴀᴄᴇʙᴏᴏᴋ
🔸https://m.facebook.com/MeseleNigatuDek0
ሐምሌ 1️⃣3️⃣ ቀን 2011 ዓ.ም