
21/07/2025
ምድር ነገ (ጁላይ 22) በፍጥነት በመሽከርከር በታሪክ አጭር ከሆኑ ቀናት አንዷን እንደምታስመዘግብ ተተነበየ
| የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ባወጡት አዲስ መረጃ መሰረት፣ ምድር ነገ ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 በዘንግዋ ዙሪያ ያላትን የመሽከርከር ፍጥነት በመጨመር በታሪክ ውስጥ ከታዩት አጫጭር ቀናት መካከል ሁለተኛዋን እንደምታስመዘግብ ትንበያ ተሰጥቷል።
ይህ በቅርብ ዓመታት እየታየ ያለው የምድር የማሽከርከር ፍጥነት መጨመር የሳይንስ ማህበረሰቡን ትኩረት ስቧል።
እንደ space.com ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ነገ ምድር አንድ ሙሉ ዙር ለመጨረስ ከመደበኛው 24 ሰዓት ገደማ 1.34 ሚሊሰከንዶች ያነሰ ጊዜ ይወስድባታል ተብሏል።
ይህ በ2020 ከጀመረው የምድር የመሽከርከር ፍጥነት መፋጠን ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የተመዘገቡ የፍጥነት ክብረ ወሰኖችን እየሰበረ ይገኛል ነው የተባለው።
ምድር ለረጅም ጊዜ በጨረቃ የስበት ኃይል ምክንያት እየቀዘቀዘች እና ቀናት እየረዘሙ ቢሆንም፣ ከ2020 ወዲህ እየታየ ያለው መፋጠን ግን ያልተጠበቀ ነው ተብሏል።
የሳይንስ ሊቃውንት ይህ ያልተለመደ የፍጥነት መጨመር መንስኤ ምናልባትም የምድር ፈሳሽ የውስጥ እምብርት (liquid core) ፍጥነት መቀነስ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።
የእምብርቱ ፍጥነት መቀነስ የማሽከርከር ኃይልን በማከፋፈል የውጪውን ንብርብሮች (ማንትል እና ቅርፊት) በፍጥነት እንዲሽከረከሩ ሊያደርግ ይችላል ነው የተባለው።
ይህ መፋጠን ከቀጠለ፣ እ.ኤ.አ. በ2029 አካባቢ "negative leap second" የሚባል፣ ከአቶሚክ ሰዓቶች ላይ አንድ ሰከንድ የመቀነስ ያልተለመደ እርምጃ እንዲወሰድ ሊያስገድድ ይችላል ተብሏል።
ምንም እንኳን ይህ በዕለት ተዕለት ህይወታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ባያሳድርም፣ እንደ ሳተላይቶች እና የጂፒኤስ (GPS) ሲስተሞች ያሉ ትክክለኛ ሰዓት ላይ የሚመሰረቱ ቴክኖሎጂዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ነው የተባለው።
በዚህም የተነሳ፣ ዓለም አቀፍ የሰዓት ተቆጣጣሪዎች የሰዓት ትክክለኛነትን ለማስጠበቅ የሚደረጉ ማስተካከያዎች አስፈላጊ ይሆናሉ ነው የተባለው።