
10/06/2025
የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1.93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ቀረበ።
የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1.93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ቀርቧል፡፡
የረቂቅ በጀቱን መግለጫ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አቅርበው ውይይት እየተካሄደበት ነው።
ከ2018 ረቂቅ በጀት 1.2 ትሪሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 415 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ፣ 315 ቢሊዮን ብር ለክልል መንግስታት ድጋፍ እንዲሁም 14 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ድጋፍ የሚውል ነው።
ከረቂቅ በጀቱ 1 ትሪሊዮን ብር ወይም 73 በመቶውን ከታክስ ገቢ 236 ቢሊዮን ብር ከልማት አጋሮች ቀሪውን ደግሞ ከፕሮጀክቶች ድጋፍ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች ለማግኘት መታቀዱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ገልፀዋል።
በረቂቅ በጀቱ ከጥቅል ሀገራዊ ምርት አንፃር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት 2.2 በመቶ እንዲሁም የተጣራ የበጀት ጉድለት 1 በመቶ መሆኑንም የገንዘብ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
መንግስት የበጀት ጉድለቱን በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ ብድር በመውሰድ ሳይሆን በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ እንደሚሸፍን ነው የገለፁት።
ጥብቅ የገንዘብ እና የበጀት ፖሊሲን በመከተል የመንግስት ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሸፈን ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።
ይህም የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እና ውጤታማ የበጀት አጠቃቀምን ለመተግበር የሚያስችል መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የ2018 ረቂቅ በጀት የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን እና የ10 ዓመቱን መሪ የልማት እቅድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የ8.9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚጠበቅም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።