
08/07/2025
በየአካባቢው የሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶችን ህብረተሠቡ ጠብቆና አልምቶ የመጠቀም ኃላፊነት እንዳለበት ተገለጸ።
ማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል ውሃ መሥኖና ማዕድን ልማት ቢሮ በሀዲያ ዞን ዱና ወረዳ በ130 ሚሊዮን ብር የገነበው ቀንቅቾ ዋገበታ የዉሃ ፕሮጀክት ርክክብ ተደርጓል።
ሆሳዕና፦01/11/2017 (ሀድያ ቴሌቪዥን)
በርክክብ ፕሮግራሙ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አሰተያየት የውሃ ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት በአካባቢው በዉሃ እጥረት ምክንያት ሲደርስ የነበረውን እንግልትና በንፁህ ውሃ እጦት የሚከሰተውን የጤና ችግር በመቅረፉ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በነዳጅ የሚሰራ በመሆኑ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ሲገጥም የውሃ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ ስጋታቸውን በማስቀመጥ ለዘላቂ መፍትሄ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀም እንዲቻል ትብብር እንዲደረግ ጠይቀው ፕሮጀክቱን ጠብቆ ለመጠቀም ቃል ገብተዋል።
የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የፐብሊክ ሰርቪስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ታምሬ ባደረጉት ንግግር የዉሃ ፕሮጀክቱ በማህበረሠቡ የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ የመለሰ ትልቅ ፕሮጀክት እንደሆነ ጠቁመዋል።
የልማት ፕሮጀክቱን ህብረተሠቡ ከመንግስት ተረክቦ በመንከባከብና በመጠበቅ አቆይቶ የመጠቀም ኃላፊነት አለበት በማለት የወረዳው አስተዳዳርም የበኩሉን እንደሚወጣ ገልፀው በልማቱ የተሣተፉትን ሁሉ አመስግነዋል።
የሀድያ ዞን የዉሃ መስኖና ማዕድን ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መለሰ ኃይሌ በበኩላቸው፤ የዉሃ ፕሮጀክቱ በክልል ደረጃ በከፍተኛ ትኩረት ሰፊ በጀት በመያዝ የተከናወነ መሆኑን አንስተው የልማት ተግባሩ 5 ቀበሌያት 40 ቦኖዎችን በመትከል 41ሺህ ህዝብ ንጹ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ አልቆ አገልግሎት መጀመር ብቻውን በቂ ባለመሆኑ አገልግሎቱን ለማስቀጠል በሚያስፈልገው ሁሉ መሣተፍና በኃለፊነት ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የማዕከላዊ ክልል ውሃ መስኖና ማዕድን ቢሮ ምክትል የመጠጥ ዉሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙላቱ ጡሞሮ እንደገለፁት የውሃ ፕሮጀክቱ በክልሉ 130 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የተከናወነ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የልማት ተግባሩ እስኪጠናቀቅና ከተመረቀም በኋላ በቂ ሙያዊ ክትትል እየተደረገ ቆይቶ ለርክብክብ ወቅት መድረሱን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን የአካባቢው ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን በማድረግ መጠቀም ያስፈልጋል በማለት ፕሮጀክቱን ከነዳጅ ወጪ ወደ ኤክትሪክ ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ክልሉ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
የዉሃ ፕሮጀክቱ ሰኔ 2016 ዓ/ም የክልሉ ርዕሰ መሥተዳደር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት መመረቁ ይታወሳል።
አድማሱ ወልዴ