
01/09/2025
የወለደችውን የሶስት ቀን ህጻን አባቱን ባለማወቋ ከነህይወቱ የአፈር ማዳበሪያ ኮምፖስት ውስጥ ከታ የገደለችው እናት በእስራት ተቀጣች
በምዕራብ ወለጋ ዞን አንድ አነስተኛ ቀበሌ ውስጥ ያደገችው ጠጂቱ ካሳ ወደ ጊቢ ከተማ በመምጣት በሰራተኝነት ተቀጥራ የተለያዩ ግለሰቦች ቤት ሰርታለች።በዚህም የብዙ ሰዎችን አመልና ጓዳ በደንብ ማወቅ ችላለች።
ግለሰቧ በመጨረሻ በመስተግዶ ስራ የተቀጠረችው ጊንቢ ከተማ ታዋቂ ሆቴል ሲሆን ከወጣቶች ጋር የመተዋወቅ እድል አግኝታለች።ከተዋወቀቻቸው ወጣቶች መካከል ከአንድ ሁለቱ ጋር የፍቅር ግኑኝነት መስርታለች። በዚህም ሂደት ላይ እያለች ለእርግዝና መጋለጧ የምዕራብ ወለጋ ዞን ፖሊስ ዋና መምርያ የኮሙኒኬሽን ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቹቹ ኢቱ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
እርግዝናው በፈጠረባት ተጽእኖ ስራ ለማቆም የተገደደች ሲሆን የተጸነሰው ልጅ አባት አለማወቋ ደግሞ የስሜት ውዝግብ ውስጥ ከቷታል።ይህ በእንዲ እንዳለ አብራቸው ከቆየቻቸው ወንዶች መካከል የእርግዝናዋን ሁኔታ ስትነግራቸው አንዱም የእርጎዝናውን ውጤት ተቀብሎ አባት ነኝ የሚል ያጣች በመሆኑ ጓደኞቿ ጋር ተጠግታ ወንድ ልጅ ትገላገላለች።
ከሶስት ቀን ቧኋላ ከአራስ ቤት ተነስታ ሀምሌ 22ቀን 2017 ዓ.ም ሰባት ሰዓት ላይ ለአፈር ማዳበርያ የተዘጋጀ ኮምፖስት ውስት አባቱን ያላወቀችውን ጨቅላ ልጅ ከነህይወቱ ከታው መመለሷ ተገልጿል ።ከአራት ቀን በኋላ ደግሞ የምትቀብርበትን ቦታ አዘጋጅታ ከማዳበሪያው ኮምፖስት ውስጥ ስታወጣ የተመለከቱ ነዎሪዎች ወዲያውኑ ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጉና በቁጥጥር ስር ያውሏታል።
ፖሊስም ወዲያው ምርመራውን በበቂ ማስረጃና የአስክሬን ምርመራ አጠናክሮ ለአቃቢ ህግ የላከ ሲሆን አቃቢ ህግም ከፖሊስ የቀረበውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ በወንጀል ሕግ ቁጥር 544 ህፃንን መግደል ወንጀል ክስ ይመሰርታል።በዓቃቢ ህግ የተመሰረተውን ክስ የተከታተለው የምዕራብ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠጂቱ ካሳ ጥፋተኛ መሆኗ በአቃቢ ህግ ማስረጃ በመረጋገጡ በአስራ ሶስት ዓመት እስራት እንድትቀጣ የወሠነባት መሆኑን የምዕራብ ወለጋ ዞን ፖሊስ ዋና መምርያ የኮሙኒኬሽን ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቹቹ ኢቱ ለብስራት ሬዲዮ ገልጸዋል ።