11/04/2025
የእለት ተእለት ኑሯችን ውስጥ ድንገት የሚመጡብን (መቼ እንደሚመጡ የማናውቃቸው) ነገሮች አሉ። ለምሳሌ:- ረሀብ መቼ እንደሚርበን አናውቀውም ፣ መቼ እንደሚጠማን ፣ ሽንት መቼ እንደሚመጣን ፣ እንቅልፍም መቼ እንደሚይዘን ፣ በሽታም መቼ እንደሚያመን ....ብዙ ብዙ ነገሮች መቼ እንደሚመጡ አናውቅም። ህይወታችን በህይወት መስተጋብራችን በየቀኑ በምናከናውናቸው ድርጊቶች ሰርፕራይዞቻቸው የተሞላ ነው በተለይ በተለይ ደግሞ በዋናነት #ሞት መቼ ደርሶብን እንደሚይዘን የማናውቀው ትልቁ ድንገታዊ እንግዳችን ነው።
ከላይ የጠቀስናቸው ድንገት የሚይዙን ነገሮች ሁሉ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ የምንችልባቸው ናቸው። ለረሀባችንም ፣ ለጥማችንም ፣ለእንቅልፋችንም ፣ ለበሽታም ለሌሎቹም ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንችላለን። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዱንያ ላይ ቀሪ የሆኑ የዱንያ ሀጃዎች መሆናቸው ክፋታቸው እና ዱብዳቸው ያን ያህል ነው።
ሞት ግን....ሞት ግን የኋለኛውን አለም የዘላለም ህይወትን ጉዳይ ማሰሪያ መቋጫ የተከረቸመ መዝጊያ በር ነው። ለዛም ነው ታላቁ ጌታችን አላህ ﷻ ሞት ደርሶ የዱንያ ቆይታችንን ከማገባደዳችን በፊት በቻልነው አቅም መዘጋጀት እንዳለብን የሚነግረን።
وَٱعْبُدْ رَبَّكَ حَتَّىٰ يَأْتِيَكَ ٱلْيَقِينُ
እውነቱም (ሞት) እስኪመጣህ ድረስ ጌታህን ተገዛ፡፡
(14 : 99)
كُلُّ نَفْسٍۢ ذَآئِقَةُ ٱلْمَوْتِ ۗ وَنَبْلُوكُم بِٱلشَّرِّ وَٱلْخَيْرِ فِتْنَةًۭ ۖ وَإِلَيْنَا تُرْجَعُونَ
ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፡፡ ለመፈተንም በክፉም በበጎም እንሞክራችኋለን፡፡ ወደኛም ትመለሳላችሁ፡፡
(20 : 35)
كُلُّ نَفْسٍۢ ذَآئِقَةُ ٱلْمَوْتِ ۗ وَإِنَّمَا تُوَفَّوْنَ أُجُورَكُمْ يَوْمَ ٱلْقِيَٰمَةِ ۖ فَمَن زُحْزِحَ عَنِ ٱلنَّارِ وَأُدْخِلَ ٱلْجَنَّةَ فَقَدْ فَازَ ۗ وَمَا ٱلْحَيَوٰةُ ٱلدُّنْيَآ إِلَّا مَتَٰعُ ٱلْغُرُورِ
ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፡፡ ምንዳዎቻችሁንም የምትሞሉት በትንሣኤ ቀን ብቻ ነው፡፡ ከእሳትም የተራቀና ገነትን የተገባ ሰው በእርግጥ ምኞቱን አገኘ፡፡ ቅርቢቱም ሕይወት የመታለያ መሳሪያ እንጅ ሌላ አይደለችም፡፡
(2 : 185)
እነዚህን እና ሌሎች ብዙ በዱንያ ህይወታችሁ ለፈጠርኳችሁ አላማ ኑሩ የሚሉ ብዙ የቁርአን አያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በዱንያ ግርግር በተዘናጋንበት ወቅት ድንገት ሞት ከያዘን መመለሻ ወደሌለው አለም ከተገባ ፀፀት እና ለቅሶ የጉም ላይ ስዕል ብቻ ነው።
حَتَّىٰٓ إِذَا جَآءَ أَحَدَهُمُ ٱلْمَوْتُ قَالَ رَبِّ ٱرْجِعُونِ
አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ እንዲህ ይላል «ጌታዬ ሆይ! (ወደ ምድረ ዓለም) መልሱኝ፡፡
(22 : 99)
وَلَيْسَتِ ٱلتَّوْبَةُ لِلَّذِينَ يَعْمَلُونَ ٱلسَّيِّـَٔاتِ حَتَّىٰٓ إِذَا حَضَرَ أَحَدَهُمُ ٱلْمَوْتُ قَالَ إِنِّى تُبْتُ ٱلْـَٰٔنَ وَلَا ٱلَّذِينَ يَمُوتُونَ وَهُمْ كُفَّارٌ ۚ أُو۟لَٰٓئِكَ أَعْتَدْنَا لَهُمْ عَذَابًا أَلِيمًۭا
ጸጸትንም መቀበል ለእነዚያ ኀጢአቶችን ለሚሠሩ አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ «እኔ አሁን ተጸጸትኩ» ለሚልና ለነዚያም እነርሱ ከሓዲዎች ኾነው ለሚሞቱ አይደለችም፡፡ እነዚያ ለእነሱ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡
(3 : 18)
አላህ በቀሪው የዱንያ ሀያታችን ለአኸራ ስንቅ የምንሰንቅ ታታሪ ባሮች መካከል አላህ ያድርገን።
ማሜ አላህ ይዘንልህ አላህ ቀብርህን ሰፋ አድርጎ በጀነት ኑር ያብራልህ። ከውዱ ነብይ ረሱል ﷺ በጀነተል ፊርደውስ ጎረቤት ያድርግህ።
✍️ Bilaluna
https://t.me/Xuqal