06/02/2026
የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ልጅ ሚካኤል (ፋፍ) “ከምን ልጀምር” የተሰኘ አዲስ አልበም ይፋ አደረገ
******************
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በተለይም በሂፕ ሆፕ (Hip Hop) ዘውግ ውስጥ የራሱን ደማቅ አሻራ እያሳረፈ የሚገኘው እና በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው ዝነኛው ድምፃዊ ልጅ ሚካኤል (ፋፍ)፣ 4ኛ የስቱዲዮ አልበሙን ለአድማጮች ለማቅረብ መዘጋጀቱን በይፋ አስታወቀ።
“ከምን ልጀምር” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ይህን አዲስ አልበም ለማዘጋጀት ስድስት ወራት የፈጀ ሲሆን፣ በውስጡ 15 አዳዲስ ሙዚቃዎችን አካቷል። አልበሙ በመጪው ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ለገበያ እንደሚውልም ተገልጿል።
ልጅ ሚካኤል አልበሙን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፥ “ይህን የሙዚቃ ስልት እኔ አልጀመርኩትም፤ ከታላላቆቼ በክብር የተቀበልኩትን በክብር ለህዝቡ አደርሳለሁ” በማለት በኢትዮጵያ በሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ዘውግ መሠረት ለጣሉ ሙዚቀኞች በክብር እውቅና ሰጥቷል።
በተጨማሪም ስልቱን ከኢትዮጵያ ባህል፣ ታሪክ እና ዜማ ጋር በማዋሃድ ለዘመኑ ትውልድ በሚመጥን መልኩ ለማቅረብ መሞከሩን ገልጾ፤ በዚህ መንገድ ለኢትዮጵያዊ ሂፕ ሆፕ ዘውግ የራሱን ልዩ አሻራ ማሳረፍ መቻሉን አስታውቋል።
“ከምን ልጀምር” የተሰኘው አልበም የልጅ ሚካኤል የሙዚቃ ጉዞን፣ የሕይወት ትምህርቶችን፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን እና የትውልድ ሀሳቦችን በሂፕ ሆፕ ቅርፅ ውስጥ በጥልቅ የሚያቀርብ እንደሆነም ተገልጿል።