
20/10/2024
የወባ በሽታ
በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል የወባ በሽታ ወረርሽኝ በሚመስል መልኩ በጣም ብዙ ሰው እየሞተ ነው። በወላይታ ብቻ በቀን ከ40-50 ሰው እየሞተ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ገልፀውልኛል። ይህ ቁጥር በቀን የሚሞተውን በትክክል ላይገልፅ ይችላል፣ምክንያቱም በሽታው ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ስለመጣ በተለይ በገጠራማው ክፍል በርካታ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። የህክምና ቁሳቁስ እና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በመፈጠሩ የሞት ቁጥሩ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በስልጤ፣በከምባታ፣ በጉራጌ ዞኖች እንዲሁም በምስራቅ ወለጋ እና ዙርያው ወረርሽኙ ተባብሷል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ በበኩሉ ከ1.2ሚሊዮን በላይ አጎበር ለማሰራጨት እየሰራሁ ነው ብሏል።
በአንድ ሳምንት ብቻ ከ51 ሺህ በላይ የወባ ህሙማን ቁጥር ተመዝግቧል " - የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
በአማራ ክልል በአንድ ሳምንት ብቻ ከ51 ሺህ 650 በላይ የወባ ህሙማን ቁጥር መመዝቡን የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
በክልሉ 40 ወረዳዎች 72 በመቶ የሚሆነው የወባ ስርጭት እንደሚሸፍኑም የኢንስቲትዩቱ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር የገለፁ ሲሆን የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አስረድተዋል።
የወባ በሽታ ስርጭት በክልሉ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ የገለፁት አስተባባሪው የ2017 በጀት ዓመት በባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 65.8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።