
14/07/2025
የደበበ እስጢፋኖስ ከዲቁና እስከ ቅስና ያለው
ስልጣነ ክህነት መሻሩን ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል አስታወቁ ።
==================================
ሐምሌ7ቀን 2017 ዓ.ም
++++++++++++++
የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ
አቡነ ፋኑኤል ሐምሌ 7ቀን 2017 ዓ/ም በቁጥር ሀ/ስ/053/17 በጻፉት ደብዳቤ የደበበ እስጢፋኖስን ከዲቁና እስከ ቅስና ያላቸውን ሥልጣነ ክህነት መሻራቸውን አስታወቁ።
ብፁዕነታቸው በደብዳቤያቸው እንደገለጹት ሰኔ 23,2017 ዓ.ም በቁጥር ሀ/ስ/050/17 በተጻፈ ደብዳቤ ደበበ እስጢፋኖስ ክብረ ክህነትን በሚያጎድፍ ድርጊት ስለተጠረጠሩ ጉዳዩ እስኪጣራ እንዲሁም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን የዘረመል (DNA) ምርመራ አድርገው ነገሩ እስኪረጋገጥ ድረስ ስልጣነ ክህነታቸው ቀደም ሲል ተይዞ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ደበበ እስጢፋኖስ የእግድ ደብዳቤውን ወደ ጎን በመተው በንቀትና በድፍረት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጥሰዋል።
ያሉት ብፁዕነታቸው በፍትሀ ነገሥት አንቀጽ 6 ቁ.228”ቄስ ወይም ዲያቆን ኤጴስ ቆጶሱን ቢንቀው ብቻውን ቤተ መቅደስ ቢሰራ እርሱ ከማዕረጉ ይሻር ተከታዮቹም ይሻሩ በሚለው ድንጋጌ እና ” በፍት.አን.6 ቁ.227”በታወቀች ኃጢአት በእርግጥ የተሻረ ቄስ ወይም ዲያቆን ቢኖር ከዚህም በኋላ ቀድሞ ሳይሻር በሰሞኑ ወራት ይሠራው የነበረውን የአገልግሎት ሥራ ተደፋፍሮ ቢሠራ ከቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ ይለይ ሥራውንም እያወቀ ከርሱ ጋር አንድ የሆነ ሁሉ ይሻር” በሚለው ሕግ መሠረት ለሕግ ተገዢ ባለመሆናቸው እንዲሁም ክህነታቸው መያዙን እያወቁ በዕለተ ሰንበት ሰኔ 29 ቀን እንዲሁም ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም በድፍረትና በማን አለብኝነት ቀድሰው በማቁረብ ቀኖና ቤተክርስቲያንን መሻራቸውን ብፁዕነታቸው በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።
ስለዚህ ከዲቁና እስከ ቅስና ያላቸው ክህነት የተሻረ መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው ከደበበ እስጢፋኖስ ጋር አብሮ የሚቀድስ ዲያቆንም ሆነ ቄስ በቀኖናው መሠረት ከክህነቱ የሚሻር መሆኑን ገልጸው ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ክህነቱ ከተሻረ ጋር ሕብረት ካደረጉ የሚወገዙና ከምእመናን አንድነት የሚለዩ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን።ብለዋል።
አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትም ይህንን ቀኖናዊ ውሳኔ
አክብረው እንዲሰሩ በጥብቅ እናሳሰባለን። በማለት የገለጹት ብፁዕነታቸው የደብረ ቁስቋም ቅ/ማርያም አስተዳደር፣ ካህናትና ምእመናን ስለ ቀጣዩ የቤተክርስቲያኑ አገልግሎት ምክክር ለማድረግ ወደ ሀገረ ስብከቱ መምጣት እንደሚኖርባቸው በዚሁ ደብዳቤ በግልባጭ የታዘዙ መሆኑን እናሳውቃለን።
በማለት በጥብቅ አስታውቀዋል።
ዲ/ን ይሁን ዘደብረ ገነት@topfans