
17/10/2022
በትግራይ ክልል ሽረ ከተማ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት አንድ የረድዔት ሰራተኛው መገደላቸውን ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ቡድን (ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ) ገለጸ።
ተቋሙ በዚህ የአየር ጥቃት የረድዔትሰራተኛውን ጨምሮ ሶስት ሰዎች መገደላቸውንም ቅዳሜ ጥቅምት 5፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የጤናና የስነ ምግብ ቡድን አባል የሆኑት የረድዔት ሰራተኛው ለሴቶች እና ህጻናት እርዳታ እያቀረቡ ባለበት ወቅት በተፈጸመ ጥቃት ከቆሰሉ በኋላ ህይወታቸው አርብ ጥቅምት 4፣ 2015 ዓ.ም እለት ማለፉን መግለጫው አትቷል።
በዚህ ጥቃት ሌላ የአይአርሲ የረድዔት ሰራተኛ የቆሰሉ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉና እንደቆሰሉ መግለጫው አክሏል።
ተቋሙ “የእርዳታ ሰራተኞች እና ሰላማዊ ዜጎች በፍፁም ኢላማ መሆን የለባቸውም” ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሽረ ከተማ ላይ ተፈጸመ በተባለው የአየር ጥቃት ላይ ምንም አይነት አስተያየት ባይሰጥም ከዚህ ቀደም ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እንደማያደርግ መግለጹ ይታወሳል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ባሉባት ሽረና አካባቢው ባሉ በርካታ ግንባሮች ጦርነቱ እየተጠናከረ መምጣቱንም ተከትሎ አለም አቀፍ ተቋማት ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
የትግራይ ኃይሎች ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ጦርና የኤርትራ ጦር በከተማዋ እና አካባቢው የከባድ መሳሪያ ድብደባና የአየር ጥቃት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ከሰዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ሰላማዊ ዜጎች ኢላማ መደረጋቸውን አውግዟል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦረል “በሽረ የቀጠለው ጦርነት እንዲሁም ሰላማዊ ነዋሪዎች ኢላማ የመደረጋቸው ሪፖርት አስደንጋጭ ነው” ብለዋል ።
"እውነተኛ የሰላም ጥረቶች ወታደራዊ ጥቃቶች ወይም ትንኮሳዎቸ እንዳልሆኑ" በገለጹበት የትዊተር መልዕክታቸው "አለም አቀፉን ህግ ማክበር የሁሉም ግዴታ ነው" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጦርነቱ መባባሱን በማስመልከት የተፈጠረባቸው "ከባድ ስጋት" ከገለጹ በኋላ ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
"በሽረ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት የፈጸሙት ሰላማዊ ሰዎችን ያልለየ ጥቃት አሳሳቢ ነው" በማለት የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ኃላፊ ሰማንታ ፓወር ተናግረዋል።
ሙሉውን ለማንብበ፦https://bbc.in/3eyNrfv