Visionary Ethiopian

  • Home
  • Visionary Ethiopian

Visionary Ethiopian እውነትን በጋራ የምንሰብክበት ኢትዮጵያዊነትን የምናቀነቅንበት መድረክ ነው። እንደ ንስር እየተመኘን እንደ ዶሮ እንዳንኖር ያተጋል። ያነቃል።

03/02/2023

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ
***********,,,*******
ቤተክርስቲያን ለልጆቿ ከፊታችን ባለው የነነዌ ጾም እየደረሰባት ላለው እና በአገራችን ኢትዮጵያ እንዲሁም በሕዝቡ እና በአገልጋዮቿ ላይ ስለሚደርሰው መከራ እና ሰቆቃ ሁሉ በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን የነነዌ ሕዝቦ ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ እግዚአብሔርን እንደለመኑት ልጇቿም ጥቁር ለብሰው ሱባኤውን እንዲያሳልፉ ጥሪዋን አቅርባለች።

እኛም ልጆቿ የቤተክርስቲያንን ጥሪ ተቀብለን በነዚህ ሶስት ቀና አበዝተን በመጾም እና በመጸለይ እግዚአብሔር ጥያቄያችንን እንዲመልስልን፣ አገራችንን ጽኑ ሠላም እንዲያደርግልን፣ ሕዝቦቿን ዘር ሃይማኖት ብሔር ሳይለይ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ እንዲጠብቅልን፣ አማጽያንን ወደ ልባቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግልን፣ ወዘተ በቤተክርስቲያን በመገኘት ከእግዚአብሔር ጋር እንድንነጋገር እግዚአብሔር የሚለንን እንድንሰማ ይሁን።

አንዳንዶች በይሉኝታ ተመሳስለው ለማደር ፍርሐትም አርዷቸው ላያደርጉ ይችሎ ይሆናል፤ ነገር ግን አብዛኞች እንደሚያደርጉት የቤተክርስቲያንን ጥሪም እንደሚሰሙ ተስፋ አደርጋለሁ።

እግዚአብሔርን በጸሎት መለመን የአንዲት እምነት ተግባር ብቻ አይደለምና እግዚአብሔርን የምታመልኩ እግዚአብሔር እንደሚሰራ የምታምኑ የእግዚአብሔርን ሥራ ታዩ ዘንድ በጾም በጸሎት አገር ላይ የተቃጣው ነገር እንዲመለስ፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እያንዣበበ ያለው ነገር እንዲረግብ ሁላችንም አብረን በመቆም ጥቁር ለብሰን እንጹም እንጸልይ።

ከጾም እና ከጸሎት በቀር ማሸነፍ አይቻልም።

ይቆየን።

03/02/2023

i was created to accomplish something specific that no one else can accomplish.

ሌሎች እንዲያደርጉልህ ሌሎች ድምጻቸውን እንዲያሰሙልህ ሌሎች ያንተን ድርሻ እንዲወጡልህ የምታስብና የምትተኛ ከሆነ ተሳስተሃል። እንደ አሣማው ትበላ እንደሆነ እንጂ ምንም አይለወጥም።

ተነስና የተፈጠርክለትን ዓላማ ኑር።

Vision is the primary motivator of human action , and , therefore , everything we do should be because of the vision God has placed in our hearts.

ወዳጄ ለምን የተፈጠርክ ይመስልሃል? አንዲሁኮ ለኮታ አልተፈጠርክም። የተፈጠርከው እግዚአብሔር በአንተ ላይ ሊያከናውነው በፈለገው ዓላማ ምክንያት ነው።

Vision influence the way you conduct your entire life, ...

Without vision , you have no values to guide your living. Life has no meaning. Activity has no meaning. Time has no purpose. Resources has no application.

Vision is the juice of life. It is the prerequisite for passion and the source of persistence.

When you have vision, you know how to stay in the race and complete.

ሁላችንም ፊሽካ የተነፋበት የሕይወት ሩጫ ውስጥ ነን ሩጫው መች እንደሚጠናቀቅ አይታወቅም። የደከሙ ያቋርጣሉ፣ ተስፋ የቆረጡ ያቋርጣሉ፣ ዓላማ የሌላቸው ያቋርጣሉ፣ ግብ ያላስቀመጡ ያቋርጣሉ፣ ... አንተ ግን በሩጫው ውስጥ የተገኘኽበትን ዓላማ ስለምታውቅ አታቋርጥም።

የሩጫውን ሜዳ ሕግ ታውቃለህ፣ በሩጫው ለማሸነፍ የምትሄድበትን መንገድ ታወቃለህ፣ ተግዳሮቶቹን ጠንቀቅህ ታውቃለህ፣ ሩቅ እንደምትጓዝ ታወቃለህ፣ አሸናፊ ስትሆን የምታጠልቀውን ሜዳልያ 🏅🏆 የምትጨብጠውን ዋንጫ ታውቃለህ። ለማሸነፍ እንጂ ለተሳትፎ የሩጫው ሜዳ እንዳልገባህ ታውቃለህ።

ሩጥ ...

ሩጫውን ስታጠናቀቅ የሕይወት አክሊል ይጠበቅሃልና።

ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ፤ አበቃሁ ።

ይቆየን።

31/01/2023

ጌታ ሆይ ልንጠፋ ነው

የቅዱሳን ሐዋርያት ድምጽ ነው፤ አጠገባቸው ካለ ጌታ ይልቅ መምጫው ያልታወቀን ማዕበል አመኑ። ልንጠፋ ነው ብለው ተጨነቁ።

የእምነትህ ልክ በፍርሃትህ መጠን ይለካል። ከፈራህ አታምንም ካመንክ አትፈራም።

ሰሞኑን በተነሳ ማዕበል የተሰማን ፍርሃት ያለማመናችንን ልክ ያሳያል። የሲኦል ደጆች አይችሏትም የተባለላትን ቤተክርስቲያን ጥቂቶች ለሥርዓቱ የማይገዙና በሥርአት የማይጓዙ ትንሽ ማዕበል ሥላስነሱ ቤተክርስቲያን ልትፈርስ ነው ብለን የፈራን። ታንኳይቱ ቤተክርስቲያን ላይ ያለን ጌታ አለማወቅ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዕበሉን ጸጥ እንደሚያደርግ አለማመን ነው።

የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሰው ዓይን ያላየውን/ያየውን የሰው ጆሮ ያልሰማውን/የሰማውን ማዕበል ስትወጣው ነው የኖረችው።

የትኛውም ችግር ያለመፍትሔ አልተፈጠረም። ጌታችን መፍትሔ አለው። ሐዋርያቱ ማዕበሉ ሲያናውጻቸው ጌታን የተኛ እና የተዋቸው መስሏቸው ቀሰቀሱት ልንጠፋ ነው አሉት፤ አድነን ብለውም ለመኑት።

ማዕበሉን ጸጥ አደረገው።

አሁንም ማዕበሉን ጸጥ ያደርገው ዘንድ ይቻለዋል።

ብዙዎች አገር ልትበተን፣ ቤተክርስቲያን ልትጠፋ የሚመስላቸው ጌታን የማያውቁት እውቀት የጎደላቸው ብዙ ናቸው።

የማዕበሉ መናወጽ የሐዋርያቱን እምነት ለማጽናት እንጂ ታንኳይቷን ለመገልበጥ አልነበረም። የዛሬይቱም ቤተክርስቲያን መናወጽ የሚያምነውን ከማያምነው፣ የጸናውን ካልጸናው፣ እያንዳንዳችን ከወዴት እንደቆምን ለመለየት እንጂ ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ አይደለም።

ብዙዎች ከቅንነት በመነሳት "ቀኖና/ስርአት" ነው የተጣሰው የሚሉ አሉ፤ የሆነውን አለማወቅ ነው። አገራት እየፈረሱ ያሉት በስርአት አልበኞች መሆኑን ካለመረዳት ነው። "ወገኔ እውቀት ከማጣት የተነሳ ጠፋ" እንዲል መጽሐፍ ከእውቀት የራቅን እና በደቦ የምንመራ ስለሆንን አይፈረድብንም።

ሁሉ በስርአትና በደንብ ሲሆን መልካም ነው። ቀኖና ሥርአት የናደ ዶግማ እነደማይጥስ እንደምን እርግጠኛ እንሆናለን። በእንቁላል ስርቆት የጀመሩኮ ናቸው አገርን ለማሻሻጥ የሚያስማሙት።

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና አንዱ የቆመችበት አምድ/ምሰሶ ነው። ቤተክርስቲያኒቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ ቀኖናን ያውቃል። በደጅ ሲያልፉ የሰሙ ሊያውቁት አይችሉም።

ለማስታወስ ያህል ቀኖና የሚሻር እና የሚሻሻል ሲሆን ይህንንም ማድረግ የሚችሉት ሊቃነጳጳሳት በሲኖዶስ ብቻ ነው። ማንም ተነስቶ እንደ እድር ወይም እቁብ መተዳደሪያ አይሽረውም/አያሻሽለውም።

እድር እና እቁብም ስረአት አላቸው ምልአተ ጉባኤው በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት መሟላት አለበትና።
እንደ ምዕመን ከእኛ የሚጠበቁው መጸለይ ብቻ ነው።

ይቆየን

ደረሰ ረታ
23/5/2015ዓ.ም.

እንኳን አደረሳችሁ።
09/01/2023

እንኳን አደረሳችሁ።

28/12/2022

"ከማያውቁት መልዐክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል" ይህ ለውጥን ያለመፈለጋችን ምልክት እና ለውጥን የምንከላከልበት የስንፍና ጋሻችን ነው።

ለመሆኑ በምን መስፈርት ነው ከመልዐክ ሰይጣን የሚሻለው? የት ነው ሰይጣንን እንዲህ የለመድነው? እውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መልዐክን አያውቅም?

ከለመድነው ለመውጣት ያለመፈለግ ድካማችን እዚህ ድረስ ብርታት አግኝቷል ማለት ነው። ወይስ ምቹ ከባቢያችንን ለማስከበር ላለመልቀቅ የምናደርገው ጥረት ነው?

ሰዎች የለመዱትን ሥፍራ የሚመርጡት ስለሚመች ሳይሆን አዲስ ነገር ለመልመድ ስለምንፈራ ነው።

"ረግረግ የለመደች እንቁራሪት ባህር ያለ አይመስላትም" ይባላል፤ ሰዎችም እንዲሁ ከሚኖሩበት ሕይወት የተሻለ ሕይወት ያለ አይመስላቸውምና ለውጥ ይፈራሉ።

ሰዎች ለውጥን የሚጠሉት "ውድቀትን" ስለሚፈሩ ነው፤ በነገራችን ላይ ውድቀት የሕይወት መጨረሻ አይደለም የስኬት መጀመሪያ እንጂ። ልብ ያላልነው ነገር ማንኛውም ሕይወት ውስጥ ውድቀት እንዳለ ነው። ብልህ ሰው የስኬት ጎዳና ላይ እያለ እንኳን ከወደቀበት እየተነሳ ከግቡ ይደርሳል። ያሸንፋል።

ታላላቅ ሰዎች ሕይወታቸው የተመሰረተው ውድቀት ላይ ነው፤ የዘር ፍሬም ወድቆ ነው ብዙ የሚያፈራው። ከብዙዎች ሕይወት የምንማረው ከውድቀት በኋላ መነሳት፣ ከመነሳት በኋላ ስኬት እንዳለ ነው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን የአገራችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ለዚህ እንደምሳሌ ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ናቸው።

የስኬት ምንጩ "ለውጥ" ነው፤ ለውጥ ከትንንሽ ነው የሚጀምረው። ለማድረግ "አይሆንም/አይቻልም/አይሳካም" የሚለውን ደካማ አስተሳሰብ ከመጥላት ይጀምራል።

ለእኔ ከ"ማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል" የሚለውን ደካማ አስተሳሰብ በመቃረን እጀምራለሁ።

ለኔ መልአኩ ይሻለኛል
ለኔ ሰይጣን ምርጫዬ አይደለም
የሰይጣንን ሥራ እቃወመዋለሁ
ከሰይጣን ጋር ሕብረት የለኝም

ኢትዮጵያውያን እውነት የምንኖረው ሕይወት ይመቻል? አሁን የምናገኘው ገቢ እና ወርሐዊ ወጪያችን ይመጣጠናል?
የምንመርጠውን ኑሮ ነው የምንኖረው?
አሁን ካለኝ ነገር የተሻለ ምርጫ የለም?

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አሁን የምንኖረውን ኑሮ እየኖርን ያለነው ተፈርዶብን ሳይሆን ወይም የሚመጥነን ኑሮ ሆኖ ሳይሆን ለውጥ ስለምንፈራ ነው።

ለዚህ ነው በአባባላችን ከመልአክ ይልቅ ሰይጣን ስንመርጥ የኖርነው። " የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዘንድ ይኖራል ያድናቸውማል።" እንዲል ዛሬ በክብር የምትነግ ገናናው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሆይ እንድለወጥ አበርታኝ።

ሰልስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣህ፣ በእምነት ያጸናህ እኔንም በመንፈሳዊ ሕይወቴ አጽናኝ ካለሁበት የማይመች ሕይወት አውጣኝ በለውጥ ጎዳና ምራኝ።

አገሬን ሕዝቧን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከክፉ አድራጊዎች ጠብቅልኝ።

ማዳኑን የምታምኑ ቅዱስ ገብርኤል ከተቃጣ መቅሰፍት ያድነን። በተሰጠው የማማለድ ስልጣን በምልጃው ይራዳን።

ሕዝቤ ሆይ ከአጉል ልማድ ተላቀቅ ሰይጣን ከመልአክ አይሻልምና።

እንኳን ለገናናው መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በዐል አደረሰን አደረሳችሁ።

ደረሰ ረታ
19/4/2015ዓ.ም

21/12/2022

የዘር ፖለቲካ ምን ዓይነት ችግር እንዳለው ከቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ከተማርነው የላቀውን ላለፉት ሶስትና አራት ዓመት ከአገራችን ፖለቲካ ብዙ ተምረናል።

ላላደጉ አገራት ይልቁንም ደግሞ ለኛ አይነት ማህበረሰብ ጥላቻን ካልሆነ በቀር የሚያተርፈው ነገር እንደሌለ የዛሬው አዳሬ አመላክቶኛል።
በለቅሶ ምክንያት ከአዲስ አበባ ውጪ ነበር የነበርኩት።

የለቅሶ ቤት አዳር እንደሚታወቀው ድንኳን ውስጥ አለበለዚያ በየመንደሩ ዘመድ ቤት ተፈልጎ ይታደራል። አቅሙ ወይም ፍላጎቱ ኖሮሽ ሆቴል ማደር ቅንጦት አለበለዚያም በሕገ ለቅሶ ቤት የተከለከለ ነው።

እንደዚህ ዓይነት ቦታ ላይ ጠላትሽ የቅርብ ሰውሽ ነው፤ እንድታርፊ አይፈቅዱልሽም። ተመሳሳይ ነገር ገጥሞኝ ብቻዬን ሴቶች የበዙበት ቤት ተነጥፎልኝ አደርኩ።

አደርኩ የሚለውን ቃል የሚተካልኝ ተለዋጭ ቃል ስላጣሁ እንጂ እንቅልፍ በዓይኔ አልዞረሞ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በለቅሶው ዋዜማ አልተኛሁም። እውነት ለመናገር የናፈቀኝ እንቅልፍ ሳይሆን ጸጥታ ነበረ። ሠላም አጣሁ።

ወሬ ትጣላላችሁ ከነአባባሉ "ሴት በዛ ..." ነው የሚባለው። መቼስ እኔን የናፈቀኝ እረፍት እና እንቅልፍ እነሱንም (ሴቶቹን) ይናፍቃቸዋል። ነገር ግን አስቀድሞ እንደ መገለጫ አልያም እንደ ትንቢት የተነገረላቸው ቃል አለና ለወሬው ጊዜ አልበቃቸውም።

ወሬ ትጣላላችሁ ወሬ አይነት አለው፤ ጥላቻ እና የጥላቻ ንግግር መንግሥት ቁጥጥሩን ጠበቅ አድርጎ ባይሰራበትም አስፈላጊነቱ ምንም አያጠያይቅም። አዳሩን ሙሉ አንድን ብሔር በጥላቻ ሲያብጠለጥሉት አመሹ። ዘጠኝ ሰአት ሲያልፍ ደግሞ እንደገና ተነሱ።

ችግሩ የምሽቴ ጉዳይ አይደለም እንደ አገር ወደኋላ ያስቀረን፣ እንዳንተማመን ያደረገን፣ እርስ በእርስ ያባላን፣ ትፈርሳለች አትፈርስም የሚል ውርርድ ውስጥ ያስገባን ምክንያቱ የዘር ፖለቲካ ነው።

በዚህ ልክ ሴት ልጅን ለዚያውም ምራቋን ዋጥ ያደረገች ዕድሜዋ አርባን የተሻገረ እንዴት በፖለቲካ ለዚያውም በጥላቻ እንቅልፏን ታጣለች? የእናት ሆድ ሲባል የቀድሞ እናቶቻችን ሆድ ትዝታ ውስጤ ቀርቶ ተታልያለሁ። እነዛ እንስፍስፍ እናቶች፣ እነዚያ ዘር እና ብሔር የማያውቁ እናቶች፣ እነዚያ ለሰፈር ሕጻናት በሙሉ ጡታቸውን አጥብተው ያሳደጉ እናቶች ምትክ ጥላቻ ርዕሳቸው የሆነ እናቶች ኢትዮጵያ አበቀለች።

"የተማረ ይግደለኝ" እንዳላለ የኢትዮጵያ ሕዝብ በ"ተማረ" እየሞተ ነው። እነዚህ ሴቶች ከሞላጎደል የተማሩ 'ፕሮፌሽናል' ናቸው። ነገር ግን አንደበታቸው ያላዋቂ ነው። ጥላቻ የቆሸሸ አዕምሮ ጥራጊ ነው።

እነዚህ የለቅሶ ቤት ሴቶች የአገራችን ነጸብራቅ ናቸው ጥላቻን ምን ያህል ቤተኛ ሆነን እየኖርን እንደሆነ ማሳያ ነው። የሰው ልጅ ታፍኖ በዚህ ልክ አንዱ ሌላኛውን ከጠላ በልቡ ጥላቻ ከሞላ ቢመቻችለት ምን ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም።

ለነገሩ በሴቶች ላይ አጠነጠንኩ እንጂ ጥላቻ ጾታን መሰረት አላደረገም። ዕድሜስ ቢባል ማንን ከለከለ? ልጆቻችን ከትምህርት ይልቅ አንደበታቸውን የፈቱት በፖለቲካ ከሆነ ሰንብቷል። የኢትዮጵያ ተተኪ መንግሥታት የትምህርት ነገር አልሳካ ቢላቸው የሕጻናቱን ጭንቅላት በዘር ፖለቲካ ለመንደፍ ፖሊሲ መቅረጽ አላስፈለጋቸውም። አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ፖለቲካ ነውና።

ፖለቲካችን የት ያደርሰን ይሆን? ሁሌም የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው። ይህንን ጥያቄ ሳልመልስ ጥላቻ ሌላው ሥጋ ለብሶ በሰው ቁመት መጥቷል። እስከዛሬ በፖለቲካ ሰበብ አገራችን ላይ የተቃጣው መቅሰፍት ያላጠፋፋን ሕዝባችን ውስጥ የነበረው ፍቅር ነበረ። ነገር ግን አሁን ያለው ስሩን እየሰደደ የመጣው ጥላቻ በምን ይቋጭ ይሆን?

ከሰሞኑ በእምነት ተቋማት መካከል የአገሪቱን ሰማይ አየር የቀየረው አንዱ የጥላቻ ንግግር አካል እንጂ የዶክትሪን ልዩነት አይመስለኝም። ፖለቲካ ውጤቱ ትልልቆችን መገርሰስ እስኪመስል ድረስ ላለፉት ሶስት እና አራት አስር አመታት በአገራችን ተከብረው የቆዩትን የእምነት ተቋማት እስልምናን እና ክርስትናን ፖለቲካው ደፍሯቸዋል። ተሰሚነት እና ተቀባይነት አሳጥቷቸዋል። ሸምጋይ እና አስታራቂ ሽማግሌዎች ተንቀዋል። ቱባ ባህል ያለው የገዳ ሥርአት አባቶች ተገድለዋል። ካህናት እና ሼሆች ተገድለዋል።

ቤተእምነቶች ፈርሰው ተቃጥለዋል። የየቤተእምነቱ ተከታዮች በየቦታው ተሸማቀው የአምልኮ ነጻነት እና የማምለኪያ ቦታ አጥተዋል/ተነጥቀዋል። ይህ ፍሬ የጥላቻ ውጤት ነው።

እና ወደየት እየሄድን ነው?

በአንድ አጋጣሚ በአንድ ቤት ውስጥ የተሰባሰበ ኢትዮጵያዊ መልኩ ይህ ከሆነ ሰፊዋ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች?

ይኸው 11:00 ሲሆን ሁሉም እንቅልፍ አሸንፎታል። እኔም ትዝብቴን ለእናንተ ሰደድኩኝ። የኢትዮጵያን ጥፋት ከሚያሳየን ፈጣሪ ሁላችንንም በእንቅልፍ ያሸንፈን።

13/12/2022

የሰማይ ቤት ደላሎች
ክፍል ፪
ደረሰ ረታ
4/4/2015ዓ.ም
____________~
_____________+-
የሰማይ ቤት ደላሎች ሁሉም መነሻቸው ከውስጥም ይሁን ከውጪ መዳረሻቸው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነች። በዚህ ጉዳይ ላይ ዙሪያ ጥምጥም መሄድ አያስፈልግምና። ተከታዮቻቸውም ቢሆኑ የማያውቋት ልጅነታቸውንም በአግባቡ ያልተወጡ የጠፉ ልጆቿ ናቸው።

ለምንድነው ደላላ የበዛው? ለምንድነው አፍአዊ እና አካላዊ ጥቃቶች የተበራከቱት? ለምንድነው ከልካይ የታጣው? ለምንድነው ራሷን የማትከላከለው? ምዕመኑስ ከንፈር ከመምጠጥ እና ተመሳስሎ ከመኖር የዘለለ ማድረግ የተሳነው? ለምንድነው ሁሉም ፊቱን ወደዚች ቤተክርስቲያን ከዘመን ዘመን በተሻገረ መልኩ ያዞረው?

ለምን? መፍትሔ አይሆንም።

ችግሩን ማወቅ የመፍትሔው አንድ አካል እንደሆነ ጸሐፊው ልብ ይለዋል፤ ነገር ግን ዘለዓለም ዓለም ዙሪያውን ስንዞር መኖር የለብንም።

ችግሩ መዋቅራዊ ነው። መፍትሔውም መዋቅራዊ መሆን አለበት።

በቡድኖች እና በጥቂት ግለሰቦች የሚደረግ አይደለም።

ከፊት የሚታዮት ከኋላቸው ጡንቻቸው የፈረጠመ ኃይሎች ነጸብራቆች ናቸው። ዘመን ያስቆጠረ መዋቅር፣ አገርን ማንቀሳቀስ የሚችል በጀት፣ ምድራዊያንን ሊያንቀጠቅጥ የሚችል ጉልበት፣ የውስጥ እና የውጪ ኃይሎች ('መንግሥትን' ጨምሮ) ጥምረት፣ ወዘተ አለ።

አንዱ ተነስቶ ማርያም አታማልድም ፣ ታቦት ጣኦት ነው(ሳጥን ነው)፣ ኢየሱስ አማላጅ ነው፣ ቅዱሳን እንደእኛው ሰው ናቸው፣ ወዘተ የሚለውን ብቻ እያየን ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ፣ ... ብቻ ደፋ ቀና በማለት የምንወሰን ከሆነ ተሳስተናል።

ዓላማቸው ምዕመናንን ማስኮብለል፣ ቤተክርስቲያንን ማቃጠል፣ ስርአተ ቤተክርስቲያንን መናድ፣ ወዘተ ብቻ መስሎን ከሆነ ተሳስተናል።

የሰማይ ቤት ደላሎች እንደ እንግዳ ደራሾች ዛሬ የመጡ አይደሉም። ትናንት ነበሩ ዛሬ አሉ ነገም ይኖራሉ፤ ደላሎች ጠፍተው አያውቁምና። ቤተክርስቲያንን ግን ሊያነዋውጿት አልቻሉም። አቃጥለዋታል፣ ምዕመናኖቿን አርደዋል፣ ገለዋል፣ አፈናቅለዋል፣ የአምልኮ መብታቸውን ነፍገዋል፣ መጠጊያ አሳጥተዋታል፣ ... አለሁልሽ ባይ መከታ የመንግሥት ተቋምም ሆነ ቤተክህነት የላትም። ድንበሯ ቅጥሯ ተደፍሯል፣ አማሳኞች ወረዋታል፣ በጠላት መዋቅሩ ልክ ከፋፍለዋታል፣ ... ግን አለች። ባሰቧት ልክ አልፈረሰችም።

ከውስጥ ያሉ ልጇቿም "የሰማይ ደጆች አይችሏትም" እያለ የሚመጻደቅ ብዙ ልጆች አፍርታለች፤ አዎ አይችሏትም። ነገር ግን የሲኦል ደጆች አይችሏትም እና በየዘመኑ የተነሳ ሁሉ እንዲነቀንቃት መተው የለብንም።

አላማው "ቤተክርቲያናዊ" ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሕዝብ ብዛቷ፣ በመዋቅሯ፣ በዶግማ እና ቀኖናዋ ወዘተ ሁለት ሺ ዘመን ያስቆጠረች በቀላሉ የምትነቀነቅ ስላለሆነች እርሷ ላይ ጠንክሮ መስራት አገርንም ጭምር ለማፍረስ ቀላል እንደሆነ ይገመታል። ዛሬ ድረስ የአገርን አንድነት አስጠብቃ ኖራለችና ወደፊትም ይህንኑ የማስቀጠል አቅም እና ሕልም አላት። ስለዚህ አገርን ለማፍረስ የሚነሳ የውስጥ ኃይል ብቻ ሊኖር አይችልም። (የውስጥ ኃይል ብቻ የሚለው ይሰመርልኝ) ከውጪ በትልቅ አጀንዳ እና በጀት የሚደግፍ ከሌለ በቀር በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም። ለዚህም ነው ኮሽ ባለ ቁጥር መንግሥት "የውጪ ኃይሎች እጅ አለበት" የሚለው። (ካመነበት ይህቺን አገር የሆነች ተቋም ከጠላቶቿ መጠበቅ ነበረበት)

ላለፉት ሰላሳ እና አርባ አመት አውሮፓውያን እና አሜሪካ ሌሎችም አህጉሮች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው አምልኮ እየቀነሰ ሲመጣ ሰይጣናዊ አምልኳቸው እየተመነደገ ሲመጣ (ተግባራቸው ሳይቀር ሰይጣናዊ በሆነበት ዘመን) ለምን አፍሪካ ይልቁንም ኢትዮጵያ "ጌታን እንድትቀበል) የሙጥኝ ተባለ? ለምን የትኩረት አቅጣጫቸው ወደራሳቸው እና ወደ ያላመነው ክፍለ ዓለም አልሆነም? አስቀድማ የኦሪትን ቀጥሎም የአዲስ ኪዳኑን ክርስትና በጃንደረባው አማካይነት የተበቀለች ኢትዮጵያን የሙጥኝ ማለት የጤና ነውን?

የሰማይ ቤት ደላሎቹ በአንድ ጊዜ ከአነቃቂ ንግግሮች ወደ ወንጌል ሰባኪነት/አስመላኪነት የተሻገሩት በጤና ነው? በእውነተኛ እና መሠረት ባለው አስተምህሮ ላይ ያልተመሰረተ የወንጌል አገልግሎት ሕብረተሰቡን መጋታቸው አግባብነቱ እስከምን ድረስ ነው? መንግሥት በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ሕጉ ቢከለክለውም ቅሉ ዝምታው አግባብ ነውን? የወንጌል አማኞች ሕብረትስ ይኽንን ጉዳይ እንዴት ይመለከተዋል?

ለምሳሌ እናንሳ አንድ ወንድማችን ከሰሞኑ በአደባባይ የተናገረውን በአደባባይ ይቅርታ ጠየቀ፥ እንዲህ የሚል ነበረ፦ " ኢየሱስ ክርስቶስ ከማርያም ሥጋ አልነሳም ብዬ ከአምስት አመት በፊት ያስተማርኩት ስህተት ነው ከሥጋዋ ሥጋ ነስቷል" ብሎ ይቅርታ ጠየቀ።

ይህ አስተምሮ በይቅርታ ብቻ የሚታለፍ ተራ ንግግር አይደለም። የዶግማ ለውጥ ነው። ትልቅ የአካሄድ እና የአምልኮ ለውጥ አለው። አሁንም በስህተት ላይ ሌላ ትልቅ ስህተት የጨመረ ክህደት ነው። በትንሹ እንመልከተው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ብላ ታምናለች፤ ታስተምራለችም። ለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስን ከእመቤታችን ቅድስት ንጽህት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቷል ብላ የምታስተምረው። የዚህ ወንድማችን የይቅርታ መንፈስ ከዚህ አስተምሮ ጋር ሲነጻጸር ስህተት ብቻ ሳይሆን ክህደትም ጭምር ነው።

ሌላውን እንተወውና የወንጌል ሰባኪነትን ለአምስት አመታት መሰረት እና እውቀት ላይ ሳይሆኑ በመሰለኝ እና ደስ አለኝ ማስተማር ከክህደትም አልፎ የቅዱስ ጷውሎስ አይነት አጉል አይነት ቀናኢነት ይሆንብናልና (ምዕመናንን ማሳደድ ክርስቶስንም እንደማሳደድ የሚቆጠር ክህደት ነውና) መመለስ ይሻላል።

እስኪ እግረ መንገዴን አንድ ጥያቄ ላክል፦ ጌታን የተቀበላችሁ በወንጌል ያመናችሁ ከአምስት አመት በፊትም ከአምስት አመት በኃላም "ነው" ብሎ ሲያስተምራችሁ "ተሳስቻለሁ" ብሎም ይቅርታ ሲጠይቃችሁ በዚያው አዳራሽ ተቀምጣችሁ "አሜን" ያላችሁ አጨብጭባችሁ ድጋፋችሁን የገለጣችሁ። "ለምን?" ስለምን አላላችሁም" እንዴት?" ብላችሁስ ለምን አልጠየቃችሁም። ሰውየውን ነው የምትከተሉት ወይስ የምታመልኩት ዶግማ እና ቀኖና ያለው አምልኮ አላችሁ? ወይስ መሔጃ ያጣችሁ ናችሁ።

እኔ እንደ ክርስትና እምነት ተከታይነቴ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የስላሴን አንድነት እና ሶስትነት ከአንድ ከፍ ብላ ሁለት ከሶስት ከፍ ብላ አራት ብላ ብታስተምር ወይም
ጨፍልቃ ላስተምር ብትል ዝም ብል ክርስትናዬ ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

እናንተስ?

ደላሎች አንድ ነገር ባለበት ተረጋግቶ እንዲቆይ አይፈልጉም ምክንያቱም የገቢ ምንጫቸው እና ሥራቸው ይነጥፋልና። አንዱን ሻጭ ሌላውን ገዢ እንዳደረጉ መኖር ነው፤ የዘለዓለም የሚባል ነገር አያውቁም። ለዚህ ነው መግቢያዬ ላይ በጠቀስኩላችሁ መጠን የምንቸገረው። ደላላ በሰለጠነበት አገር ተረጋግቶ የሚኖር አንዳች ግለሰብም ሆነ ቡድን አይኖርም። አንዱን ሲሸጡ አንዱን ሲያስወጡ አንዱን ሲያስወድዱ አንዱን ሲያከስሩት ይኖራሉ። የሰማይ ቤት ደላሎችም እንደዚያው።

መረጋጋትን የሚፈልግ ደላላ ደላላ አይደለም፤ መርሐቸው ነው።

*** ***** ******
ይቀጥላል ይቆየን።

11/12/2022

የሰማይ ቤት ደላሎች

በደረሰ ረታ
ታኅሣሥ 2 ቀን 2015ዓ.ም
*********************

ለኢትዮጵያውያን ስለደላላ ማስረዳት ለቀባሪ ማርዳት ነው፤ ገጠመኜን ለመናገር ብቻ ያህል ትንሽ ስለደላላ ላውራችሁ። በኦሮሚኛ "የተቸገረ ከስር ይውላል" ረከታቱ ጀለኦላ የሚባል አባባል አለ። ያለፈውን ሳምንታት በጣም ተቸግሬ ነበረ ያሳለፍኩት። ሕጻናት ልጆች አሉኝ አንደኛዋ ትምህርት ቤት ስለምትውል ችግር የለውም። ነገር ግን በቅርቡ አመት ከሁለት ወር የሆናት ልጄ ጉዳይ አስጨነቀኝ። የጭንቀቴ ጉዳይ የቤት ሰራተኛዬ (በእኛ ቤት አጠራር ሆስተስ) ሄዳብኝ ነው። (ሌሎች አስፈላጊ ሰይ*ኖች) ይሏቸዋል።

ሳሳጥረው በነዚህ ሁለት ሳምንት ብቻ አራት የቤት ሰራተኛ ቀጥሬአለሁ። የመጀመሪያዋ በገባች በሁለተኛ ቀኗ አረብ አገር ለመሄድ ዝግጅት ላይ እንደሆነች ተናግራ ወጣች፣ ሁለተኛዋ በገባች በቀናት ውስጥ አሞኛል ብላ ሄደች፣ ሶስተኛዋ ምንም ነገር አታውቅም የምታውቀው ስልክ ማውራት እና ቴሌቪዥን ማየት ብቻ ነው፣ አራተኛዋ ደግሞ ሙከራ ላይ ነች .... የተነሳሁት ስለቤት ሰራተኞቹ ላወራችሁ አይደለም ስለደላሎቹ እንጂ።

ሁሉንም ስቀጥር ደመወዛቸው ልጅ ለመያዝ እየተባሉ ሶስት ሺ የኢትዮጵያ ብር ነበረ የሚከፈላቸው ... ገንዘቡ እንዴት እንደሚገኝ የወር ደሞዝተኛ ያውቀዋል (ሰላሳ ቀን ፈግተን አንድ ቀን ነው የሚከፈለን) አደራ ጎበዝ የሆነች የምትሻለዋን ስጠኝ ደመወዝ ያለችውን እከፍላለሁ እለዋለሁ። እሱ (ደላላው ማለት ነው) ስለተቀጣሪዋ ፕሮፋይል መዘርዘር ይጀምራል። የማትችለው የሥራ አይነት የለም። የማትችለው የምግብ አይነት (የአበሻ የፈረንጅ) የለም። ያልሰራችበት የቤት አይነት የለም። (ከኮንደሚኒየም እስከ ግራውንድ + ምናምን ) የሚገርማችሁ ይህንን ፕሮፋይል ልጆቹ (ሰራተኞቹ) ራሳቸው አያውቁትም። ደላሎቹ ቅጥፈታቸው ጫፍ የለውም።

እኛስ ብትሉ ከቀጣሪዎች ቅጥፈት ከትናንት አንማርም የደላላን ባህሪ አናውቀውም ሁልጊዜም እንሸወዳለን። ሁሌም እናምናቸዋለን ሁሌም ያሉንን አምነን የቤታችን አስተዳዳሪ፣ የልጆቻችን አሳዳጊዎች፣ የበጀታችን ማናጀሮችን ይዘን ወደቤት እንገባለን።

ህጋቸው ራሱ ከሕገመንግስቱ ሳይበልጥ ይቀራል? ኮሚሽን የሁለታችንንም እንከፍላለን፣ (የሰራተኛዋ ከደመወዝ የሚቆረጥ በሚል ሒሳብ)። በዚህ ብቻ ሶስቴ የደላላ ተበልቻለሁ።

ከገንዘብ እና ከድካም ባሻገር ምን አይነት የሥነልቦና ቀውስ እንደሚገጥመን ቤት ይቁጠረው፣ ልጆቻችን በጨቅላ እድሜያቸው የስንት ሰው ፊት እንደሚያዩ አስቡት፣ የስንቱስ ባለትዳሮች ቤት በጭቅጭቅ ሰላሙን ያጣል፣ ስንቱስ የመንግስት ሰራተኛ የአመት እረፍቱ ይቆነደዳል፣ ስንቱስ የቅርብ አለቃውን ፊት ያያል? ሆድ ይፍጀው።

ወደቀደመ ጉዳዬ ልመልሳችሁ ደላላ ማለት እንግዲህ እንዲህ ነው፤ በሰው ላብ እና ቁስል የሚከብርና ሕይወቱን የሚያቃና ነው። እርሱ እየከበረ የሕይወት መደላድሉን እያበጀ ቤትህን የሚያናጋ አጭበርባሪ ነው። ለቃሉ የማይታመን ቀላማጅ ነው።

የቆየ አንድ ታሪክ ልጨምርላችሁ ሃያ አመት ገደማ ነው ከቤት ወጥቼ የራሴን ቤት ለመከራየት 'አንዲት ክፍል ቤት ቆንጆ ጽድት ያለች ሠላማዊ ሰፈር' ፈልግልኝ ብዬ ለደላላው ነገርኩት። አገኘሁ ብሎ ደወለልኝ እንደዛሬው በመኪና አልነበረም የወሰደኝ የድሮ ደላሎች ብዙዎች መኪና አልነበራቸውምና። ረጅም መንገድ ስለቤቱ ገለጻ እያደረገልኝ ገሰገስን በገለጻው የተነሳ ልቤ ምቱ ጨመረ እስከ ዛሬ ድረስ ከቤተሰብ ጋር በአንድ ክፍል በአንድ አልጋ ላይ መኖሬ ጸጸተኝ።ቸኮልኩ ለዘለዓለም ከዚህ ቤት እንደማልወጣ ሌላ ቤት እንደማልቀይር ቃልኪዳን ገባሁ። ሳላየው ወደድኩት። ደረስን ... የሆነ ስርጥ ይሁን ስምጥ ቦታ ላይ ቆምን፣ ከቆምንበት በተወሰነ እርምጃ ርቀት ወንዝ አለ፤ ከወንዙ ዳር የአመድ ክምር አለ፣ ከአመዱ አቅራቢያ ብቻዋን ዘመናት መቆሟን የሚያሳብቅባት በሯ እንደ ሱቅ በር ለሁለት የተከፈለ (ላይ እና ታች ማለት ነው) ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር የማትሞላ ያዘመመች ቤት አየሁኝ። በስመ አብ ... ብዬ አማተብኩ። ሰው እንዴት እንደዚህ አይነት ቤት ውስጥ ይኖራል? ለዚያውም ወንዝ ዳር አጥር እንኳን ሳይኖረው። ደላላው ከሐሳቤ አቋረጠኝ። እጁን ሐሳቤን ወደሰረቀችው የአዲስ አበባን ነዋሪ አኗኗር የታዘብኩበትን ቤት ጠቆመኝ። ቀበል አድርጌ "አይገርምህም እኔም እያየኋት ነበረ ..." ከማለቴ አላስጨረሰኝም። " እኔም እንደምትወዳት ገምቼ ነበረ፤ በቃ ላንተ የምትሆን ቤት ይህቺ ናት።" ብሎ ደመደመ።

ጠላታችሁ ሰይጣን ይደንግጥ እንደደነገጣችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። በጣም ደነገጥኩ ... ምንም ማለት አልቻልኩም ... ቃላት እንደሚያጥር ያን ቀን ገባኝ። ደላላ ምን አይነት ሰው እንደሆነ ቢገባኝም ዛሬ ድረስ እንደተማረርኩባቸሁ አለሁ።

ደላላ እንግዲህ የሌለ ነገር አለ፣ ጥቁሩን ነጭ፣ መራራውን ጣፋጭ፣ የዓለማችን አስጠሊታውን ነገር ቆንጆ አድርጎ የሚተርክላችሁ ይሉኝታቢስ ነው። ግን ደግሞ ሁሉም ሰው ያምነዋል ቢማረሩበትም ተመልሰው እሱ ጋር ከመሄድ አይታቀቡም።

ምድራውያን ደላሎችን በአጭሩ በዚህ መልኩ ከተረዳናቸው ሰማያውያን ደላሎችን እንመልከት።

ሰማያውያን ደላሎች ያልኳቸውን እናንተ እንደየ ቤተእምነታችሁ ስትፈልጉ ሰባኪ፣ ፓስተር፣ መጋቢ፣ አጥማቂ፣ ወንጌላዊ፣ የጌታ ሰው፣ የእግዚአብሔር ሰው ወዘተ ማለት ትችላላችሁ። ሁሉም ለኔ ደላሎች ናቸው።

የእግዚአብሔርን መንግሥት በትክክል አይነግሩንም። በብዙ ድካም በብዙ መልካም ሥራ የምትወረሰዋን የእግዚአብሔር መንግሥት እነሱ ከፈለጉ እጃችንን ይዘው ያስገቡናል። ድነሃል ብለው ያሳምኑናል። ለነርሱ ከተጃጃልን አምላካችን ዳግም ሲመጣ (ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝ፣ ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ) የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች እንኳን ለእግዚአብሔር መንግሥት መግቢያ እንደሚያስፈልግ አይነግሩንም።

ስለ ፍቅር በፍጹም አይሰብኩንም፤ ስለ ትህትና ራስን ዝቅ ስለማድረግማ አይታሰብም። እነርሱ ትእቢት ልባቸውን ስለደፈነው በትህትና የሚበልጣቸውን አይሹም። ደቀመዛሙርቶቻቸው ሁሉ በትዕቢት የታጀሩ ናቸው ስለመንግሥተ ሰማያት እንኳን እንደ ቤታቸው ሳሎን ቀለል አድርገው እንዲያዩ አስረድተዋቸዋል። አስተሳሰባቸው ሁሉ ሌሊት ሌሊት ገነት እያደሩ ቀን ቀን ከእኛ ከአለማውያን ጋር ለመዋል ወደምድር የመጡ ይመስላሉ። ይህ ሁሉ በሰማይ ቤት ደላሎች ስብከት የተነሳ ነው።

የአበሻን ሥነልቦና በደንብ ስላወቁ አያስጨንቁትም እውነቱን አይነግሩትም ሽንገላ ብቻ ነው። "አሜን" ሲል እና ሲያጨበጭብ እልል ሲል ውሎ ከየአምልኮ ቤቱ ይወጣል። ስታንድአፕ ኮሜድ አላስቅ አላዝናና እስኪለን ድረስ እነርሱ ጥርሳችንን አያስከድኑንም። ምክንያቱም ማሳቅ ብቻ ሳይሆን 'ስለሚያድኑን'፣ በሐብት እና በቆንጆ ነገር ፕራንክ ስለሚያደርጉን፣ ትላልቅ ወንጀሎች በየመድረኮቻቸው በምስክርነት ሲናዘዙ ተጠያቂነት አለመኖሩን ስትመለከቱ ከገነት የቀጥታ ስርጭት እንጂ ሕግ ባለበት በኢትዮጵያ ምድር ያላችሁ አይመስላችሁም።

ይህ ሁሉ እንዴት ሆነ ካላችሁ ምድራችን ኢትዮጵያ ደላላ የሚያሾራት ስለሆነች ለምን? ብለን መጠየቅ ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ነው።

የሰማይ ቤት ደላሎች እንደምድራውያን ደላሎች አንድነት የላቸውም በጋራ አይሰሩም። የምድሩ ደላላዎች የቤት ሰራተኛ ሲቀጥሩ፣ ቤት እና መኪና ሲያሻሽጡ፣ ቅምጥ ሚስት ሲያቃምጡ ኮሚሽን ይጋራሉ። ሰማያዊ ደላሎች ግን በጥቅም ይጣላሉ። እንዴት እንደሚተራረቡ፣ እንደሚሰዳደቡ፣ እንደሚሞላለጩ፣ ስታዩአቸው ሰይጣንን ትሁት ሆኖ ታገኙታላችሁ።

አንዳንዴ የሰማይ ቤት ደላሎችን ክፋት ስትመለከቱ ሰይጣንን ከገነት ያባረረ አምላካችን ምነው እነዚህ ፍጡራን ታገሳቸው አስብሏችኋል። የምድር ደላሎች በገንዘባቸው የፈለጋቸውን ሲያደርጉ አውቃለሁ እንጂ አጃቢ፣ ጋርድ፣ ትጥቅ፣ ወዘተ እንዳላቸው አላውቅም።

የሰማይ ቤት ደላሎች ግን ባለስልጣን ያስንቃሉ። ግድንግድ አጃቢ እና 'ቦዲጋርድ' አላቸው። የሚሄዱበት መኪና፣ የሚለብሱት ልብስ፣ የሚጫሙት ጫማ፣ የሚኖሩት ቅንጡ ህይወት፣ ምኑም ከሐዋርያት ሕይወት ጋር አያመሳስላቸውም። የወንጌል ሰባኪነት በምድራዊው እውቀት ከዶክተሮች እና ፕሮፌሰሮች በላይ ስንት እጥፍ የላቀ ጥቅም የሚያስገኝ እውቀት አልባ 'ሞያ' ሆኗል በ21ኛው ክፍለ ዘመን።

የሰማይ ቤት ደላሎችን ጉዳይ እስከ ተአምረኛ ተከታዮቻቸው ለመግቢያ ይህን ያህል ካነሳን በዝርዝር እና በጥልቀት በቀጣይ ክፍል እናያለን።

09/12/2022

ሶስተኛው ክፍል ከባለፈው የቀጠለ ****አስታውሳለሁ ሁለቱም ልጆች ነበሩ።

ከጨቅላ እድሜያቸው ወዲህ ነፍስ ካወኩ/ካወቁ በኋላ የተገናኘነው ያቺ ምሽት ነች።

ከአመታት በኋላ በሥራ ምክንያት ለተወሰኑ አመታት እዛው ሰፈር ተመላልሻለሁ። አንድ ቀን እንኳን ጎራ አላልኩም። ምሳ ብላ ቡና ጠጣ ባይ አላገኘሁም።ተፈልጌ የመገኘቴ ከንቱነት እዚህ ጋር ጎልቶ ይወጣል። አባቴ ሞልቶለት እንዳልተወኝ ጠልቶኝ እንዳልሸሸኝ አሁን ተገልጦልኛል። ባያሳድገኝም የሚያድግ ልጅ ስለወለደ ብቻ ምስጋና ይገባዋል።

በዚህ ሰአት ጽሑፌን ስጀምር አንዲት ሴት በቴሌቪዥን መስኮት አባቷን ስትፈልግ እንደሷ አባቷን የምትፈልግ እህቷን ማግኘቷን ስመለከት ልጆች መች ነው የምንፈላለገው ብዬ ጥያቄ ፈጠረብኝ። ልጆቻችን ወላጅ ሳይሆን አክስትና አጎት እንደሚናፍቃቸው ገባኝ። ይህ ድንበር መቼ ነው የሚሰበረው የሚል የጅል ጥያቄ ጆሮዬ ላይ አቃጨለብኝ።

አራተኛው የአባቴ ልጅ እና ብቸኛው ወንድሜ የደነደነ ልብ አለው እንድል ያሰኘኝ ቀን አንድ ምሽት ላይ አለፈ። ምን እንደበደልኩት አላውቅም ከአንዴም ሁለቴ በትምህርቱ አግዤዋለሁ። እኔ ደስ ሳይለኝ ወንድም ስላላቸው ደስ እንዲላቸው አድርጌአለሁ። ከፊቴ በቆሙበት ሰአት አንድም ቀን ፊቴን አልመለስኩባቸውም ነገር ግን እኛን እየገፋህ ፈጣሪህ ጸሎትህን የሚሰማህ ይመስልሃል አለኝ። ፈጣሪ ሰው አይደለም እንጂ አዎ ልክ ነህ።

ሚስቴ ልጅ ወልዳ እሱ አጎት የሆነበትን ቤተሰብ መጥቶ ያላየ አምኜ የተቀበልኩት ወንድምነት የት ድረስ ይዘልቃል? እሱ ታላቅ ሲፈልግ እኔ ወንድም ስፈልግ እርጅና ጸጋ ሆኖልን አረፈው። ወቃሽ ከመሆን የባሰ በሽተኛነት የለም እኔ ስወቅሰው እሱም ፈጣሪ ፊት ሲከሰኝ እንደ ሰው ላንፈላለግ በአደባባይ ተጠፋፋን።

እነዚህ የዚህ ታሪክ መነሻ ምክንያት እህትማማቾች አትበትነን አሰባስበን የሚል ጥሪ ላልተገኘ አባታቸው መልእክት አየር ላይ አውለዋል። አባታቸውን ብቻ አይደለም እየፈለጉ ያሉት የማያውቋቸውን እህት እና ወንድሞቻቸውን ጭምር ነው። እኛስ እየተዋወቅን ያለን እና አውቀን የተራራቅን መጨረሻችን ምን ይሆን? ተወቃሹ ማን ይሆን? እኔ እሆንን? አንተ አልክ። እንደማትሉ ተስፋ አደርጋለሁ።

ባይቀጥል እና ሁሉ ነገር መጨረሻው ይሄ ቢሆን ይሻለኛል።

የማያልቅ ነገር አበቃሁ።
***

07/12/2022

ከባለፈው የቀጠለ****ታሪክ

የመሰናበቻ ቃላት ማፈላለግ ጀመርኩ። የትኛውም ቃላት ችኮላዬን ሊገልጥልኝ አልቻለም። አንድ ሊወጣ ያልቻለ ቃል ግን አፌ ውስጥ ይገላበጣል።

ጓደኛዬ ቀድሞ 'ሂድ .... እስክትወጣ እዚሁ እንጠብቅሃለን' አለኝ። ተነፈስኩ ቢሆንም ግን ምቾት አልሰጠኝም። መሄዴ ደስ ቢያሰኘኝም እኔን መጠበቃቸው ግን ደስ አላለኝም። ይኼንን ሐሳቤን ለመግለጥ ግን አሁንም አልቻልኩም። ምንም አዲስ ነገር አዲስ ስሜት ውስጤ ሲፈጠር አላየኹም። አይ እቆያለሁ አትጠብቁኝ የሚል ቃል ከአፌ አፈትልኮ ወጣ።

ጓደኞቼን ትቼ ወላጆቼ ከበር ይጠብቁኛል ብዬ ጥዬ መውጣት ጓደኞቼን ከመክዳት እኩል ቆጠርኩት የማላውቀውን ለማግኘት ያወኳቸውን ጥዬ ላለመምጣት ልቤ ጨከነ። ተመካከሩ አባት እንዲህ አለ፥ "እናንተ ተቀጣጠሩና ስትጨርስ ተገናኝታችሁ እቤት ይዞህ ይምጣ" ደመደመ አባትነቱን በትእዛዝ ጀመረ። ይመችሃል፣ ትመጣለህ፣ የሚጠብቅህ ሰው አለ፣ እኔ ቤት መምጣት ትፈልጋለህ፣ ወዘተ አልጠየቀኝም። እሱ ሊያገኘኝ ስለፈለገ የኔን ምላሽ አልፈለገም። ቢሆንም ባይሆንም ከዚህ የሚቀልጥ አማራጭ ለርሱ አልነበረም። ምናልባት ለዘመናት ይህቺን ቀን ሲጠብቃት ኖሮ ይሆናል። ሰሜን ሆቴል የመገናኛ ቦታችን አድርጌ ወደ ውስጥ ዘለኩ።

ምርቃቱም፣ ሽኝቱም፣ ድግሱም፣ ሽርጉዱም፣ ጓደኝነቱም በአንድ ገጽ ወረቀት ሰርተፊኬት ተተክቶ ሁላችንም ተለያየን። ይኸው ጊዜው ይነጉዳል። ሁለት አስር አመታት ቆርጥመን በላን። ፎቶ ብቻ ትዝታችንን ይዞ ቀረ። እኛ የዘጠናዎቹ ከፎቶ በቀር የሚያቀራርበን ነገር አልነበረንም። የበረታ ፖስታ ሳጥን ቁጥር ይቀያየር እንደሆነ እንጂ የረባ ስልክ እንኳን አልነበረም። ኢሜይል አይታሰብም። ፖስታውም በመስሪያ ቤት ቁጥር ወይም በኬርኦፍ ነው የምትገናኘው። ድሮ ቀረ የሚያስብል ነገር የለኝም። ሁሉም ነገር ዛሬ ላይ ነው ለልጆቻችን የተመቻቸው።

ምሽት ላይ ሰሜን ሆቴል ተገናኘን፤ ከአክስቴ ልጅ ባሻገር አንድ አንሶላ ተጋፈን አንድ መኝታ ተጋርተን አንድ የቤት ጥላ ስር ኑሮን የተጋራን የመጀመሪያው የሥራ ባልደረባዬ፣ ጓደኛዬ፣ የሩቅቅቅቅቅ ዘመዴ አብሮን ተከስቷል። (ልዩ ትዝታ ነበረን ትልቁ ግብዧ ሻይ ነበረ ሶስታችንም ሻይ አዘዝን። በሶስት ትናንሽ ማንቆርቆሪያ የፈላ ውሃ፣ ሶስት ከወተት የነጡ ሲኒዎች፣ ሶስት የከበሩ መአድን የሚመስሉ ማንኪያ፣ አንድ የስኳር ማቅረቢያ፣ ሶስት የሚነከሩ ሻይቅጠሎች ቀረቡልን።

በሰአቱ ወሬውን እየመራሁ የነበርኩት እኔ ስለነበርኩ ወደሻይው ያመራሁት ዘግየት ብዬ ነበረ። ወዳጆ እና የሥራ ባልደረባዬ 'አራዳ' ቢጤ ነበረና ሻዬውን እየጠጣ ደረስኩበት የአክስቴ ልጅ ግን ግራ ተጋብቶ እኔን ይጠብቀኛል። ጠጣ እንጂ አልኩት እንዴት አድርጌ በሚል እይታ አየኝ፤ ተረዳሁት 'አሪፍ አይቸኩልም' አይደል። አበጃጀሁለት። መጠጣት ጀመርን ጨወታው ደርቷል። ባልደረባዬና ጓደኛዬ የመሬን ጉሽ ጠላ እየጠጣ ያለ ይመስል ቱፍ እያለ ነው። ለካስ ሻይ ቅጠሏ ጉድ አምጥታለች።

ጠራሁት ምቾት ውስጥ አይደለም ግብዧው ቅጣት አክሎበታል የጓጓለትን ሻይ እንደልቡ ለመጠጣት አልቻለም። ጉሽ ጠላ ሆኖበታልና።

አፌ አላረፈም ምነው ቀደህ ጨመርክበት አልኩት 'አይ እንደዚህ ይሻለኛል' ብሎ አለማወቁን ሸመጠጠን። እኔም ቢሆን አይቼ እንጂ ጠጥቼ አላውቅም። የሚነከር ሻይ ቅጠልና አባቴን ያወኳቸው በአንድ ቀን ነበረ።

ምሽታችን በሳቅ እንደታጀበ ጉዞ ወዳልታሰበ ሰፈር አጣና ተራ 18 አከባቢ ሆነ። ያ ወቅት የቀለበት መንገዱ መሰራት የጀመረበት ወቅት ነበረና የምሽት ጉዞአችንን የተደላደለ አላደረገውም። በብርሃን የፈለገኝን አባት ፍለጋ በጨለማ ለማግኘት መኳተን ጀመርኩ። የተቆፋፈረውን መንገድ ተሻግረን ደረስን። የምሽት አቀባበል ድምቀቱ አይታይም። በምሽት ሹልክ ብዬ እንደገባሁ ሹልክ ብዬ ሲነጋ ወጣሁ።

የወንድምና እህቴ እናት እግዚአብሔር ይስጣትና ነፍስ አውቄ ከአባቴ ጋር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የመተኛት እድሉን ሰጠችኝ። ላስታውሰው የማልችላቸውን ነገሮች ስንጫወት እንዳመሸን ትዝ ይለኛል። ከዚያ ቀን የቀረበ ዳግመኛ የምናወራበት እድሎች ሳይኖሩ ለሁለተኛ ጊዜ የእድሜዬ ግማሹ ዳግም ነጉዷል። አባቴም እድል ገጥሞት ምርቃቴ እና ጋብቻዬ ላይ ቆሟል። ወልዶ ካሳደጋቸው አንዷን ድሯል። ከሌላ የወለዳትን አሳድጎ ለቁምነገር ባያበቃትም ለአፈር አብቅቷል። አለን እሱም አለ።

ደስ የሚለው ነገር እድለኛ ሆኜ ሳልፈልገው ፈልጎ አገኘኝ። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ቤተሰቦች በተለያየ ሚዲያዎች ሲፈላለጉ ሳይ አባቴ እርሱ ራሱ ፈልጎ ባያገኘኝ እፈልገው ነበር እላለሁ። እንጃ። ልፈልገው ብልስ ትዝታዬ፣ ምልክቴ፣ ምክንያቴ ምንድን ነው? እኔና አባቴ ትዝታ የለንም። ምልክት የለንም። ታሪክ የለንም። እንዲህ ተጀምሮ እዚህ ጋር ተቋረጠ የሚባል የቤተሰብ ታሪክ የለንም። ደስ የሚለው ግን ፈልገን ይሁን ሳንፈልግ የምንጠፋፋው ተገናኝተናል።

ደስ ከሚለኝ ነገር አጥቼ ያገኘኹት ነገር ባይኖርም ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ወንድማቸውን ማግኘታቸው እና በደንብ ነፍስ እስከሚያውቁ ድረስ ከጎናቸው በመሆኔ ደስ ይለኛል። ያቺን ምሽት ደስታዬንም ይሆን አለመደሰቴን በሆዴ አምቄ እነርሱን ደስ በሚል ፊት መቀበሌ እህትና ወንድሜ በእቅፌ ማምሸታቸው ደስ ይለኛል።

በመገኘቴ መሃል እህቴ እና ወንድሜ ሲማሩ አጠገባተው መኖሬ ሲመረቁ ያሻቸውን አድርጌ መመረቃቸው እንደ ዕድሜዬ ታላቃቸው ሆኜ መገኘቴ ደስታዬ ነበረ። በደስታዬ መካከል ሐዘኔ የልብ ስብራቴ የሆነችው በእህትነቷ ትልቅ ተስፋን የጣልኩባት ስሜን እንኳን መጥራት ሳይቻላት ወንድሜ እያለች በፍቅር ቃላት የምትጠራኝ የአባቴ ሶስተኛ ልጅ የኔ ሁለተኛዋ እህት ሞት ከእናቴ ሞት በላይ ከፈጣሪዬ ጋር እንድንኳረፍ አድርጎኛል።

የመጨረሻ ድምጿን የሰማሁት በሰው አገር እያለች ከህመም እንዳገገመች ነበረ። ተሽሎኛል እመጣለሁ ብላ አታላኝ ላትመጣ ወዳለያየን ወደ አምላኳ በዶኗን በሳጥን አሽጋ ነፍሷን በፈጣሪ እቅፍ አደረገች። የአባቴን ትርፍ የሷ በልብ ተዳፍኖ የቀረ ፍቅር ብቻ ነው።

* **
ይቀጥላል

05/12/2022

1992 ዓ.ም የፋሲካ ፆም ሊፈታ አንድ ሳምንት ሲቀረው አርብ ቀን ይመስለኛል። ከምሣ ሰአት በኋላ ሲሆን ሰአቱን በውል አላስታውሰውም።

ከተቀጠርኩበት መሥሪያ ቤት የመጀመሪያውን ስልጠና ወስጄ የምረቃት ወይም የመሸኛኛ ፕሮግራም በመጠኑ ተዘጋጅቷል። ልጆች ስለነቀርን ለበአል ከቤተሰብ ጋር እንድንውል አስበውልን እንጂ ጊዜው ገና አንድ ወር ይቀረው ነበረ።

ፕሮግራሙን ከሚያዘጋጁት መካከል አንዱ እኔ ነኝ፤ እንደውም ዋነኛው ነኝ። የከተማ ልጅ ባልሆንም ለአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ (መቶ ኪሎ ሜትር) ስለመጣሁ እንደ ከተማ ሰው ነው የሚያዩኝ አብረውኝ የነበሩት ሰልጣኞች።ደግሞም ነበርኩ እኔ አልነበርኩ እንዴ ሰፈር የማስጎበኛቸው እና የባስ ትኬት የምቆርጥ ታክሲ ለመያዝ ቦታ የምለይ። የሁሉም ገንዘብ እንዳይጠፋ እኔጋ ነበረ የሚቀመጠው። የታክሲም የሻይም የሚከፈለው ከዚሁ ላይ ነው። ጥሩ አስጎብኚ ነበርኩ።

የምርቃታችን ቀን ምሳ ሰአት ከሄድኩበት ስመለስ ሁለት በጉጉት የሚጠብቁኝ አካላት ነበሩ። አንደኛው ጥቁር እንግዳ ሲሆን ሁለተኞቹ ሰልጣኞች ነበሩ። የሰልጣኞቹን ለጊዜው እንግታውና ወደ ጥቁር እንግዳው ልውሰዳችሁ።

ጥቁር እንግዶቹ ሁለት ናቸው፤ ከሁለት አንደኛውን ብቻ ነው የማውቀው። ቢሆንም ትንሽ ዘለግ ካለ አመታት በኋላ ነው የተገናኘነው። ሁለተኛውን አለማወቄም ይሁን ማወቄ የሚደነቅ ነገር አልፈጠረብኝም። በቦታውም መገኘታቸው በሰአቱ ያንን ያህል ጉድ አላሰኘኝም። በኋላም ቢሆን። ዋናው ጉዳይ ከበር ውጭ የጠበቀኝ ሳይሆን ከበር ውስጥ ያሉት ናቸው። (በዕለቱ አብረውኝ የተመረቁትን ወይም ስለጣናውን አብረን ያጠናቀቅናቸውን ልጆች ምስል በፎቶ ስመለከት አሁን ያህል ስሜቱ በውስጤ አለ።)

ከሰልጣኞች ውስጥ አንደኛው ከአገር ውጪ መሆኑን አውቃለሁ ሌሎች በስራ ገበታቸው እንዳሉ እጠረጥራለሁ። አንድ ሴት ግን ዛሬም አንድ ሕንጻ ላይ በተለያየ ክፍል እንሰራለን። እርጋታዋ ላለፉት ሁለት አሥርት አመታት እንዳለ ነው። ወጣትም እናትም ሆና እንደዛው ነች።

ሁለቱ ሰዎች አንደኛው የአክስቴ ልጅ ሲሆን ከልብ የምወደው ጓደኛዬ ነው። ዝምድናው ሳይሆን ጓደኝነቱ ይበልጥብኛል። ከሥጋው ይልቅ ጓደኝነቱ ለኔ ብዙ ነገር እንዲያደርግ አድርጎታል። ይወደኛል፣ የሚወደውንም ነገር ሳይቀር ለኔ ይሆን ዘንድ ይመኛል። ታላቅና ታናሽ ወንድምና እህቶች ቢኖሩትም እንደሱ ጓደኞቼ ስላልነበሩ አልተፈላለግንም። ካገባሁ በኋላ አንዴ ቤት ድረስ መጥቶ ጠይቆኛል።አሁን ላይ የት እንዳለ አላውቅም።

ከአይን የራቀ ከልብ ይርቃልና ተራርቀናል። በአክስቴ ልጅነቱ ታናሹን ከአንዴም ሁለቴ ቅርብ ጊዜ ተገናኝተናል ስልክም ተለዋውጠናል ግን አንጠያየቅም። ለዚህ ነው ከሥጋ ዝምድና ጓደኝነት የሚበልጥብኝ።

ጓደኛዬና የአክስቴ ልጅ አብሮት የቆመውን ሰው 'ሠላም በለው እንጂ' አለኝ። በውስጤ ከነበረው ችኮላ ጋር ተደማምሮ ያንን ያህል ሳልጓጓ እጄን ለሠላምታ ዘረጋሁለት። ሠላም ተባባልን ከዚያኛውም በኩል ከኔ ባልተናነሰ ሁኔታ የሠላምታዬን አጸፋ መለሰልኝ። አይኖቹ ግን አይኔ ውስጥ ነበሩ።የጥፋተኝነት ስሜት ይነበብባቸዋል።

ጓደኛዬን ለመሄድ ተሰናበትኩት እስኪ መጨረሻቸውን ልይ በሚል ትዝብት ሁለታችንንም ተመለከተን። ቻው ቸኩላለሁ ውስጥ እየጠበቁኝ ነው አልኩት ወደ ስልጠና ማዕከሉ በር በጣቴ እያመላከትኩ። አጠገቡ የቆመውን ሰው በእጁ እየጠቆመ 'አታውቀውም' አለኝ። ቀና ብዬም አላየሁትም መልሴ አጭር ነበረ አላውቀውም። ልቤ በቦታው የለም ግቢ ውስጥ ነው ዝግጅቱ ጋር ደርሷል። እያስተናበርኩ ነው።

'አባትህኮ ነው' ... ስሙን ጠራልኝ አልሰማሁትም። አባት እጁን ዘረጋ። መልሼ በድን ሥጋዬን እጄን ዘረጋሁለት። እጄ ወደ አባቴ ሣይሆን ጓደኛችሁ ሰው ሰላም እያል እናንተም በስፍራው ስለተገኛችሁ ሠላም የምትሉት አይነት ሰላምታ ነበረ። ጓደኛዬ(የአክስቴ ልጅ) 'ተሳሳሙ እንጂ' አለ፤ ተቃቀፍን። ወዲያው ከእቅፉ ወጣሁ የጥላቻ አልነበረም የችኮላ እንጂ። አባት እስከ አሁን ዓይኑ እንጂ አፉ ምንም አይናገርም። ሙሉ ለሙሉ ሐላፊነቱ የወደቀው በአክስቴ ልጅ ላይ ነው። አባትና ልጅ ዛሬም ድረስ አያወሩም በልብ ብቻ ነው የሚነጋገሩት። አባት ሲበዛ ዝምተኛ ነው ልጆችም የአባትን ዝምታ ወርሰዋል።

እንደዛ ቀን ቸኩዬ አላውቅም። ፕሮግራም እንዳለኝና መሄድ እንዳለብኝ ነገርኳቸው ለጓደኛዬ እንጂ ለአባትየው አልነበረም። እዚህ መሆኔን አውቀው እኔን ለማግኘት ጓደኛዬ የሆነው የአክስቴ ልጅ ከአባቴ ጋር ሊያስተዋውቀኝ እንደመጡ ገለጠልኝ።

አባቴን ሳገኘው የመጀመሪያዬ አልነበረም በልጅነቴ አየው ነበረ አባቱ/አያቴ ጋር ሲመጣ እንገናኛለን። ግንኙነታችን ግን ከሕጋዊ ሚስቱ የወለደኝ ሳይሆን ከውጪ ድንገት ሳልፈለግ እንደተወለደ ልጅ ነበረ። ያኔም አሁንም ስንገናኝ የሆነ ምቾት ተሰምቶት አላየሁበትም። ለዚህ ነው አባቴን መለየት/ማወቅ የተሳነኝ። እናቴ ግን አባታችንን እንዳንረሳው ብዙ ጥረት ታደርግ ነበረ። ፎቶው ቤታችን ነበረ እንዳንረሳው አያታችን የልብስ ሳጥን ውስጥ ነበረ ተቆልፎበት የሚቀመጠው ሳጥኑ በተከፈተ ቁጥር እንድናየው ይደረጋል። እኛ ግን አናየውም። አያታችን አባታችሁኮ ነው ሳሙት እያሉ ሥጋ የሌለው አካል ያስታቅፉናል በመስታወት ውስጥ ያለን ምስል።

ያ ምስል በፍጹም በውስጤ የለም። ከፊቴ የቆመውን ሰው በአባትነት አይደለም ድንገት በማውቀው ሰው ልክም ላውቀው እና ልቀበለው/ላውቀው አልቻልኩም።

ይቀጥላል

Address


Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Visionary Ethiopian posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Visionary Ethiopian:

Shortcuts

  • Address
  • Telephone
  • Alerts
  • Contact The Business
  • Claim ownership or report listing
  • Want your business to be the top-listed Media Company?

Share