
12/08/2025
ለፋኖ ሕክምና አልሰጠንም - ዓይደር ሆስፒታል (መቐለ)
-------
"ለፋኖ ቁስለኞች ህክምና አልሰጠንም" ሲል አይደር ሆስፒታል ገለፀ፡፡ በሰሞኑን በአማራ ክልል ቆቦ ውስጥ በፋኖ ታጣቂዎችና በመንግስት ሀይሎች መካከል የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ ቁስለኛ ታጣቂዎችን መቀሌ የሚገኘው አይደር ሆስፒታል እንዳከመ ሲገለፅ መቆየቱን ወጋህታ ፋክትስ አውስቷል፡፡
እንደዘገባው ቅዳሜ ነሀሴ 3 ቀን 2017 በቆቦ ከተማ በተፋላሚዎቹ መካከል ከፍተኛ ውጊያ የተከናወነ ሲሆን ይህንን ተከትሎ በውጊያው የቆሰሉ ታጣቂዎች በመቀሌ አይደር ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ ስለመሆኑ በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ተገልጿል፡፡
ስለጉዳዩ የአይደር አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል ህዝብ ግንኙነት ቢሮን ማነጋገሩን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ቢሮው በሰጠው መልስም ‹‹ሰሞኑን በአማራ ክልል ከተከናነው ውጊያ ጋር በተያያዘ እኛ ጋር ተኝቶ የታከመ አንድም ቁስለኛ የለም›› ብሏል፡፡ የዜና ምንጩ እንዳለው የሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል ሰራተኞችም እንዲህ አይነት ታካሚ እንዳላዩ ተናግረዋል፡፡