13/08/2022
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር እና የመስቃን ወረዳዎች ውሳኔ በተመለከተ ከህገመንግስቱ አንጻር ሲታይ:-
በምንተስኖት መቻል
በዛሬው እለት ሁለቱ የመስቃን ወረዳዎች እና የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ምክርቤቶች በክላስተር ለመደራጀት በሙሉ ድምፅ አጽድቀዋል። ውሳኔያቸውን አከብራለሁ። ግን ደግሞ ውሳኔው የብልጽግና ፓርቲ ከTPLF የወረሰው የሴራ ፖለቲካ ውጤት እና ጉራጌን የመከፋፈል እቅድ እንደሆነ ለአፍታም አልጠራጠርም።
የሆነ ሆኖ ዋናው ነገር ውሳኔያቸው ህገመንግስቱን መሠረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም? የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በ2011 ዓ.ም በክልል ለመደራጀት በሙል ድምጽ ባጸደቀው ውሳኔ ላይስ አሉታዊ ተጽእኖ አለው ወይስ የለውም የሚሉት ነጥቦች ማየቱ አስፈላጊ ሲሆን በዚህ በጣም አጭር ጽሁፍ ይህንኑ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
1. እንደሚታወቀው የጉራጌ ዞን ምክርቤት በክልል ለመደራጀት አስፈለጊ መስፈርቶች ተብለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 46 ስር የተደነገጉትን መስፈርቶች በማሟላት ህዳር 17/2011 ዓ.ም በክልል ለመደራጀት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
ይህም ማለት በወቅቱ የቡታጀራም ሆነ የመስቃን ወረዳ ተወካዮች ድምጻቸውን ሰጥተዋል ማለት ነው። የሆነ ሆኖ ጥያቄው በህገመንግስቱ አንቀፅ 47 መሠረት ለክልሉ ምክርቤት ቢቀርብም ምክር ቤቱ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ባለማደራጀቱ ምክንያት በወቅቱ በነበረው የፌዴሬሽን ምክርቤት ስልጣን በሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 251/2001 አንቀጽ 19 መሠረት የጉራጌ ዞን ምክርቤት ቅሬታውን ለፌዴሬሽን ምክርቤት አቅርቦ መልስ በመጠበቅ ላይ ነው።
እንግዲህ በዚህ መልክ ህግና ስርዓት ጠብቆ የቀረበ ጥያቄ ወደኋላ ሊመለስ የሚችልበት ምንም አይነት የህግ አግባብ እንደሌለ መረዳት ያስፈልጋል።
2. ሌላውና መሠረታዊው ነገር በህገመንግስቱ አንቀጽ 47 (2) ስር በግልጽ እንደተደነገገው በክልል መደራጀት የሚችሉት ብሔሮች: ብሔረሰቦች ወይም ህዝቦች ብቻ ናቸዉ። ህገመንግስቱ ብሄር: ብሄረሰብ እንዲሁም ህዝብን በተመለከተ የተናጥል ትርጉም ባይሰጥም በአንቀጽ 39(5) ስር ወጥ በሆነ መልኩ ትርጉም የሠጣቸው ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሠረት ብሔር፡ ብሔረሰብ ወይም ህዝብ ማለት ሰፋ ያለ የጋራ ባህል: የጋራ ቋንቋ: የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ እና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸዉ ብሎ ትርጉም ይሰጣል።
እንግዲህ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የምንችለው ሁለቱ የመስቃን ወረዳዎችም ሆኑ የቡታጀራ ከተማ አስተዳደር የብሔር: የብሔረሰብም ሆነ የህዝብ ትርጉም የማያሟሉ ሲሆን ጉራጌ በሚለው ብሔር ውስጥ የታቀፉ ናቸው። ይህ ከሆነ ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት በህገመንግስቱ አንቀጽ 47(2) መሠረት ከክልል ጋር በተያያዘ እራሳቸው ችለው ምንም አይነት ህጋዊ ውጤት ሊኖረው የሚችል ውሳኔ ማሳለፍ አይችሉም።
በአጭሩ በዚህ ጉዳይ መወሰነ የሚችለው ጉራጌ የሚለውን ብሔር የሚወክለው የጉራጌ ዞን ምክርቤት በመሆኑ ውሳኔያቸው ህገመንግስታዊ መሠረት ያለው አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ ከጅምሩ የክላስተር አደረጃጀት ህገመንግስታዊ መሠረት ያለው አይደለም። ክላስተር የሚለው ቃል እራሱ ለህገመንግስቱ ባዳ ነው። በመሆኑም ከላይ ከተጠቀሰው ምክንያት በተጨማሪ በክላስተር ለመደራጀት ማጽደቅ በራሱ ህገመንግስታዊ መሠረት ያለው አይደለም።
በመጨረሻም የጉራጌ ህዝቦች ሆይ የቤት ስራችን ብዙ ነውና ምስራቅ ምዕራብ ሳንል አንድነታችን እናጠናክር።
Emat Gurage