09/08/2023
❤ ?
❤ ?
❤ ?
ከዝሙት አጋንንት እና ከዝንየት በተጨማሪ በሕልመ ሌሊት የሚፈትነን አጋንንት የትኛው ነው?
❤ ?
በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
ሼር በማድረግ ለወዳጆ ያንሸራሽሯት
በትዕግስት እና በጥሞና አንብቡት!
የወለላይቱ እመቤት ልጆች መቼም ሱባኤ አይደል! በድካም ውስጥ ሆኜ ስለጻፍኩ የሐሳብ መደጋገም ካለ እያረማችሁ አንብቡት፡፡ በዚህ በሱባኤ የአጋንንት ውጊያ የሚበረታበት፣ሕልመ ሌሊት ደግሞ በተደጋጋሚ የሚከሰትበት ነው፡፡ የበጎ ነገር ጠላት አጋንንት እኛን ከመንፈሳዊ አገልግሎት እና ተገልጎሎት ለማሰናከል እኛ ላይ ዓይኑን ፈጠጥ፣ጥርሱን ገጠጥ የሚያደርግበት ጊዜ በአጽዋማት ወቅት ነው፡፡
ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) የሚባለው አንድ ሰው ተኝቶ በሕልሙ ወንድን በሴት፣ ሴትን በወንድ አምሳል እንደ ገሐዱ በሚመስል ሩካቤ ሥጋ የሚታየንና ከሰውነታችን ፈሳሽ የሚወጣበት ሂደት ነው፡፡ ዝንየት የሚባለው ደግሞ በሕልመ ሌሊት የሚፈታተነን አጋንንት ነው፡፡ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ወንድና ሴት ሳይል በማንኛውም ሰው ላይ በተለያየ ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡
በሱባኤ ጊዜ ሕልመ ሌሊት ከመታን እለቱን ቤተ-ክርስትያን በተለይም ቤተ-መቅደስ መግባት፣ቅዱስ ቁርባን መቀበል፣ጸበል መጠመቅና መጠጣት፣ አንችልም፡፡ በማግስቱ ግን ሰውነታችንን ታጥበን፣ልብሳችንን ቀይረን ቤተ-ክርስትያን መግባት፣ቅዱስ ቁርባን መቀበል፣ጸበል መጠመቅና መጠጣት እንችላለ፡፡ እንደዚህ የምናደርገው አንደኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ስለሆነ ነው፡፡
ሁለተኛ ቅድስት ለሆነችው እናት ቤተ-ክርስትያን ክብር ከመስጠት አንጻር ነው፡፡ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን በዘሌዋውያን ምዕራፍ 15÷2 ላይ ‹‹ማንም ሰው ከሥጋው ፈሳሽ ነገር ቢወጣ፣ስለሚወጣው ነገር ርኩስ ነው›› ይልና እዛው ቁጥር 16 ላይ ‹‹ማንም ሰው ዘር ከእርሱ ቢወጣ፣ገላውን ሁሉ በውኃ ይታጠባል፣እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው›› ይላል፡፡ /ዘሌ 15÷16/
ተወዳጆች ሆይ ልብ በሉ ‹‹ማንም ሰው›› ነው እንጂ ወንድ ሴት፣ወጣት አዛውንት አይልም፡፡ ይህ የሚያሳየው ኦርቶዶክስ የሆነ በየትኛው ጾታ እና የእድሜ ክልል ያለ ሁሉ ሕልመ ሌሊት ከመታው እለቱን ሳይሆን ማግስቱን ነው ቤተ-ክርስትያን መግባት የሚችለው፡፡ ‹‹እስከ ማታ›› የሚለው ሕልመ ሌሊት ሲመታን ለአንድ ቀን ብቻ የተከለከልን መሆናችን ያስረዳል፡፡
መቼም ሕልመ ሌሊት የሚመታን ማታ ወይም ሌሊት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ማታ ወይም ሌሊት ሕልመ ሌሊት ከመታው ቀኑን ውሎ እስከ ማታ ነው የሚረክሰው፡፡ ከማታ በኃላ ንፁህ ይሆናል፡፡
ወዳጆቼ አንዳንዶች ‹‹ሕልመ ሌሊት ከተመታችሁ እስከ ሦስት ቀን ቤተ-ክርስትያን መግባት አይቻልም›› ይላሉ፡፡ ይህንም ‹‹ማነው ያለው›› ስትሉ የፈረደባቸው ‹‹አባቶች›› ናቸው ይላሉ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም አባቶቻችንም የሚነግሩን እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቤተ-ክርስትያን የማንገበው ሩካቤ ሥጋ ስንፈጽም ብቻ ነው፡፡
ሕልመ ሌሊት መታን ማለት በቤት እና በቅጽረ ቤተ-ክርስትያን ሆኖ መጸለይ አይቻልም ማለት አይደለም፡፡ በሱባኤም ሆነን ሕልመ ሌሊት ቢመታን ሰውነታችን ታጥበት ሱባኤው መቀጠል እንጂ ማፍረስ የለብንም፡፡
❤ ?
ወዳጆቼ ሕልመ ሌሊት በራሱ ኃጢአት አይደለም፡፡ ግን ኃጢአት የሚሆንበት ሂደት አለው፡፡ አንድ ሰው በሕልሙ ሕልመ ሌሊት ቢመታው በዚህም ከሰውነቱ አባለ ዘር ይፈሳል፡፡ የአባለ ዘር መፍሰስ ኃጢአት የሚሆነው በራስ ፍቃድ ሲሆን ነው፡፡ ለምሳሌ ወዶ እና ፈቅዶ ግለ ወሲብ ሲፈጽም፣የወሲብ ፊልም በማየት ከሚመጣ የሰውነት ሙቀት ጋር ዘር ሲፈስ፣ከተቃራኒ ጾና ጋር በሚደረግ አልባል ንክኪና መሳሳም ነው፡፡
ሕልመ ሌሊት እላፊ በልቶ እና ጠጥቶ ከሚመጣ የሥጋ ፈተና ከሆነ ኃጢአት ይሆንበታል፡፡ ቅድስናን የሚያጎድል በመሆኑ የኃጢአተኝነት ስሜት እንዲጫነን ያደርገናል፡፡ ግን አንድ ሰውን ሕልመ ሌሊት ቢመታው ኃጢአት የሚሆንበት ሂደት አለ፡፡ ይህም አንድን ሰው ሕልመ ሌሊት ሲመታው ማለትም አጋንንቱ በሚያውቃት ሴት ተመስሎ በተኛበት ተገናኝቶት ዘሩን ቢያስፈስሰው የዚህ ችግር ሰለባ የሆነው ሰው በተፈጠረው ነገር ለምሳሌ ሴቷን እያሰበ፣ በሕልሙ ያየውን እያሰበ የሚደሰት፣ በሕልሙ የተፈጠረውን ግንኙነት በምልሰት እያየ ደስታን ካጣጣመ ኃጢአት ነው፡፡
ምክንያቱም ይሁዳ በመልእክቱ ‹‹እያለሙ ሥጋቸውን ያስደስታሉ›› ብሏልና፡፡ /ይሁ 1÷8/ በሕልማችን የተፈጠረውን ሕልመ ሌሊት በምልሰት በማየት እና በማሰብ መደሰት ሳይሆን መጸጸት መቆጨት ካልተሰማን ኃጢአት ነው የሚሆንብን፡፡
ወዳጆቼ የአጋንንት የረከሰ ሐሳብ በሕልማችን እየተከሰተ ሕልመ ሌሊት ሲያጋጥመን የተፈጠረውን ክስተት በጸጸት አጋንንቱን ልናሳፍረው ይገባል እንጂ የሆነውን እንደ በጎ ነገር ልንቀበለው አይገባም፡፡ ይህ እሳቤያችን ከፈጣሪ መለኮታዊ እርዳታ እንድናገኝ ይረዳናል፡፡ የማንቆጭ፣የማንጸጸት ከሆነ የዝንየት አጋንንት ይለምድና የሌሊት ደንበኛው ያደርገናል፡፡
እዚህ ላይ አንድ መረሳት የሌለበት ነገር አለ፡፡ አንዳንዴ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) በሰይጣን ፈተና ብቻ ላይከሰት ይችላል፡፡ ምናልባት ከምንጠቀማቸው ምግብና መጠጥ እንዲሁም ከሥጋ ባህርያችን ሊከሰት ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሰውነታችን ሲስማማው በራሱ ጊዜ ፈሳሽ ሊወጣ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሮ ነው፤ ምንም ማድረግ አይቻልም በጸጋ መቀበል ነው፡፡ ለምሳሌ ማታ ትኩስ ነገር ሙቅ፣ሻይ አብዝተን የምንጠጣ ከሆነ በዘር ከረጢጣችን ያለው አባለ ዘር በራሱ ጊዜ ሊፈስ ይችላል፡፡
ተወዳጆች ሆይ በተአምረ ማርያም ላይ እንደሰማችሁት በሕልመ ሌሊት የተፈተነው ወጣት መነኩሴ ሕልመ ሌሊት ሳይሆን በሥጋው ምክንያት ሞት የመጣበት ስለመሰለው ‹‹የፍትወትን ጣዕም ዛሬ ቀምሰሻልና ወዮልሽ›› በማለት አምርሮ እራሱን ጠልቶ ወደ እመቤታችን አንብቶ ቢማጸናት እመቤታችን ተገልጣ ፈተናውን አርቃለት፣በእጆችዋም ምልክት አድርጋለት ከሕልመ ሌሊት ተላቆ በሰጠችው ሐብተ ፈውስ ብዙ ድንቆችን አድርጎ ነበር፡፡ እኛም ወለላይቱ እመ ብርሃን በሕልመ ሌሊት የሚፈትነንን አጋንንት በጸሎቷ እንድታስርልን፣እንድታርቅልን ከተማጸናት በእውነትም ይህን ፈተና፣ይህን መናጢ ታርቅልናለች፡፡
❤ ?
ተወዳጆች ሆይ ሕልመ ሌሊት ከሚከሰትብን ምክንያቶች ዋና ዋናዎችን ከዚህ በታች እናያለን፡፡
1ኛ/ በአጋንንት ይከሰታል
በጣም የሚገርመው በሕልመ ሌሊት (ዝንየት) የተፈተናችሁ እስቲ ልብ በሉ፡፡ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ሳትገቡ በዓለም ሳላችሁ ብዙም አይከሰትም፡፡ ቢከሰትም ለአቅመ-አዳምና ለአቅመ ሔዋን በደረስንበት ወቅት በሥጋ ባህሪያችን ይከሰታል፡፡ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ገብተን በተግባር መኖር ስንጀምር ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) በተደጋጋሚ ይመታናል፡፡ በተለይ ወንዶችን ቋሚ ደንበኞች ያደርገናል፡፡
ወዳጆቼ አጋንንት ጸበል እንዳንጠመቅ፣ ቤተ ክርስትያን ገብተን ጸሎት እንዳናደርስ፣ ከመለኮታዊው ማዕድ እንዳንቋደስ/ቅዱስ ቁርባን እንዳንቀበል/ ከሱባኤ ዋሻ ለማስወጣት ከሚጠቀምበት ዋንኛ ማሰናከያ መፈተኛው ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ነው፡፡ አባቶቻችን ‹‹ተጻቦዖ›› ይሉታል ‹‹ተጻብዖ›› ማለት ቃሉ የግዕዝ ሲሆን መጣላትን ያመለክታል፡፡
እኛ ሀገር ሰላም ብለን በተኛንበት ሰይጣን በማናየው መልኩ በሕልመ ሌሊት ስለሚጣባንና እኛ የማንፈልገውን ፈቃደ ሥጋ በማሳየት ፈትኖን ከሰውነታችን ፈሳሽ እንዲወጣ ስለሚያደርግ ‹‹ተጻብዖ›› ብለውታል፡፡ በእውነት ከዚህ በላይ ምን ጸብ አለ? ሰው የማይገላግለን፣ሰው የማይደርስልን፣ጮኸን የማናመልጠው ጠብ፡፡
ተወዳጆች ሆይ በሱባኤ ላይ ሆነን አጋንንት በሕልመ ሌሊት ቢፈትነን ሱባኤያችን አይፋረስም፡፡ ሕልመ ሌሊት ስለመታን ሱባኤያችን አይቋረጥም፡፡ ምናልባት በዋሻ ውስጥ ሱባኤውን የያዝን ከሆንን ለአንድ ቀን ከደጅ እንሆናለን አልያም ሰውነታችንን ታጥበን ተመልሰን ልንገባ እንችላለን፡፡
ይህን የሚወስነው የገዳሙ የአባቶች ሥርዓት ነው፡፡ ስለዚህ በሱባኤ ጊዜ በሕልመ ሌሊት በተደጋጋሚ ብንፈተን ሊደንቀን አይገባም፡፡ ይልቁንም ከአጋንንቱ ጋር በስውርና በገሃድ እየተዋጋን ስለሆነ ደስ ሊለንና በጸሎት ልንዋጋው ይገባል፡፡
ሰይጣን ሕልመ ሌሊትን (ዝንየትን) ለጸሎት ማስታጎያነት ይጠቀምበታል፡፡ ሌሊት ጸሎት ካስለመድን ከመነሳታችን በፊት ሕልመ ሌሊት ይመታናል፡፡ ከዛ በኋላ ተነስተን መጸለይ ይከብደናል፡፡ ከሰውነታችን ፈሳሽ ስለወጣ፤ ጥሩ ስሜት ስለማይሰማን ‹‹ጠዋት ታጥቤ እጸልያለሁ›› በማለት ጸሎታችንን እናስተጓጉላለን፡፡
ለዚህ መፍትሄው በፍፁም ጸሎታችንን አለመተው ነው፡፡ በዚያ በሌሊት ሙሉ ሰውነትን መታጠብ ስለሚከብድ ከቻልን ፈሳሽ የወጣበትን እርጥበት የተሰማንን ቦታ ታጥቦ መጸለይ፡፡ ሴቶችም አንቀጸ ሥጋችሁን አሊያም እጃችሁን በመታጠብ ጸሎታችሁን መቀጠል፡፡
ሰይጣን የራሳችንን ሰውነት እየተጠየፍን ጸሎት እንድንተው ነውና የሚሻው በምንም ምክንያት ጸሎት መተው የለብንም፡፡ እንኳን በሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ተመትተን ቀርቶ በጥሩ ሰዓት ማናችውንም ንፁሆች አይደለንም፡፡ የሚገርመው የማያፍረው ሰይጣን በሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ቤተክርስትያን ገብቶ ይፈትነናል ማለት ሳይሆን፤ እኛ ላይ ያለው አጋንንት በስውር ለዚህ ፈተና ሊዳርገን ይችላል፡፡
ቤተ ክርስትያን ለንግሥ አዳር ስንሄድ አባቶች አትተኙ የሚሉን አንድም ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ሊመታንና ሊፈትነን ስለሚችል ነው፡፡ ለአንድ ቀን ሌሊት ቤተ-ክርስትያን ጊዜያችንን በጸሎት ብናሳልፍ ካልሆነ ማህሌቱንና ሰዓታቱን ብንሰማ ይበልጥ ጥቅም ስላለው አለመተኛቱ ይመረጣል፡፡
2ኛ/ የዝሙት መንፈስ ካለብን
ተወዳጆች ሆይ የዝሙት አጋንንት ያው አጋንንት ቢሆንም ከሌሎቹ አጋንንት የሚለው በተልዕኮው ነው፡፡ የዝሙት አጋንንት ሰዎችን በዝሙት ማጥመድና መጣል፣ከቅድስና ሕይወት ሰዎችን ማግለል ነው፡፡ የዝሙት መንፈስ ካለብን ይበልጥ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ሊፈትነን ይችላል፡፡ የዝሙት መንፈስ ማለት በልቦናችንና በአእምሮአችን ዝሙትን በማሰብና ሲከፋም ወደ መፈጸም የሚያደርሰንና ከፈጣሪ የሚያጣላን እርኩስ መንፈስ ነው፡፡ የዝሙት መንፈስ በተለይ ባላገቡ ወጣቶች ላይ ይጸናል፡፡ አሁን አሁን ግን ያገቡትም የዚህ መንፈስ ተጠቂ እየሆኑ ነው፡፡
ወዳጆቼ ወጣቱ በዝሙት መንፈስ በተለያየ መንገድ ሊጠቃ ይችላል፡፡ አንዱ ተፈጥሮአችንን በመጠቀም ነው፡፡ ይህ ማለት ወደ እሳትነት ዕድሜ ክልል በምንገባበት ጊዜ የሥጋ ባህሪያችንን በመጠቀም የዝሙት መንፈስ ሊጠናወተን ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው ወንዶች ዓይናችን ወደ ሴቶች፣ ሴቶችም አይናችን ወደ ወንዶች ማማተር፣ በልዩ ፈቃድ መመኘትና ልባችንም ፈቃደ ሥጋን ለመፈጸም በሚከጅልበት ሰዓት ውሻ በቀደደው አንዲሉ የዝሙት መንፈስ ወደ ውስጣችን ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ውስጣችን ገብቶ ለዓመታት ከተቀመጠ በኋላ በተደጋጋሚ ቤተ-ክርስትያን ለመሄድ በተዘጋጀንበት ጊዜና በሱባኤ ላይ ፈተናውን በግልፅ ይጀምራል፡፡ ሳናውቅ በድብቅ ገየባው የዝሙት መንፈስ በግልጽ ይፈትነናል፡፡
ሌላው በዓለማዊ ሕይወት በምንኖርበት ጊዜ የተለያዩ ዝሙት ተስቃሽ ፊልሞችን በምንመለከትበትና መጽሐፍቶችን በምናነብበት ጊዜ መንፈሱ ሳናውቀው ወደ ውስጣችን ይገባና፤ በኋላ ሁሉን ትተን በመንፈሳዊነት ወደ ቤተ-ክርስትያን መገስገስ ስንጀምር በሕልመ ሌሊት (በዝንየት) በመፈተን ከቤተ-ክርስትያን ያስቀረናል፣ በፈተናም ያስመርረናል፡፡ ውድ አንባቢያን ፊልም ማየትና መጽሐፍት ማንበብ ኃጢኃት ባይሆንም የምናየውን ፊልምና የምናነበውን መጽሐፍ መምረጥ ይገባል፡፡ ጸያፍ እና ሥጋና ነፍስን የሚያሳድፍ ፊልም/ቨዲዮ/ ከሆነ ድብን ያለ ኃጢአት ነው፡፡
3ኛ/ ስንታበይ
አንዳንድ ጊዜ ምናልባት የዝሙት ሐሳብ ሲጠፋልን እራሳችንን እንደ ንፁህ በምንቆጥርበት ጊዜ ወይም ወደ ብቃት ደረጃ የደረስን አድርገን ስናስብ፤ ይህ መታበይ ነውና በትንሹ ጽድቃችን እራሳችንን ከፍ እንዳናደርግና ለራሳችን ልዩ የጽድቅ ቦታ እንዳንሰጥ እግዚአብሔር ሊገስጽን እንዲህ አይነት ፈተና ይመጣብናል፡፡
በመታበይ ውስጥ ያለን ሰዎች ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) በሚመታን ሰዓት የኃጢአተኝነትና የመርከስ ስሜት ስለሚሰማን ራሳችንን ዝቅ በማድረግ ስለምንወቅስ እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነት መንፈስ እንዲኖረን ስለሚሻ በዚህ መልኩ ሊያስተምረን ይችላል፡፡
በአንድ ወቅት ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችን በሰውነቱ ያደርገው የነበረውን ቅንዋት እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ ጌታም እጅግ ይወደው ስለነበረ ሰጠው፡፡ ዮሐንስም የጌታን ቅንዋት በሰውነቱ ቢያደርገው ፍፁም ድንግልና እንደ መላእክት ንፁህነት ተሰማው፡፡ ጌታም የተሰማውንና ያሰበውን ስላወቀ ወዳጄ ዮሐንስ ሆይ ‹‹ንጹህ ማነው?›› አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹ጌታ ሆይ! አንተ እና እኔ›› አለ፡፡
ጌታም ወዳጁ ዮሐንስ በመታበይ እንዳይወድቅበት ስላሰበ ሌሊት በሕልመ ሌሊት ፈተነው፡፡ ጠዋት ሲያገኘው ‹‹አሁንስ ንፁህ ማነው?›› አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹ጌታ ሆይ ንፁህ አንተ ብቻ ነህ’’ አለው፡፡ ዮሐንስም ሰው ምንም ቢመረጥ ንፅህና የባህሪ ገንዘቡ ለጌታችን ብቻ እንደሆነ በመመስከር እራሱን ዝቅ በማድረግ ተምሮበታል፡፡
ከዝሙት አጋንንት እና ከዝንየት በተጨማሪ በሕልመ ሌሊት የሚፈትነን አጋንንት የትኛው ነው?
ሀ/ ሴት ዓይነ ጥላ
ተወዳጆች ሆይ ሴት ዓይነ ጥላ ያለችበት ወንድ በሕልመ ሌሊት መከራውን ነው የምታበላው፡፡ ዓይነ ጥላዋ ስለምትቀናና ስለምትወደው ሌሊት እየመጣች በተኛበት ትገናኘዋለች፡፡ እጅግ የሚያጸይፈው ደግሞ ሴት ዓይነ ጥላ ወንድን የምትፈትነው በእናቱ፣በእህቱ በአክስቱ፣በዘመዱ፣በሥራ ባልደረባው፣በሚያውቃት እና በማያውቃት ሴት እየተመሰለች በሕልመ ሌሊት ትመታዋላች፡፡ አንዳንዱ ላይ ባስ ስትል በእንስሳት እየተመሰለች ትፈትነዋለች፡፡
ብዙ ወንዶች ሌሊት በተኙበት ከሴት ጋር ገሃድ የሚመስል ግንኙነት ሲፈጽሙ ቀለል ስለሚያደርጉት፤ ባስ ካለም ፈተና እንጂ ሴት ዓይነ ጥላ መሆንዋን አያውቁም፡፡ ዓይነ ጥላዋ ወንድን በሴት አምሳል እየመጣች ሁሌ የምትፈትነው ከሆነ የችግሩ ሰለባ የሆነው ሰው በመንፈሳዊ ሕይወቱ ታዝለዋለች፣ ጸሎት ታስተወዋለች፣ ከቤተ-ክርስትያን፣ ከጸበል፣ ከንግሥ ታስቀረዋለች፣ በሆነው ባልሆነው ዘሩን በማፍሰስ ዘሩን ደካማ ታደግበታለች፡፡ በዚህም የመውለድ እድሉን ታጠብበታለች ሲብስም ልጅ እንዳይወልድ ታደርገዋለች፣ለመካንነት ትዳርገዋለች፡፡
ለ/ ወንድ ዓይነ ጥላ
ወንድ ዓይነ ጥላ ያለባቸው ወይም የሚያንዣብብባቸው ሴቶች በሕልመ ሌሊት ይመታሉ፡፡ የሴቶች ከወንዶች የሚለየውና የሚከፋው ዓይነ ጥላው እንደ ባል አድርጓቸው እጮኛና ትዳር እንዳይዙ ከማድረጉ ባሻገር ሌሊት እየመጣ በሚገናኛቸው ወቅት ዓይነ ጥላዊ መርዙን በማህጸናቸው ውስጥ በማስቀመጥ እንደ ጽንስ ሆኖ ሊቀመጥ መቻሉ ነው፡፡
በዚህም ሴቶቹ እጮኛ አይዙም፣ትዳር አይመሠርቱም ምናልባት ትዳር ቢይዙም ትዳራቸውን በተለያየ ምክንያት መበጥበጡ እንዳለ ሆኖ ማህጸናቸውን በመዝጋት ለልጅ አልባነት ሊዳርጋቸው ይችላል፡፡ ማህናቸውና አፍረታቸው ላይ በመቀመጥም የሩካቤ ፍላጎታቸውን በመግደል፣የሴትነት ስሜታቸውን በማጓደል ደመ ቀዝቃዛ ያደርጋቸዋል፡፡
ወዳጆቼ ወንድ ዓይነ ጥላው ልክ ወንዶቹን እንደሚፈትነው ሁሉ ሴቶቹንም በአባታቸው፣በወንድማቸው፣በአጎታቸው፣በቅርብ ዘመዳቸው፣በሚያውቁትና በማያውቁት ሰው እየተመሰለ ይገናኛቸዋል፡፡ ዓይነ ጥላውም ይህንን ልምድ ያደርገውና ሴቶቹን የሌሊት መጠቀሚያው ያደርጋቸዋል፡፡
ዓይነ ጥላው አንዳንዶቹን ገና ብቅ ሳይሉ፣ምኑንም ሳይለዩ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ይገናኛቸዋል፡፡ ሌሎቹን ደግሞ ለአቅመ ሄዋን ሲደርሱ መገናኘት ይጀምራል፡፡ ሲብስበት ካገቡ በኃላ ባል እያላቸው እየመጣ ይገናኛቸዋል፡፡ አላፍር ሲል ደግሞ እድሜ ሲገፋ፣ስሜት ሲጠፋ እየመጣ ይገናኛቸዋል፡፡ በዚህም ለሕልመ ሌሊት ይዳርጋቸዋል፡፡
ሐ/ ሴት ዛር
ሴት ዛር ያለችበት ወንድ ልክ እንደ ዓይነ ጥላው ሁሉ ሌሊት እየመጣች ወንዱን ትገናኘዋለች፡፡ ሴት ዛር ከዓይነ ጥላ የሚያከፋት ምንም ሴት ዛር ብትሆን ቀኒታ ስለሆነች ጾታ አትመርጥም፡፡ ወንዱን ለሕልመ ሌሊት እና ለሩካቤ ሥጋ ስንፈት ትዳርጋለች፡፡ ሴቶችን ደግሞ ሌሊት እየመጣች በመደበት ከባላቸው ጋር ሩካባቤ እንዳይፈጽሙ፣በባላቸው ዘንድ እንዳይወደዱ፣እንዲጠሉ፣ለሩካቤ ሥጋ መስእብ እንዳይኖራቸው ታደርጋለች፡፡
ዓይነ ጥላ በተለይ ሴት ዛር ያለችበት ወንድ መንፈሷ የሕልመ ሌሊት ሰለባ ከማድረጓም ባሻገር አካላዊ እና ስሜታዊ ጉዳት ታደርስበታለች፡፡ ይህም ወንዱ እስኪቱ/ብልቱ/ ለግንኙነት ዝግጁ እንዳይሆንና እስኪቱ እየተሸበሸበ ወደ ፍሬው ማህደር እንዲገባ ታደርጋለች፡፡ በቀላሉ እስኪቱን ታመነምናለች፡፡
መ/ ወንድ ዛር
ወንድ ዛር ያለባት ሴት ልክ እንደ ወንድ ዓይነ ጥላ ሁሉ ሴቷን ሌሊት እየመጣ ይገናኛታል፡፡ አንድ ሴት ሌሊት እየመጣ የሚገናኛት ወንድ ዓይነ ጥላ ይሁን ሴት ዓይነ ጥላ በምን ትለያለች ካልን ወንድ ዛር ከሆነ ሁሉም በሕልሟ ያለ ፈቃድዋ በግድ እያስገደደ እያስፈራራ ነው የሚገናኛት፡፡ የማታውቀው ኃይለኛ ወንድ በግድ ሲገናኛት ታያለች፡፡
የወንድ ዛር ከዓይነ ጥላው የሚከፋው ሴቷን እንደ ሕጋዊ ባል አድርጎ ማስቀመጥ፣ አብሯት ሌሊት በሕልሟ በመማገጥ መኖር ነው ዓላማው፡፡ ወንድ ዛር ያለባቸው ሴቶችም እጮኛ አይዙም፣ ትዳር አይመሠርቱም፣ ትዳር ቢይዙም ዛሩ ማሕፀናቸው ላይ ቁጭ ብሎ ልጅ እንዳይወልዱ ያደርጋል፡፡ ቢያረግዙም ጽንሱን በደም በመምታት ሊያስቀርድ ይችላል፡፡ እንዲሁም ዛሩ አፍረታቸው ላይ በመቀመጥ፣ ስሜት ቀስቃሽ ገላቸው ላይ በመቆናጠጥ ስሜት አልባ ያደርጋቸዋል፡፡ ሩካቤ ሥጋ ቢፈጽሙም ምንም ስሜት እና ደስታ የላቸውም፡፡
ወዳጆቼ በአንድም በሌላ ከዝሙት አጋንንት ሌላ ሴት ዓይነ ጥላ፣ ወንድ ዓይነ ጥላ፣ ሴት ዛር፣ ወንድ ዛር ካለብን የሕልመ ሌሊት ሰለባ ነው የምንሆነው፡፡ እነዚህ አጋንንት በሥጋዊም በመንፈሳዊም ሕይወታችን የሚያደርሱብን የሕይወት መቃወስ እንዳለ ሆኖ ለሕልመ ሌሊት ይዳርጉናል፡፡ ወገኖቼ ሕልመ-ሌሊት (ዝንየት) በተደጋጋሚ ሲፈትነን እግዚአብሔር እንደተወን ቤተ-ክርስትያን እንዳንገባ፣ እንዳልተፈቀደልን መቁጠር የለብንም፡፡ ይልቁን ፈተና እንደሆነ አውቀን አጋንንቱን ልንዋጋ ይገባናል፡፡
ተወዳጆች ሆይ ሱባኤ ስንገባ ወንድ ሴት ሳይል በሕልመ ሌሊት ምናልባት የሚፈትነን አጋንንት ስለሚኖር እረሳችንን ለፈተና ዝግጁ አድርገን ልንጀምር እንጂ በአጋንንት ፈተና ልንደናበር አይገባል፡፡
❤ ?
1ኛ/ ጸሎት
ሕልመ ሌሊት የሚያስቸግረን ከሆነ ማታ የእለት ውዳሴ ማርያም ከበረታን ከመዝሙር ዘጠና ጋር ጸልየን መተኛት፡፡ እመቤታችንን የዝንየት አጋንንቱን እንድታስርልን እንድታርቅልን መማጸን፡፡ ያኔ በሌሊት በተቃራኒ ጾታ እየተመሰለ የሚፈትነን የሕልመ ሌሊት አጋንንት (ዝንየት) ሲርቀን በሰላም መኖር እንጀምራለን፡፡ ወዳጆቼ ብርቱ ጸሎት እንኳን ከሕልመ ሌሊት ከገሃነመ እሳት ይታደገናልና በርትተን እንጸልይ፡፡ ማታ ማታ ውዳሴ ማርያም፣አርጋኖን የቻልነውን ያህል ብንጸልይ የእመቤታችን ጥበቃ እናገኛለን፡፡
2ኛ/ ሕልመ ሌሊት እንደመታን ተመልሶ አለመተኛት
ብዙዎቻችን ሕልመ ሌሊት ሲመታን ተስፋ በመቁረጥ ተመልሰን በዛው እንተኛለን፡፡ ይሄ ድርጊታችን አጋንንቱን ከማስደሰቱም በላይ ለነገ የልብ ልብ ይሰጠዋል፡፡ እኛ በሕልመ ሌሊት ምክንያት ጸሎቱን ትተን ‹‹ጠዋት ታጥቤ እጸልያለሁ›› በሚል ስንፍና ከተኛን አጋንንቱ እየደጋገመ እየመታን ሕልመ ሌሊቱን ጸሎት ለማስታጎያ ያደርግብናል፡፡
ስለዚህ ሕልመ ሌሊት እንደ መታን ፈጥነን በመነሳት ከቻልን ሰውነታችንን መታጠብ ካልቻልን አንቀጸ ሥጋችንን በመታጣብ ጸሎታችንን መጸለይ፡፡ ወዳጆቼ ሕልመ ሌሊት እንደ መታን ተነስተን ታጥበን በመጸለያችን የነገ የአጋንንቱን ውጊያ በር እንዘጋበታለን፡፡ አጋንንቱ በሕልመ ሌሊት የሚመታን አንድም እንዳንጸልይ ስለሆነ እኛ ደግሞ በተቃራኒ ከጸለይን አጋንንቱ ይርቀናል፡፡
3ኛ/ ማታ ውኃ አብዝቶ አለመጠጣት
ሕልመ ሌሊትን ለማስታገስ አንዱ መፍትሔ ማታ ውኃ አብዝቶ አለመጠጣት ነው፡፡ ይህንን ከመጻሕፍተ መነኮሳት ሁለተኛው የሆነው ፊልክስዮስ ‹‹አካልን የሚያደርቅ፤ከሕልመ ሌሊት፣ከዘር መፍሰስ የሚከለክል፤በመዓልት ኃልዮ ኃጢአትን የሚያጠፋ እንደ ውኃ ጥም የለም፡፡ ምንም ቢጾሙ፣ምንም ከምግብ ቢያከፍሉ አብዝቶ ውኃ ከጠጣ አይጠቅምም፡፡ ምነዋ ትለኝ እንደ ሆነ ሆዱ ቂብ ትላለች›› /ፊልክ.ክፍል 3 ተስእ 38/
ውኃ ማታ አብዝቶ መጠጣት ዘር በቀላሉ እንዲፈስ ያደርጋል፡፡ አባቶቻችን በሕጋዊ ጋብቻ ያሉትን ባለ ትዳሮች ‹‹ሩካቤ ሥጋ ከመፈጸማቸው ከ30 ደቂቃ በፊት ንጹህ ውኃ ጠጡ›› የሚሉት በግንኙነት ጊዜ በሰውነት በቂ ውኃ ካላ የወንድ ዘር በቀላሉ ወደ ሴቷ ማህፀን ስለሚደርስ ነው፡፡ ውኃ ለወንድ ዘር ተሸካሚ ነው፡፡ ውኃው ነው የወንድን ዘር እንደ መርከብ በመሸከም ከማህፀን የሚያደርሰው፡፡ ስለዚህ ማታ ማታ ውኃ አብዝቶ አለመጠጣት ትኩስ ነገርም አለማዘውተር ይመረጣል፡፡
4ኛ መስገድ
ሕልመ ሌሊት አዘውትሮ የሚፈታተነን ከሆነ ስግድት ላይ መበርታት፡፡ በተለይ ማታ ከመተኛታችን በፊት እራሳችንን በስግደት ቀጥቅጠን መተኛት፡፡ በስግደት የደከመ ሰውነት ላይ አጋንንት የበላይነት አይኖረውም፡፡ ስግደት ከእነዚህ ዓይነት አጋንንታዊ ጾር የምንርቅበት እና መፍትሔ የምናገኝበት ስለሆነ መቼም ስግደት ባይሆንልንም መስገድ መልመድ ይገባናል፡፡
5ኛ/ መጠንቀቅ እና ማማከር
ተወዳጆች ሆይ እራሳችንን ለፍትወት እና ለዝሙት ከሚያጋልጡን ነገሮች የምንርቅ ከሆነ አጋንንቱ በእኛው ስህተት ለሕልመ ሌሊት አይዳርገንም፡፡ እንዲሁም ፈተናው ሲደጋገምብን ሲበረታብን አባቶችን በግል በመፍትሔው ዙርያ ማመከርና የሚሉንን መስማት እና መተግበር፡፡
ወዳጆቼ አጋንንት ወንድ ሴት ሳይል በሕልመ ሌሊት መፈተኑን አይተውም፡፡ ስለዚህ እኛ በጾም፣በጸሎት በስግደት መዋጋቱን ልንተው አይገባም፡፡
‹‹ከእመቤታችን በጸሎት መልስ የምናገኝባቸው ጠቃሚ መንገዶች›› ከሚለው መጽሐፌ ተወስዶ ብዙ አዳዲስ ሐሳቦች ተጨምሮበት ተጻፈ፡፡
ነሐሴ/1/15 ዓ.ም
አዲስ አበባ