
17/08/2025
አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፈ
ሴሎም ሚዲያ/ ለንደን/ 11 ነሐሴ 17/25
አርቲስት ደበበ እሸቱ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል።
አርቲስት ደበበ እሸቱ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን÷ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም እና በጋዜጠኝነት ሙያ በርካታ ሥራዎችን ለአድማጭ ተመልካች አቅርቧል፡፡
ተዋናይ፣ ኮሜዲያን እና አዘጋጅ ሆኖ ለረጅም ዓመታት ያገለገለው አርቲስቱ ÷ በቴአትር መድረኮች በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሥራዎችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡
አርቲስት ደበበ በሀገር ፍቅርና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (በአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) መድረክ ላይ ለበርካታ ዓመታት በተዋናይነትና በአዘጋጅነት አገልግሏል።
አርቲስት ደበበ መጀመሪያ በቴአትር መድረክ የታየው በመንግስቱ ለማ ያላቻ ጋብቻ ሲሆን÷ በመቀጠልም በሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የተለያዩ ሥራዎችን አቅርቧል፡፡
አርቲስቱ ከተሳተፈባቸው ሥራዎች መካከል ያላቻ ጋብቻ፣ ሮሚዮና ዡልየት፣ ጠልፎ በኪሴ፣ ዳንዴው ጨቡዴ ፣ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ፣ ኦቴሎ፣ አንድ ዓመት ከአንድ ቀን፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ በቀይካባ ስውር ደባ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ የወፍ ጎጆ ፣ የቬኒሱ ነጋዴ ፣ ማዕበል እና ሌሎች ይገኙበታል፡፡