08/08/2025
ጉራያ ሓለፎም : ቀይ ባህር የቀጠፋት አበባ🌹😥
እውነተኛ ታሪክ:‼️👇
በራያ ምድር ፣ ራያ አላማጣ ወረዳ ልዩ ስሙ ዳዩ በሚባል መንደር ነው የተወለደችው። ለቤተሰቦቿ የመጀመርያ ልጅ ስትሆን 3 ታናናሽ እህትና ወንድሞችም ነበሯት።
ጠይም ፣ ቀጭን ፣ ቁመቷ ዘለግ ያለች የ 15 አመት አፍላ ልጃገረድ ነበረች። ቅቤ የጠገበው ዞማ ፀጉሯ ንፋስ ዘንፈል ዘንፈል ሲያደርገው ክረምት ያለመለመው የመስከረም እሸት ነበር የምትመስለው። እንደ አሎሎ ከብለል ከብለል የሚሉት ትልልቅ አይኖቿ ፣ የቆላ ፀሀይ ያልቀየረው ደም ግባቷ ፣ ከንፈሯን ከፈት ስታደርግ ብልጭ የሚሉት ድርድር ጉራማይሌ ጥርሶቿ ፣ለመንካት እንኳ የሚያሳሳው ለስላሳ ገላዋን ለተመለከተ ፣ በችግርና በድህነት የኖረች ለፍቶ አዳሪ ፣ እናቷን አጋዥ የገበሬ ልጅ ሳትሆን ፣ ቤተመንግስት ተሞላቃ ያደገች የንጉስ ልጅ ነበር የምትመስለው። ስታሳሳ! እምቡጥ አበባ🌹
ቤተሰቦቿ በእርሻ ስራ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች ሲሆኑ የኑሮ ደረጃቸው ከፍተኛ ድህነት ያለበት ነበር። ይሁን እንጂ የተረጋጋ ያገኛትን አመስግኖ የሚኖር ሳቅ ጨዋታ የማይለይበት ቤት ነበር።
እንደ ሁሉም የራያ ልጃገረዶች ከብቶችን እየጠበቀች ፣ ከዚያም ባልጠነከረ ወገቧ ውሀ ተሸክማ ፣ ለናቷ ቤቷን ጠራርጋ ቡና የምታፈላ ፣ ወፍጮ እህል አስፈጭታ ፣ ላአርሶአደሩ አባቷ ምሳ አመላልሳ ፣ እርሻ ጎልጉላ ፣ እንጨት ለቅማ፣ ታናናሾቿን አዝላ ፣ ከእናቷ ጋር ገበያ ሸቀጥ ሸምታ የምትገባ ታታሪ ልጅ ነበረች።ጉራያ!
በአከባቢውና በቤተሰቧ በጣም ተወዳጅ ልጅ ነበረች። በጣም ታታሪ ከመሆኗ የተነሳ ከሁሉም ቀድማ ተነስታ ቀኑን ሙሉ ያለ እረፍት ላይታች እያለች ውላ ማታ ከሁሉ ኋላ ነበር የምትተኛው።
የመንደሩ ሰዎችም ይህን አይተው:
"ትርእያ ደቃቕ ልባ ግን ህንዲ ከረን!" ነበር የሚሏት።
(ትንሽ ነች ልቧ ግን እንደተራራ ትልቅ ነው!)
እውነት ነው ! ጉራያ ህልሟ ሁሌም ቤተሰቦቿን ማገዝ፣ እህት ወንድሞቿን መንከባከብ እናቷን ማስደሰት ብቻ ነበር። የሷ ደስታ እናቷን ማሳረፍ ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን ታድያ ከጓደኛዋ ጋር ውሀ ለመቅዳት እየሄዱ "ስዑዲ ደይንኸድ" (ሳኡዲ አረብያ ለምን አንሄድም?) አለቻት ። እዛ ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፈልበት ስራ እንደምታገኝ በዚህም ቤተሰቦቿን እንደምትረዳ ትነግራታለች። እሷም በንግግሯ ተሳበች ፣ በቅፅበት ለአባቷ ጥንድ በሬዎችና የወተት ላሞች ገዝታ ቤታቸው እምቧ እያሉ ሲራረራጡ ታያት ፣ የጎደለው ጎተራቸው እህል ሞላ ፣ባዶ የሆነው የእናቷ አንገት ወርቅ በወርቅ ሆነላት ፣ ልትፈርስ ትንሽ የቀራት ጎጆ ቤታችቸው ቪላ ቤት ሆና ቆርቆሮው አብረቀረቀባት፣ ከምንም በላይ የእናቷን እረፍት ፈለገች ፣ ይህን ስታልም ድንገት ፊቷ በራ የወደፊቱን አስበው ትልልቅ አይኖቿ ተስፋን ሰንቀው ይባስ ጎላ ጎላ ብለው ታዩ ፣ ዙርያዋን ቃኘች አላቅማማችም ወድያውኑ ተስማማች።
በማለዳው እንደወትሮ ሌሊት ተነሳች ፣ ባሁኑ ግን ስራ ላይ ሽርጉድ ለማለት አልነበረም እንደውም፣ ይቺ ትንሽዬ ልጅ ሩቅ ነበር መንገዷ። አገር አቋርጣ ፣ባህር አቋርጣ ፣ ድንበር አቋርጣ ወደ የማታውቀው ሀገር ለመሄድ ተነሳች።
አላማጣ ከተማ በድብቅ የገቡ ከተለያዩ ቦታ የሚመጡ ልጆች እስኪሰበሰቡ ሳምንት ቆይታ፣ ከመሰሎቿ ጋር በአንዲት ሚኒባስ ትንፋሽ በሚያሳጥር መጨናነቅ ታጭቀው ከአለማጣ አዲስ አበባ ከዚያም በሱማሌ ክልል አድርገው ቦሳሶ ጠረፍ ወስደው አስቀመጧቸው።
ከአንድ ቀን ኋላም ደላላ መጥቶ ወደ ቤተሰብ ደውለው ገንዘብ እንዲያስልኩ ነገሯቸው። ይህኔ ይቺ ለጋ ቀጫጫዋ፣ ተስፈኛዋ ትንሿ ጉራያ ደነገጠች!! ስትመጣ ስርታ እንደምትከፍል ነበር የተነገራት።
ለካስ ውሸት ነበር!
ጉራያ ተጨነቀች ! እንቢ እንዳትል ሰው ሀገር ነው ያለችው። እንዳትደውል ደግሞ ፣ ድንገት በሌሊት ጥላቸው የሄደቻቸውን የእናትና አባቷን ድምፅ መስማት አስፈራት። ከየትስ ያመጣሉ ብላ በልቧ አሰበች። ኑሯቸውን ልለውጥ ብላ ተነስታ የሄደች ልጅ ከሌላቸው ላይ ላኩልኝ ማለት አሳቀቃት። እነዛ አሎሎ የሚመስሉት አይኖቿ እስኪቀሉ አለቀሰች። ደላሎቹን "አረ ቤተሰበይ ዓቅሚ የውሎምይ" (ቤተሰቦቼ አቅም የላቸውም) ብላ ተንሰቀሰቀች! እነሱ ግን አልራሩላትም ። ጨከኑ!!
በመጨረሻም ጓደኞቿ "አብዚ በፅሕኺ ደማ ትምለሲ ኾይኑ ፣ አሕና ደውልና እንሀና ፣ እስኺ ለ ደውሊ። ዋላ ገንዘብ ሸይጦም ይልአኹልኺ፣ ደሓር ሰርሕኺ ድአም ትዓድይሎም።"
(እዚህ ደርሰሽ እንዴት ትመለሻለሽ ፣ እኛም ደውለናል፣ አንቺም ደውይና ንብረት ሽጠውም ቢሆን ይላኩልሽ ፣ ሰርተሽ እዳቸውን ትከፍይላቸዋለሽ። ) ሲሏት እሷም የግዷን ደወለች።
አባትና እናቷ ስልክ ስሌለላቸው ወደ አጎቷ ደውላ ሁኔታውን ነገረችው። እሱም ቤተሰብ ተጨንቆ እንዳለና እያፈለጓት እንደሆነ ነገራት። ከዚያም እናቷን ወይም አባቷን እንዲያገናኛት ጠይቃ እሱም ቅርብ ስለነበር ወደ ቤታቸው ሄደ።
"ሄሎ አደዋይ"😥 (ሄሎ እናቴ) አለች ። የእንባ ሳግ እየተናነቃት አንጀት በሚበላ ድምፅ። እናቷም ወድያውኑ ለቅሶ በለቅሶ ሆነች። ተንሰቀሰቀች!
አጎትየውም
" ዋእ ታይ ይኡ ትገብርለኽዮ ቆልዓ አብ ዓድማታ ኮይአ ድንሀ"
( ምንድነው የምታደርጊው ይቺ ልጅ በሰው አገር እኮ ነው ያለችው) ብሎ ተቆጣት!
እናቷም
" ጉራያዋይ አትዮ ታገብረኪ ? ፣ ሀምዚ ድኡ ድግበር ?፣ አነ አደዋኺ አያሕዝነክይ ዶ? ምንም ደይትናገርኺ ሙልቕ ብኺ ትኸዲ።"😥
(ጉራያዋ ምን አደረኩሽ? ፣ እንዲህ ይደረጋል? ፣ እኔ እናትሽ አላሳዝንሽም ? ምንም ሳትናገሪ ውልቅ ብለሽ ትሄጃለሽ ) አለቻት በእንባ ተሞልታ እያለቀሰች።
ጉራያም ቀበል አድርጋ
" አደየ አይትቀየምኒ፣ አነ ድኻትኹም ደይሓሰብኹ ቃርየ አይኾነይ እኮ እንድሕር ነግረኩም አይትሰዱንይ ብለ ይኡ። አነ ለለ ድኣኻትኩም ካድንሀኹሞ ኽፍአት እንድሕር ደያውፃእኹ ህራስ የብለይይ " አለቻት።😥
(እናቴ አትቀየሚኝ ፣ ለናንተ ሳላስብ ቀርቼ አይደለም። ብነግራችሁ አትሰዱኝም ብዬ ነው፣ እኔ ደግሞ እናንተን ከችግር ሳላወጣ እንቅልፍ የለኝም) አለቻት አሁንም እንባ አየተናነቃት ግን ጠንካራ ለመምሰል እየሞከረች።
እናቷም
"በሊ ታማ ክግበር ዋ ሳንትም ንልእኸልኪ ትመለሲ ዳብዓድኺ"
(ምን ይደረግ ታዳ ፣ አሁን ብር ልላክልሽና ወደ ቤትሽ ተመለሽ) አለቻት ተስፋ በማድረግ።
ጉራያም
" አይ አደዋይ ደጉም አብዚ በፅሐ አይምለስይ ዋ፣ ደላላኦም ገንዘብ ላበሉኒ ይኡ ስደዱለይ"
( አይ እናቴ እዚህ ደርሼ አልመለስም። ደላላዎቹ ብር ስለጠየቁኝ ላኩልኝ) አለቻት።
እናቷም
"እሺ አየኺ ይምፃእ ዋ ክድውለልኺ ይአ"
(እሺ አባትሽ ሲመጣስ እደውላለሁ) አለቻት።
ስልኩ ተዘጋ.............
አባቷ ከተማ እሷን ፍለጋ ቆይቶ ወደቤቱ ሲመጣ ፣ የሆነውን ነገሩት ። እሱም ገንዘብ ለመበደር ቢጠይቅም የተወሰነ ነበር ያገኘው። ሳይወድ ራሱ ያሳደገውን የሚወደውን በሬ ለሚያውቀው ሰው በርካሽ ሽጦ ላከላት።
አባቷም ደውሎ
" ኩለ ድገበርኽዮ ኳ አይግብርቶይ ዋ እንድሕር እንቢ በኽማ ምቸኣል ዳዩ ባዕሉ ይሓልኺ"
(ኩለ ያደረግሽው እንኳ ጥሩ አይደለምና ፣እምቢ ካልሽማ ምንይደረግ ታዳ ፣ የዳዩ ሚካኤል ይጠብቅሽ ) አላት።
እሷም
" አይትቀየመኒ አየዋ ፣ ዕዳኻለ ቶለ ብለ ክዓድየልኻ ይአ አይዘኻ ፣ ድኹሎም አሕዋተይ ለ ሰላም በሎም። አዮ ባሕሪ ክሸግር ስለድኾነ ስልኪ አይሰርሕይ ፣ ብትሻገርኹ ባዕለይ ክድውለልኹም ይአ ቻው"
(አባቴ አትቀየመኝ ብድርህንም ቶሎ እከፍልልሀለሁ። ለሁሉም ወንድሞቼ ሰላም በልልኝ። አሁን ባህር ልሻገር ስለሆነ ስልኬ አይሰራም። እንደተሻገርኩ ራሴ እደውላለሁ።) ብላ ተሰናበተችው። ባሁኑ አላለቀሰችም ቆርጣለች!!
ጉዞ ተጀመረ ፣ ቀይ ባህር! ወለል ያለ ሜዳ ይመስል ትኩር ብላ አየችው። በህይወት ዘመኗ ከትንሽየ ኩሬ እና የክረምት ወራጅ ወንዝ ውጪ ይህን ያህል በንፋስ ዥዋ ዥዌ የሚጫወት ደስ የሚል ግን የሚያስፈራ ውሀ ስታይ ለመጀመርያ ጊዜዋ ቢሆንም ምንም አልፈራችም። ለሷ ይህ ከቤተሰቦቿ ችግር አንፃር ምንም መስሎ ታያት።
አሮጌ ትንሽ ሞተር የተገጠመላት አንስተኛ ጀልባ ርርርርር እያለሽ ወደ ዳርቻው ተጠጋች ። ጉራያ ገረማት! "እዛ ደይአ ጀልባ ትብሀል?" (ይህች ናት ጀልባ የምትባለው?) ብላ ለጓደኛዋ ቀስ ብላ ጠየቀቻት ። እያጣደፏቸው ስለነበር አልመለሰችላትም።
በዛች ትንሽ ጀልባ ከ 150 ሰው በላይ እጅግ በማይመች ሁኔታ እንደ ማገዶ እንጨት ተደራርቦ ተጫነ። ማንም አያማርርም ፣ በቃ! ሞልቷል ማለት አትችልም። ለነሱ አንተ ገንዘብ የሚገኝብህ ተራ ጭነት ብቻ ነህ ። ያንተ ህይወት በጀልባዋ ዘዋሪዎች እጅ ላይ ነው አንገትህን ቀብረህ ቁጭ ከማለት ውጭ ምርጫ የለህም።
ጉዞ ተጀመረ በዛ የሰሃራ ሀሩር ፀሀይ ምግብ የለም ፣ ውሀ የለም፣ በዚህ መሀል የሚያስታውከው አለ። ጥም ርሀብ፣ ፣ ለመፀዳዳት እንኳ ፋታ አይሰጥህም ሽንትህ ቢመጣ እዛው ትሸናው እንደሆን እንጂ ማንም አይሰማህም ። እንዲሁም ማእበሉ የሚፈጥረው የጀልባዋ መንገራገጭ ተጨምሮ ያለው ሁኔታ ትንሽዬ ሲኦል በሉት።ገሀነም!!
በዚህ ሁሉ መሀል ቀጫጫዋ ጉራያም በሁለት ጎረምሳዎች መሀል ተቀርቅራ ፣ በውሀ ጥም ከንፈሯ ደርቆ ፣ በርሀብ አንጀቷ ተስቦ ፣ ያ ማራኪ ደም ግባቷ ገርጥቶ ፣ወጀቡ በሚፈጥረው ማእበል በቀዝቃዛው የቀይባህር ውሀ ሙሉሰውነቷን በስብሳ ዞማው ፀጉሯ ምስቅልቅል ብሏል። ፊቷ ላይ ግን ምንም ጭንቀት ፣ ፍርሀት ፣ መከፋት አይታይባትም። ለቤተሰቧ ስትል መጠንከርን መርጣለች ። የምትሰበር እትመስልም፣ ህልሟ ሩቅ ነው። የሚታያት ተስፋ ሰርቶ መለወጥ ፣ ቤተሰብ መደገፍ፣ የኑሮዋን መስመር ማቃናት ብቻ ነው። ትልቅ ህልም!!
ሆኖም ይህ ባህር የሕይወቷ ጉዞ መጨረሻ እንደነበር አታውቅም ።😥
ማእበል ተነሳ፣ ባህሩ ተቆጣ ጀልባዋም ተጨነቀች ። ውሀ ፣ ንፋስ ፣ ጩሀት ፣ ለቅሶ ...!!💔
አንድ በአንድ ሁሉም ወደ ጥልቁ ባህር ይሰምጥ ጀመር፣ ጉራያም በትንንሽ እጆቿ ትንሽ የጀልባዋ የእንጨት ቁራጭ ይዛለች ፣ በነዛ ውብ አይኖቿ ወደ ሰማይ ተመልከተች። የሚረዳት ያለ ይመስል ዙርያዋን በዝምታ አማተረች ።ግን የሚያድናት አንድም አልነበረም ። ቅዝቃዜው ሰውነቷን አደረቀው ፣ አቅም አጣች ፣ለስላሳ ገላዋ ደነዘዘ ፣እጆቿ ከዷት...
"አደደደደደደደዋይ"😥 (እናናናቴቴቴቴቴቴ) እያለች ብትጣራም ማእበሉ ድምጿን ዋጠው። ጉራያ ወደ ጥልቁ ባህር ጠለቀች፣ ዝምታ!💔
ያቺ ለማየት የምታሳሳ አበባ ፣ የሰፈሩ ሰው አይን ማረፍያ። ያቺ በዳዩ ገጠራማ መንደር መስክ ውስጥ ስትቦርቅ የነበረችው ፣ ያቺ እናቷ ትንሰፈሰፍላት የነበረችው ፣ ያቺ ዘወትር አባቷን ስታግዝ "ትባረኪ ጓለይ " (ተባረኪ ልጄ) የተባለችው ፣ ያቺ ባልጠነከረው ጀርባዋ እህት ወንድሞቿን አዝላ እሽሩሩ ያለችው ፣ያቺ ትልቅ ተስፋ የነበራት ልጅ ጸጥ አለች።
ያን ሁላ መከራ አልፋ በዚያ ምህረትን በማያውቀው ጨካኝ ባህር ውስጥ ተቀበረች።አረፈች!!😥
መርዶ መጣ ያቺ በሌሊት ማንም ሳያያት የወጣቸው ልጅ ላትመለስ አሸለበች።
"ጉራያኮ ሞይታ"😭 (ልጅሽ ሞታለች) ስትባል እናት የሰማችውን ማመን አልፈለገችም። ራሷን ስታ ተዝለፍልፋ ወደቀች። ትንሹም ትልቁም ያለቅሳል ቀዬው ሁሉ ዋይታ በዋይታ ሆነ። የሁሉ ልጅም አይደለች ጉራያ።
ለእርም እንዲሆን እንኳ ሬሳዋ አልተገኝም ፣ ከፀሎተ ፍትኋትና ለቅሶ ውጪ አስክሬኗ ቦርቃ ባደገጅበት መንደር በደብሯ ለማረፍ አልበቃም ። ይህ ሌላ ቁስል ነው።
ከዛን ቀን ኋላ እናቷ በድንጋጤ፣ የአይምሮ ህመምተኛ ሆነች። ዘወትር በሯ ደጃፍ ላይ ተቀምጣ እንዲህ እያለች ከማንጎራጎር ውጪ ምንም አትናገርም...
አቲ ሸገ እቲ ቃያሕ ብሪ፣
ጨክንኺ ዶ ትቃርይ አብ ባሕሪ ።😥
✅ "ጉራያ" ማለት "ጓልራያ" ማለት ሲሆን ፣ ትርጉሙ ደግሞ "የራያ ልጅ" ማለት ነው ። ስሙ እንደሚናገረው ይህ የአንዲት ጉራያ ታሪክ ብቻ አይደለም ። ይህ የብዙ ጉራያዎች የማያባራ ሰቆቃ ነው።
ህገወጥ ስደት ይቁም‼️ ሰላም ይንገስ‼️
Solomon Ayalew ✍️