
10/01/2025
36 ሰዎች ብቻ የሚኖሩባት ሀገር
በሀገሪቱ 36 ሰዎች እና አራት ውሾች ብቻ ይኖሩባታል። ባውግስተን ዋና ከተማዋ ናት።
የዓለማችን ትንሿ ሀገር የሞሊሲያ ሪፐብሊክ ጠባብ የቆዳ ስፋት ቢኖራትም ከሕዝቦቿ አንጻር ግን ሰፊ መሬት አላት።
ሕዝቦቿ ሞሊሲያን እንደ አንዲት ታዳጊ ሀገር ይቆጥራሉ። የራሷ መገበያያ ገንዘብ፣ የራሷ ሰማያዊ፣ ነጭ እና አረንጓዴ ቀለሞችን የያዘ ባንድራ እንዲሁም የሕዝብ መዝሙርም አላት።
ይህ ሁሉ እየሆነ የሚገኘው በዓለም ታላቋ ሀገር በአሜሪካ ውስጥ ነው። የሞሊሲያ ሪፐብሊክ በሀገረ አሜሪካ በኔቫዳ ግዛት ውስጥ ነው የምትገኘው።
የአሜሪካ መንግስትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት እንደ ሀገር እውቅና ባይሰጣትም ሞሊሲያ ግን እንቅስቃሴዋ ሁሉ እንደ አንዲት ነጻ እና ሉዓላዊ ሀገር ነው።
የአሜሪካን መገበያያ ዶላርን ሳይሆን የራሷን “ቫሎራ” የተሰኘ ገንዘብ ትጠቀማለች። ሕዝቦቿ እንግሊዝኛን እና ኢስፒሬናቶ ቋንቋዎችን ይናገራሉ።
የሞሊሲያ ሪፐብሊክ የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ መሳብ የቻለችም ሀገር ናት። በዓለም ላይ ካሉ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ሀገራት መካከል ሞሊሲያ አንዷ ስትሆን ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ምርት አላት።
ሆስፒታል እና አየር መንገድ ባይኖራትም የባሕር ኃይል፣ የባቡር ሀዲድ፣ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች፣ ባንክ፣ የፖስታ አገልግሎት፣ የየሬዲዮ ጣቢያ እና የራሷ ሰዓት አቆጣጠር ያላት ሀገር ናት።
ሞሊሲያን መጎብኘት የሚቻለው በዓመት ውስጥ ለአንድ ወር ብቻ ሲሆን እሱም ጥቅምት ወይም ሚያዚያ ወር ላይ ነው። ጎብኝዎች ወደ ሀገሪቱ ለመግባት ከሞሊሲያ መንግስት ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
ጎብኝዎች ፓስፖርታቸውን ለሀገሪቱ መንግስት ልከው ማህተም ካስመቱ በኃላ ወደ መጓዝ ይችላሉ።
ሞሊሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንጆቹ 1977 ስትመሰረት የቩልድስተይን ግራንድ ሪፐብሊክ በመባል ትታወቅ ነበር።
አሁን ላይ የሞሊሲያ ሪፐብሊክን የሚያስተዳድሯት ፕሬዝዳንት ግራንድ አድሚራል ኮሌኔል ኬቨን ባወ (ዶ/ር) ይባላሉ።