07/08/2025
ነሃሴ 1/2008 ዓ/ም ሲታወስ
ነሐሴ 1 ሌቱ ለንጋቱ ቦታውን አስረክቦ ዘወር አለ ንጋቱም ወገግ ማለት ሲጀምር የባህር ዳር ከተማ ህዝብም ከወንድ እስከ ሴት ከህፃን እስከ አዛውንት በየ ቀበሌው ተደራጅቶ እና ተቀናጅቶ ድምፁን ለማሰማት መፈክሩን ይዞ ባንዴራውን ለብሶ ከተለያየ አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ ሊገናኝ ቀጠሮ ወደያዘበት አዝዋ ሆቴል ፊትለፊት ሚሊኒየም አደባባይ አካባቢ ይተም ጀመር።
መንገዶች በህዝብ ማዕበል ተሞሉ መበደል መገደል ያንገሸገሻቸው ስርአቱ በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ እና በደል ልባቸውን የነካቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ፍትህ ለተገፋው አማራ በሚሉ መፈክሮች ታጅበው የከተማዋን ጎዳናወች አጥለቀለቁ።
ወልቃይት ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ ፣ አማራነት ወንጀል አይደለም ፣ አማራነት ይከበር፣ሞት ቢደገስልን እንኳን አንፈራም ፣ እምቢ እንደ በላይ እና ሌሎች መፍክሮችን በማንገብ ስርአት ባለው መልኩ ድፁን ማሰማት ቀጠለ።
ይህ ሰላማዊ ድምፅን የማሰማት ሂደት ምቾት ያልሰጣቸው #የብአዴን _ህውሃት_ኢህአዴግ_አመራሮች ስርጎ ገቦችን ሰልፉ ውስጥ አስገብተው "ከጎንደር ለሰልፉ የመጡ ወገኖቻችን አባይ ማዶ ላይ አታልፉም ተብለው ታግተዋል" የሚል የውሸት ወሬ ሰልፉ ላይ ነዙ፤ የባህር ዳር ህዝብም ማነው ወንድሜን ያቆመው፣ ማነው ደጀ ላይ ደሜን እንዳይገባ የሚከለክለው ብሎ ወደ አባይ ማዶ ተመመ።
ህዝቡ አባይ ማዶ ሲደርስ የጠበቀው መንገድ ተዘጋበት የተባለ ወገኑ ሳይሆን እርሱን ለመግደል እጃቸውን ቃታ ላይ ያደረጉ ምቹ ቦታ ይዘው የመሸጉ የብአዴን ህውሃት ኢህአደግ ነፍሰ ገዳይ ወታደሮች ነበሩ።
አባይ ማዶ ላይ ወንድምህ እንዳያልፍ ዘጉበት ብለው በውሸት ፕሮፖጋንዳ ነዝተው ወደ ማረጃው ቄራ ነድተው ያመጡት የብአዴን ሰርጎ ገብ ካድሬወች ህዝባችን ወደ ማረጃው ቀለበት ሲገባ ግማሹን እንዳያልፍ ድልድዩ ላይ ዘግተው ያለፈውን በጥይት አረር ያለ እርህራሄ ቆልተው ህፃን አዋቂ ሴት ወንድ ሳይሉ ገደሉ አቆሰሉ።
ህዝቡ ጥይት ካነገተው ቃታ ከሳበው ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ለማንነቱ ለነፃነቱ በጀግንነት ተዋድቋ፤ እየተኮሱበት ሳይሸሽ ከጎኑ ያለው እየወደቀ ሳይሸበር አምባገነኖችን እስከ መጨረሻው ታግሏል።
ነሃሴ 1/ 2008 ባህር ዳር ለማንነት ለነፃነት ለእኩልነት ብዙ ሩጠው ያልጠገቡ መፈክር ብቻ ያነገቡ ሰላማዊ ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ይዘው የተነሱ ልጆቿን በግፍ ያጣችበት ቀን ነው ፤ነሃሴ 1 የከተማዋ መንገዶች በደም ጎርፍ ታጥበዋል በወጣቶች አስከሬን ተሞልተዋል፤ ድምፅን በሰላማዊ መንገድ ያሰሙ ያለእርህርልሄ በግፍ ተጨፍጭፈዋል።
ይህ ቀን መቸም የማንረሳው ሁሌም የምናወሳው ለትግሉ ዋጋ የከፈሉትን አንስተን አስታውሰን ሰማእትነታቸውን የምንዘክርበት ለከፈሉት ዋጋ ክብር የምንሰጥበት ቀን ነው።
ክብር ለነፃነት ለማንነት ለእኩልነት ለታገሉ ዋጋ ለከፈሉ እየከፈሉም ላሉ ውድ ነፍሳቸውን ለሸለሙ ይሁን።