
02/08/2025
ለሰባት ዓመታት ያህል "በከፍተኛ ማጭበርበር እና በአራጣ ብድር ግፍ ተፈጸመብኝ" ሲል ታዋቂ ባለሀብቶችን ከሶ ሲከራከር የነበረው የኮስሞ ትሬዲንግ የቀድሞ ባለቤት አቶ ሃይለየሱስ መንግስቱ፣ ታሪኩ ሙሉ በሙሉ ተገልብጦበት በከባድ የማጭበርበር ወንጀል ክስ እንደተመሰረተበት ተሰማ። ከሁሉም በላይ አስደንጋጭ የሆነው ደግሞ፣ በዚህ አዲስ ክስ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ተከሳሽ መሆኑ ነው።
🔵የሰባት ዓመቱ የክስ ድራማ እና የፍርድ ቤቱ ብይን
እንደሚታወሰው፣ አቶ ሃይለየሱስ መንግስቱ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት፣ በባለሀብቷ ወ/ሮ አዜብ ምህረትአብ፣ በይልማ ስጋ ቤት ባለቤት በአቶ ተመስገን ይልማ እና በሌሎች ላይ "በከባድ እምነት ማጉደልና አራጣ ብድር" ክስ ቀርቦ ጉዳያቸው ለሰባት ዓመታት ሲታይ ቆይቷል።
ነገር ግን፣ የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ባለፈው ሚያዝያ ወር በሰጠው ብይን፣ ተከሳሾቹ ከቀረበባቸው ክስ በሙሉ በነጻ እንዲሰናበቱ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው በምክንያትነት ከጠቀሳቸው ዋነኛ ነጥቦች አንዱ፣ የዐቃቤ ህግ ቁልፍ ምስክር የነበሩት አቶ ሃይለየሱስ እራሳቸው የሰጡት ምስክርነት ለተከሳሾቹ ያጋደለ መሆኑን መግለጹ ነበር። ይህም የህንጻው ሽያጭ ህጋዊና በስምምነት የተደረገ መሆኑን አረጋግጧል።
🔵 አዲሱ ክስ፡ ከከሳሽነት ወደ ተከሳሽነት
የቀድሞው ክስ በነጻ ስንብት ከተዘጋ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ አሁን እነ ወ/ሮ አዜብ እና አቶ ተመስገን ከሳሽ፣ አቶ ሃይለየሱስ መንግስቱ ደግሞ ተከሳሽ ሆነው አዲስ የፍትሐብሔር ክስ መመስረታቸው ታውቋል።
🔴 የአዲሱ ክስ ይዘት፦ ክሱ እንደሚለው፣ አቶ ሃይለየሱስ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም.፣ "እኔ ነኝ የኮስሞ ትሬዲንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር" በማለት ፖሊስን በማጭበርበር፣ በገርጂ አንበሳ ጋራዥ አቅራቢያ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በአደራ ተቀምጠው የነበሩ ሶስት የድርጅቱን ተሽከርካሪዎች ወስደው አድራሻቸውን አጥፍተዋል።
🔴 የፖሊስ ተጠያቂነት፦ ክሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፌደራል ፖሊስ በአደራ የተቀበለውን ንብረት፣ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሳያጣራ እና ያለአግባብ ለአቶ ሃይለየሱስ አሳልፎ በመስጠት የኃላፊነት ጉድለት ፈጽሟል ሲል ይከሳል።
🔵 የቀረበው የካሳ ጥያቄ
በዚህም መሰረት፣ ከሳሾቹ እነ አቶ ተመስገን ይልማ፣ ተከሳሽ አቶ ሃይለየሱስ መንግስቱ ለወሰዳቸው ሶስት መኪኖች የ15 ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፍላቸውና ከዚህ ቀደም ያልመለሰውን አንድ መኪናም እንዲመልስ ጠይቀዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም በፈጸመው የኃላፊነት ጉድለት ለደረሰው ኪሳራ ተጠያቂ እንዲሆን በክሱ ላይ ተጠቅሷል።
ይህ አዲስ ክስ፣ ለዓመታት የዘለቀውን የህግ ውዝግብ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ሲሆን፣ የፍትህ ስርዓቱ በቀጣይ የሚሰጠው ውሳኔ በጉጉት ይጠበቃል።
ጉዳዩን ተከታትለን ተጨማሪ መረጃዎችን ይዘን እንመጣለን።
Akiya Media Meta Newsroom