
22/07/2025
የካማሺ ዞን ከፍተኛ አመራሮች የአርሶ አደሩን የ2017/2018 የምርት ዘመን የስራ እንቅስቃሴ እየጎበኙ ነው።
አመራሮቹ በደምቤ ወረዳ ተገኝተው የ2017/18 የምርት ዘመን የአርሶ አደር እርሻ እንቅስቃሴና ትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢያቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ያለውን የልማት ስራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ ፃፊዮ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት ማህበረሰቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት በማስገባት የኢኮኖሚ አቅሙን ለማጎልበት በሁሉም ወረዳዎች ስትራቴጂካዊ ልማታችን ንቅናቄ መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ህዝቡ የልማት ንቅናቄውን ተቀብሎ ወደ ስራ መግባቱን ማሳያ የሚሆኑ በኩታ ገጠም፣ በጓሮ እርሻና በተረጅነት ቅነሳና በሌሎች ዘርፎች አበርታች ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በተለይ ትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢያቸውን በማሳደግ ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በአጠቃላይ የ2017/18 የምርት ዘመን እየተሰራ ያለው የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለና ማህበረሰቡ በሚገባ ፊቱን ወደ ልማት ያዞረበት አመት መሆኑን ተናግረዋል።
የደምቤ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ወንድሙ ቦቦ በበኩላቸው በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተሰራ ያለውን የእርሻ ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይ የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራም ለማስጀመር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ማካሄዳቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል።