
07/08/2025
250 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የጫነች ጀልባ ከ7 ቀናት
አስከፊ ጉዞ በኋላ የመን መግባቷ ተገለጸ
"7 ኢትዮጵያውያን በረሃብና በውሃ ጥም ሞተዋል"
| ከሶማሊያ ወደ የመን በመጓዝ ላይ ከነበሩ ስደተኞች መካከል ሰባት ኢትዮጵያውያን በረሃብና በውሃ ጥም መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) አስታወቀ።
ድርጅቱ፤ 82 ህጻናትን ጨምሮ 250 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የጫነችው ጀልባ፣ ማክሰኞ ዕለት ደቡብ የመን በሚገኘው አርቃህ አካባቢ ደርሳለች ብሏል። ይሁን እንጂ “ሰባት ስደተኞች በመንገድ ላይ በረሃብና በጥም ሞተዋል” ሲል አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርጅቱ ትናንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ በየመን የሚገኙ ቡድኖቹ “ከቦሳሶ ሶማሊያ በመነሳት ከሰባት ቀናት አስከፊ ጉዞ ለተረፉ ሰዎች የህይወት አድን እርዳታ” ማድረጋቸውን ገልጿል ሲል አናዶሉ ዘግቧል።
ባለፈው እሁድ 154 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በየመን የባህር ዳርቻ ሰጥማ የ68 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ 74 የሚሆኑት ደግሞ ያሉበት አለመታወቁን የተመድ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።