
18/09/2025
(ይስማዕከ ወርቁ)
(፩) የግዕዝን ቋንቋ ከሰኩላሪዝም (Secularism) አንጻር ስናዬው...
የግዕዝ ቋንቋ የሦስተኛ ክፍል የተማሪዎች መጽሐፍ ደርሶኝ እያገላበጥኩ ሁሉንም አየሁት። የሶስተኛ ክፍል የተማሪዎች መጽሐፍ 83 ገጽ አለው። ሲያጠናቅቅ ከግዕዝ ቋንቋ ወደ አማርኛ ቋንቋ የሚፈታ የሙዳዬ ቃላት ይዟል።
መጽሐፉን ሳዬው በትክክል የተዘጋጀ መሆኑን አይቻለሁ። የንግግሩ ቃላት ሁሉ እምነትን እንዳይነካ ሆኖ በጥንቃቄ የተዘጋጀ መሆኑን አረጋግጫለሁ። የግዕዝ ቋንቋን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አስጠግታው እንደኖረች እሙን ነው። ይህን ሁሉም ያምናል። ሙስሊሙም ክርስቲያኑም። ግን ወደ ልጆቹ ሲመጣ አስጠግታ ያቆየችው ሃይማኖት አለችና የእነርሱን እምነት እንዳይሰብክ ልጆቻቸውን መከላከሉ ከእናትና ከአባት የሚጠበቅ ነው። ግን እነርሱ ሳይሆኑ የሚከራከሩት መጽሐፉን ያላዩት የፖለቲካ ጥገኞች የሆኑ ሰዎች መሆናቸውን መጽሐፉን እኔም ካየሁት በኋላ አረጋግጫለሁ። እንዲያውም ከተዋህዶ ሃይማኖት ጋር የግዕዝ ቋንቋ ተጠግቶ ስለኖረ አስጠግታው የኖረችውን ሃይማኖት ጥቅሶች እንዳያመጣ ስግቼ ነበር። እንደዛ ያለ ነገር ግን መጽሐፉን በማነብበት ወቅት አላገኘሁም። የግዕዝ ቋንቋ እና ሃይማኖት የተለያዩ እንደሆኑ ይህን መጽሐፍ ያዘጋጁት ሰዎች፣ ብልህ እንደሆኑ መጽሐፉን ሳነብ አረጋግጫለሁ። የመጽሐፉ "ኮፒ ራይት" ይዞኝ እንጂ ሙሉውን ለእናንተ እለጥፈው ነበር። የአዘጋጁት ሰዎች እና የተረከበው አካል መፍቀድ አለበት።
በአማርኛም የትኛውንም እምነት መስበክ ይቻላል። የእስልምናንም ሆነ የትኛውንም የክርስቲያን እምነት በማንኛውም ቋንቋ መስበክ ይቻላል። የግዕዝን ትምህርት በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ለማስገባት ያሰቡ ሰዎች ሴኪውላር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። በፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ሰኩውላሪዝምን (Secularism) ስናዬው፣ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው። እኔ ግን እንደ ሀሳብ የምሰጠው፣ ኢትዮጵያ ከፖለቲካ የፀዳ ትልቅ የቋንቋ ተቋም ያስፈልጋታል። በዛ ተቋም ተገምግሞ አልፎ ቢሄድ ኖሮ እስከ አሁን የግዕዝ ቋንቋ ባላነታረከን ነበር። ማንም መንገደኛ አያደናግረንም ነበር። ከቋንቋዎች ሁሉ ደግሞ የመጀመሪያውና ኢትዮጵያን የምናስጠራበት ቋንቋ አንዱና ዋነኛው ግዕዝ ነው። የኢትዮጵያ ቀርቶ የአፍሪካ ሁሉ ኩራት ነው።
ግዕዝ ቋንቋውን ግን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አስጠግታው ስለኖረች፣ ከዛ አንዳንድ ጥቅሶች እንዳይገቡ መጠንቀቅ ያሻል ብዬ ነበር ግን መጽሐፉን ሳነበው ምንም የሚያጨቃጭቅ ነገር አላዬሁበትም። በጥራዝ ነጠቅ ያወሩ ሰዎች ነበር የሚያደናግሩን። በተለይም ከዚህ በፊት የተለጠፉ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ያላቸውን ሰዎች መጽሐፍ ከጎግል ላይ እያወጡ በትምህርት ስርዐቱ ውስጥ የገባ መስሎን እኔም ብዙ ሰዎችን በስልክ መከራቸውን ሳበላ ነበር። ግን በፍፁም እንደዛ እንዳልሆነ መጽሐፉን ሳነብ አረጋገጥኩ። ወደ ፊት በስርአተ ትምህርቱ ውስጥ የግዕዝ ትምህርት እየሰፋ ሲሄድ፣ መጽሐፍ የሚያሰናዱ ሰዎች እንደዚህ መጽሐፍ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የማንኛውንም እምነት እንዳይነካ፣ የትኛውንም ሃይማኖት እንዳይጎሽም አድርገው የማስተላለፍ ግዴታ አለባቸው። ይህ ግዴታ ነው።
(፪) የግዕዝ ቋንቋ አስተማሪዎች እነማን ይሁኑ?
የግዕዝን ቋንቋ የሚያስተምሩት ዲያቆናትና ቄሶች ናቸው ይባላል። ሃይማኖቱ አስጠግቶት ስለኖረ፣ እምነትን እንዳነካ አድርገው የተማሩት እንዲያስተምሩ መሆን አለበት። ያውም ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ቢሆን ይመረጣል። የግዕዝ ቋንቋ ሰኩላር (Secular) እየሆነ ሲመጣ ግን ሙስሊሞቹ ሰኩላር (Secular) ሆነው ማስተማር አለባቸው። አንድን ቋንቋ እየተጸየፍክ ግን እንኳን ለማስተማር ለመማርም አትበቃም። አንዳንድ የወሎ ሙስሊሞች ግዕዝ ያውቃሉ። እኔ ዛምራ የተባለው ልቦለዴን በምጽፍበት ወቅት ያገኘኋቸው አንድ ሙስሊም ሰው በግዕዝ ቋንቋ አውርተውኛል። እንዴውም የመጀመሪያውን ምዕራፍ የሰጠሁት አንድ ሙስሊም ልጅ ወደ ቅኔ ቤት ሲገባ የሚያሳዬውን ጠባይ በመንተራስ የተፃፈ ነው።
(፫) የግዕዝ ቋንቋ የጠንቋዮች እና የደብተራዎች እውቀት ነው ለሚሉ...
ጠንቋይ ማለት አደናጋሪ ማለት ነው። አምታቺ ነው። የማታውቀውን ቃል ያነበልብልሃል። የማታውቀውን ቃል ከግዕዝ ቃል እያወጣ መተት ደገምኩልህ ሊልህ ይችላል። እንዲያውም ከድግምት ቃላት ውስጥ አረብኛም በብዛት አለበት። ትናንት አንዱ የለጠፈውን የመተት ቃል አይቼ በሳቅ ፈረስኩ። የለጠፈውም ሰው እርሱ ሙስሊም ነኝ ይላል። ግን ቃላቱን አይቼ ስመረምረው ባብዛኛው የአረብኛ ቃላት አሉበት። ጫጫጫጫ ጃጃጃጃጃ ከሚለው ውስጥ አንዳንድ በተን በተን ያሉ የግዕዝ ቃላት አሉበት። ጳጳጳጳ ፓፓፓፓፓፓ ከሚለው ውስጥ ደግሞ ብዙ የአረብኛ ቃላት አሉበት። አስማተኞች መተተኞች እንዳይበሉን እንወቅ። ካላወቅክ ደግሞ ይበሉሃል። ይሸጡሃል። እንዳትሸጥ እወቅ። በሁሉም ቋንቋ መተት አለ። ድግምት አለ። በእንግሊዝኛም፣ በጀርመንኛም፣ በፈረንሳይኛም ድግምት አለ። እንዲያውም በአፍሪካ ቋንቋዎች አይብስም? በናይጀሪያማ አስማቱን የግላቸው ያደረጉት ይመስላል። ከዛ ውጪ ወደ አስማቱ ስንወርድ የተለያዩ የሚያምታቱ እና ብዙሃኑ የማያውቃቸውን ቃላት አሰማተኞች ይደርታሉ። ካላወቅህ ተበላህ ነው የምልህ። ይሸጡሃል። ይለውጡሃል። ገንዘብህን ንብረትህን ትበላለህ።
የግዕዝ ትምህርትን አትማሩ ማለት ግን የጠንቋዮች ስብከት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም አስማቱን ካወቅክባቸው በምን ሊደግሙት ይችላሉ? ይህ ይሰመርበት።
(፬)ከህክሞና አንፃር...
የግዕዝ መጻሕፍት የህክምና፣ የስነፈለግ፣ የኬሚስትሪ የእፅዋት ሳይንስን፣ የፊዚክስ ሁሉ አጭቀው ነው የያዙት። ይህን ፍለጋ ነው ነጮች የግዕዝን ቋንቋ ለማዎቅ የሚፈልጉት። ከዚህ አንጻር ሌላ ጊዜ መመለስ አለብኝ። አሁን ተዘርዝሮ አያልቅም።
እኔ በልጅነቴ ነው ሰባተኛ ክፍል ሆኜ ወደ ሀዋሳ የሄድኩት። ሀዋሳ ማለት የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ያለበት ከተማ ናት። ተማሪቹ አፋቸውን የፈቱበት የየራሳቸው ቋንቋ አላቸው። በተጨማሪም አማርኛ፣ እንግሊዝኛ እና ሲዳምኛ ትምህርት ቤት እንማራለን። ብዙዎቹ ተማሪዎች ባለ ብዙ ቋንቋ (Multilingual) ናቸው። እኔ ግን በልጅነቴ የግዕዝ ቋንቋ በመማሬ በእርሱ እንኳን ተጽናናሁ እንጂ ከአማርኛ በቀር በምንም አልግባባቸውም ነበር። አማርኞዬም ለእነርሱ ይከብዳቸው ይመስለኛል። ብቼኝነቴ ከመጽሐፍ ጋር አቆራኘኝ። ብቼኝነቴ እንድጽፍ ገፋፋኝ። ስለዚህ ሰናጠቃልለው የግዕዝ ቋንቋንተማሪዎች መማራቸው ሊበረታታ ነው የሚገባው። በሌላ ክፍለ ሀገር ያሉት ባለ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። ቢያንስ አንድ ቋንቋ በተጨማሪ ቢማሩ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ጥሩ ጊዜ ከመጣ ደግሞ በሁሉም ክፍለሀገር ቢሰጥ ጥሩ ነው። ግዕዝ ማለት የሁላችንሞ ቋንቋ ነው። ከመጽሀፉ ላይ አልፎ አልፎ ለምስክርነት እንዲረዳ ተጠቅሜአለሁ። ሰናይ ጊዜ።