24/07/2025
አትቀልዱ ምርጫው የ10ሺህ ሰዎች ነውና!
💥💥💥♦♦♦♦🔥🔥🔥🎯🎯🎯
በአሕመዲን ጀበል
🔺🔺🔺🔺🔺
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን ምክር ቤትን(መጅሊስን) ምርጫ ስናስብ በሀገር ደረጃ ያሉትን የፌደራል መጅሊስ የጥቂት የሥራ አስፈጻሚ አመራሮች ምርጫ እንደሆነ እያሰብን ከሆነ ለስህተት እንዳረጋለን። በዚህ ምርጫ የሚመረጡት ጥቂት ግለሰቦች ሳይሆኑ ከፌደራል እስከ የወረዳ እርከን መጅሊስ ላሉ ሥፍራዎች የሚሆኑ የ10ሺህ ሰዎች ምርጫ ነው። ይህም፦
ሀ) ለፌደራል መጅሊስ 15 አባለት ይመረጣሉ።
ለ) ለክልል መጅሊሶች ለእያንዳንዳቸው 13 የሥራ አስፈጻሚ አባላት ሲመረጡ በሀገሪቱ ላሉ ለ12 ክልሎችና 2ቱ የከተማ መስተዳደሮች በድምሩ 182(አንድ መቶ ሰማኒያ ሁለት ሰዎች) ሰዎች ይመረጣሉ።
ሐ) ለእያንዳንዱ ዞን 11 የሥራ አስፈጻሚዎች ሲመረጡ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ባሉ 119 ዞኖችና በዞን ደረጃ ላሉ ከተሞች በድምሩ 1,309(አንድ ሺህ ሦስት መቶ ዘጠኝ ተመራጮች) ሰዎች ይመረጣሉ።
መ) ለእያንዳንዱ ወረዳ 9 የሥራ አስፈጻሚ አባላት ሲመረጥ በሀገሪቱ ላሉ 914 ወረዳዎችና ልዩ ወረዳዎች በድምሩ 8,226 (ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ስድስት) ተመራጮች ይመረጣሉ።
ሠ) በመላ ሀገሪቱ ከፌደራል እስከ ወረዳ በሁሉም እርከኖች በድምሩ 9, 732(ዘጠኝ ሺህ ሰባት መቶ ሰላሳ ሁለት) የመጅሊስ የሥራ አስፈጻሚዎች በዚህ ምርጫ ይመረጣሉ ማለት ነው።
ረ) ከወረዳ በታች የቀበሌ መዋቅር ያለባቸውን የሀገሪቱን አከባቢዎችን ምርጫን ከጨመርንበት የተራጮች ብዛት በእጅጉ ያድጋል። ምርጫው የሚደረገው በመስጂድ ደረጃ በመሆኑ በእያንዳንዱ ወረዳ(ወይም ቀበሌ) ዉስጥ ባሉ ምርጫ በሚካሄድባቸው መስጂዶች ላይ ለየወረዳው (ቀበሌው) የሥራ አስፈጻሚነት እጩነትና ለወረዳ መጅሊስ ምክር ቤት የሚመረጡትን ሁሉንም ተመራጮችን ስንጨምርበት የተመራጮች ብዛት በብዙ እጥፍ ይጨምራል። በመሆኑም ምርጫው የ10ሺዎች ምርጫ በመሆኑ እንደቀልድ ሊታይ አይገባም። በዚህ ረገድ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የሚከተሉትን ወሳኝ ነጥቦችን በአንክሮ ማየት የግድ ይላል።
1) ምርጫው የሚጀምረው ለየወረዳው የሚሆኑ ሰዎችን በመስጂድ ደረጃ በማስመረጥ ነው። ቀጥሎ በወረዳ ደረጃ ከተመረጡ ሰዎች ዉስጥ ተመራጮች እርስ በእርስ እየተመራረጡ እስከ ፌደራል መጅሊስ ይሄዳሉ። ይህ የሚሆን ከሆነ ደግሞ በየወረዳው የሚመረጡ ሰዎች ምናልባት ወደላይ ሄደው የክልል ወይም የፌደራል መጅሊስ አመራር ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው። ስለሆነም ለወረዳም ብለን የምንመርጣቸው ሰዎች ለወረዳ እርከንም ቢሆን ከፍተኛ ብቃት ያላቸውና ለፌደራል መጅሊስ የሥራ አስፈጻሚ ጭምር መሆን በሚችሉ ደረጃ ያሉ ሰዎችን ለይቶ በጥንቃቄ መምረጥ ይገባል ማለት ነው።
2) በመስጂድ ደረጃ በሚደረገው ምርጫ በሁሉም ሥፍራ እያንዳንዱ ሰው የአመራር ክህሎት የሌለው፥ ለሕዝበ ሙስሊሙና ዲኑ ታማኝነቱን የሚጠራጥርና የሕዝቡን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ሰው እንዳይመርጥ ብርቱ ምክክርና ጥረት ካደረገ ሁሉም ተመራጭ የሚመጣው በመስጂድ ብቻ በመሆኑ አስመራጮቹ ታማኞች እስከሆኑ ድረስ በመስጂድ ያልተመረጠ ሰው በሌላ መንገድ ወደ ምርጫው ስርዓት መግባት አይችልም። ስለሆነም ለመጅሊስ ተገቢውን ሰው የመምረጥ ጥረትና ጥንቃቄ ቁልፉ ስፍራ በመስጂድ ደረጃ የሚደረገው ምርጫ ነውና ተገቢውን ሰው ለመምረጥ ጥልቅ ምክክርና ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
3) በመላ ሀገሪቱ ለሁሉም የመጀሊስ እርክን የሚመረጡትን 10ሺህ ተመራጮች ማንነት፥ ብቃትና ደረጃ የማወቅ እድል የለህም። ያንተ እድል ባንተ ሰፈር መስጂድ የሚመረጡትን በአግባቡ መምረጥ ነው። ስለሆነም እያንዳንዳችን በየሰፈራችን መስጂድ ለወረዳችን መጅሊስ የሚመረጡትን አካላት በጥንቃቄ ከመረጥን በተዘዋዋሪና በጋራ 10ሺህ ሰዎችን እንደመረጥን ሊወሰድ ይችላል።
4) እስካሁን እንዳብራራነው ምርጫው የሚካሄደው ከታች ጀምሮ ወደላይ ተመራጮችን በየእርከኑ በመምረጥ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እገሌ የኔ ምርጫ ነው። እርሱን መርጬዋለሁ።» የሚለው የአየር ላይ ምርጫ አንዳች ዉጤት አያመጣም። ምርጫው የሚደረገው በየመስጂዱ በመሆኑ በአየር ላይ መረጥኩት ያልከው አካል በሰፈሩ ያሉ የመስጂድ ጀመዓዎች ካልመረጡት ወደ መጅሊስ አይመጣም። ስለሆነም ትኩረትህንና ትኩረትሽን ወደ ሰፈራችሁ መስጂድ በማድረግ እነማንን እንደምንመርጥ ምክከር በማድረግ በጋራ መዘጋጀት ነው። በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያም ሌሎችም በየሰፈራቸው ብቁና ተፈላጊ ሰዎችን እንዲመርጡ ማነሳሳት ይቻላል።እኔም በሚዲያዎች ስለመጅሊስ ምርጫ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እያደረግኩት ያለሁት ጥረት 10ሺህ ተመራጮቹን በየአከባቢው ተከፋፍሎ የሚመርጠው ሕዝበ ሙስሊሙ የመጅሊስን ተልዕኮን የሚያሳኩ ሰዎችን እንዲመርጥ ለማገዝ ነው።
5) አንድ ንጉስ ነበር። ንጉሠን ብዙ ሰዎች ይወዱታል። ንጉሡም ምን ያክል ሰዎች እንደሚወዱት ማወቅ ፈለገ። የሚወዱትን ሰዎችን ለመለየት ይረዳው ዘንድ በአደባባይ ላይ ትልቅ ባርሜል አስቀመጠ። እያንዳንዱ እርሱን የሚወዱት ሰዎች እየመጡ በባርሜሉ ቀዳዳ አንድ ኩባያ ወተት እንዲጨምሩ አዘዘ። ሰዎች እየመጡ በባርሜሉ ቀዳዳ መጨመር ጀመሩ። አንደኛው የንጉሡ ወዳጅ «ሁሉም ሰው ወተት ይጨምራል። እኔ ዉሃ ብጨምር ማን ያያኛል? በዚያ ላይ ሌሎቹ ወተት ስለሚጨምሩ የኔ ዉሃ መጨመር ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም» ብሎ አስቦ በኩባያ ዉሃ በማምጥት ጨመረ።
የመጨመሪያው ጊዜ አበቃና ባርሜሉ ተከፍቶ ሲታይ ሁሉም ዉሃ ሆኖ ተገኘ። ለካ እንደዚያ ሰውዬ የየራሱን ሚና ሳይወጣ «ሌሎች ወተት ይጨምራሉ። የኔ ዉሃ መጨመር ምንም ለውጥ አያመጣም» እያሉ ዉሃ ሲጨምሩ ነበር። ከዚህ የተነሳ ባርሜሉ ሙሉ ወተት ሳይሆን ዉሃ ሆኖ ተገኘ። ሕዝቡ ንጉሡን ቢወደውም በተግባር ግን ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ንጉሡን እንደማይወደው ተቆጠረ።
የኛም ነገር እንደዚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ሁላችንም የሕዝበ ሙስሊሙ ሁኔታና የመጅሊስ ነገር እንደሚመለከተን እናምናለን። እስካሁን በነበሩት የመጅሊስ አስተዳደሮች ላይ ያለን የግምገማ መጠኑ ይለያይ እንጂ ከእስካሁኖቹ የተሻለ መጅሊስ እንደሚያስፈልገን እናምናለን። እንፈልጋለንም። ወንድም ዶ/ር ኢብራሂም ሙሉ ሸዋ እንዳለው «መጅሊስን ብንተወው እንኳ እርሱ አይተወንም።» ስለሆነም ሳይረፍድ በዚህ ምርጫ ወደ መጅሊስ ብቁ፥ንቁና ታማኝ የሆኑ አመራሮችን በመምረጥ ሚናችን እንወጣ።በስልሳ ሚሊዮን ሙስሊሞች ጉዳይ አትዘናጉ።የየበኩላችሁን ሚና መወጣት ሲገባችሁ ምርጫውን እንደቀልድ አትመልከቱት። ምርጫው የ10ሺህ ሰዎች ነውና!