
08/11/2025
መንጃ ፈቃድ የታገደበት አሽከርካሪ “የተሐድሶ ሥልጠና” ሳይወስድ ወደሥራ እንዳይመለስ የሚከለክል መመሪያ ተግባራዊ እየተደረገ ነው
- አሽከርካሪዎች የተሐድሶ ሥልጠና ከወሰዱ በኃላ የሚወስዱትን ፈተና የማለፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል
ተደጋጋሚ ጥፋት አጥፍተው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዳቸው የታገደባቸው አሽከርካሪዎች፤ “ጥፋታቸውን ሊያርም” በሚያስችል መልኩ “እውቀትና ክህሎትን” መሰረት ያደረገ የተሐድሶ ሥልጠና ሳይወስዱ ወደ ሥራቸው እንዳይመለሱ የሚከለክል መመሪያ ተግባራዊ እየተደረግ መሆኑን ኢትዮ ቲዩብ ተረድቷል።
“የአጥፊ አሽከርካሪዎች የተሐድሶ ሥልጠና አሰጣጥ” የተሰኘ መጠሪያ ያለው መመሪያ የወጣበት ዓላማ አሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ ከሚፈጽሟቸው ስሕተተቶች እንዲታረሙ ለማስቻል መሆኑ ተመላክቷል። የአሽከርካሪዎችን እውቀት እና ክህሎት በማሳደግ የሚደርሰውን የሞት፣ የአካል ጉዳትና ከፍተኛ የንብረት ውድመትን መቀነስ፤ መመሪያው የወጣበት ሌላኛው ዓላማ ነው።
በተደጋጋሚ ጥፋት ምክንያት መንጃ ፈቃዳቸው በታገደባቸው አሽከርካሪዎች ላይ ተፈጻሚ እየሆነ ነው የተባለው የተሐድሶ ስልጠና፤ አደጋን ተከላክሎ ማሽከርከር፤ የፍጥነት መንገድ አጠቃቀም፣ ሙያዊ ሥነ-ምግባር የተሰኙ ይዘቶች እንዳሉት ኢትዮ ቲዩብ ከሰነዱ ላይ ተመልክቷል። የመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤዎች እና መከላከያ መንገዶች፣የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እርዳታ ላይ ሥልጠናው የሚያተኩርባቸው ተጨማሪ ይዘቶች ናቸው።
የተሐድሶ ሥልጠናው ለአንድ ሳምንት በቀን 2 ሰዓታት የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህን አጭር ሥልጠና አሽከርካሪዎች በክፍል ውስጥ በመገኘት የመከታተል ግዴታ ተጥሎባቸዋል። የተሐድሶ ሥልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የሚሰጠውን ፈተና የማለፍ ግዴታ እንዳለባቸው “የአጥፊ አሽከርካሪዎች የተሐድሶ ሥልጠና አሰጣጥ” በተሰኘው መመሪያ ላይ ሰፍሯል።
በፈጸማቸው የማሽከርከር ስሕተት የመንጃ ፈቃዱ የታገደበት ማንኛውም አሽከርካሪ፤ ይህን የተሐድሶ “ስልጠና ሳይወስድ” እና “ሰርተፍኬቱን ሳይዝ” ማሽከርከር እንደማይችልም ተደንግጓል። የተሽከርካሪ ባለቤቶችም፤ መንጃ ፈቃዱ ታግዶበት የተሐድሶ ሥልጠና ያልወሰደ አሽከሪካሪ እንዲያሽከረክር መፍቀድ እንደሌለባቸው በመመሪያው ላይ ተብራርቷል። ሆኖም ይህን መመሪያ ጥሶ ሲያሽከርክር የተገኘ ግለሰብ “ከማንኛዉም የማሽከርከር አገልግሎት” ለ 3 ወራት በድጋሚ እንደሚታገድ ተገልጿል።