05/28/2025
ውድ ወዳጆቼ
በግሌ መፍትሔ ለማግኘት ብዙ አማራጮችን ስሞክር ቆይቻለሁ። ልክ የዛሬ 15 ቀን ፣ ሐሙስ ዕለት ሕመሜን አደባባይ አውጥቼ ድጋፍ ከጠየኩ በኋላ ያገኘሁት በብሔር፣ በኃይማኖት እና በአካባቢ ያልተገደበ ፍቅር ገና ሳልታከም ሕመሜን ያስታገሰ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የተለያዩ የድጋፍ ጥያቄዎች በበዙበት እና የኑሮ ውድነቱን መቋቋም በከበደበት በዚህ ወቅት ሰዎች እያሳዩኝ ያለው ፍቅር ለመሸከም የሚከብድ ነው። በ15 ቀናት ውስጥ ከሚያስፈልገኝ 50 በመቶ ድጋፍ አግኝቻለሁ።
“አንተን ሳናሳክም አንተኛም” የሚሉ ጓደኞች፣ የሥራ ባልደረቦች እና ቤተሰቦች ስለሰጠኝ እግዚያብሔርን አመሰግነዋለሁ። ታክሜ፣ በሕይወት ቆይቼ ሁሉንም ቆሜ ለማመስገን እንዲረዳኝ እፀልያለሁ። እናንተም ፀልዩልኝ። ቀዶ ሕክምናው ተደርጎ ዕጢው ከወጣ በሕይወት የመቆየት ዕድሌ ከፍተኛ መሆኑን ሐኪሞቹ ነግረውኛል። ቀሪው 50 በመቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞልቶ መታከም እንደምችል እንደሚረባረቡልኝ ሁሉም ቃል ገብተውልኛል። ብዙዎች በየኃይማኖታቸው እንደሚፀልዩልኝ የእምነት ቃላቸውን ሰጥተውኛል። ያረፍኩበት ቦታ ድረስ እምነትና ጸበል ያመጡልኝም አሉ። አሁን ላይ የሚያስፈልገው የሕክምና ገንዘብ ተሟልቶ፣ በወገኖቼ ጸሎት ታግዤ ፈውስ ላገኝ እንደምችል ተስፋ አለኝ!
ያጋጠመኝን የጤና ችግር ለወዳጆቼ፣ ዘመዶቼ፣ የሥራ ባልደረቦቼ እና ጎረቤቶቼ ሳልናገር የሸሸኩት በግሌ መፍትሔ ለማግኘት በማሰብ ነበር። በተለይ ዕጢው በቀዶ ሕክምና መውጣት እንዳለበት ከተነገረኝ ካለፈው ዓመት በኋላ ያልሞከርኩት ነገር አልነበረም።
በተፈጥሮዬ ግራኝ ስኾን ፣ ዕጢው የሚገኝበት ቦታ ደግሞ የግራኞችን ሰውነት እንቅስቃሴ በሚቆጣጠረው በቀኝ አንጎሌ ክፍል ነው። ይኽ ሁኔታም የቀዶ ሕክምና አማራጩን አስጊና አስፈሪ አድርጎብኛል። ምከንያቱም ቀዶ ሕክምናው የንግግር ክህሎቴን ሊያሳጣኝ እንደሚችል ስለተነገረኝ ነበር።
በሀገር ውስጥ በቅዱስ ያሬድ፣ በተክለኃይማኖት፣ በላንሴት በጥቁር አንበሳና በጳውሎስ ሆስፒታሎች ሕክምና ተከታትያለሁ። ተደጋጋሚ የMRI እና ሌሎች ምርመራዎችን አካሂጃለሁ። ጣሊያን ውስጥ በዚህ ሕክምና የተሳካ ውጤት አምጥተዋል የተባሉ ሐኪም ለሚገኙበት ሆስፒታል ተገቢው ክፍያ በመፈፀም የሕክምና ማስረጃዎቼን ልኬ ከባለሞያዎቹ ጋራ ሰፊ የቪዲዮ ውይይቶችን አድርጌያለሁ፡፡ በቅርቡም የMRI ውጤቴን አስቀድሜ ልኬ ወደአሚን አጠቃላይ ሆስፒታል በመጡ ቱርካዊ ኒውሮሰርጀን ምርመራ ተደርጎልኛል። በቪዲዮ ኮንፈረንስ የህንዳዊ ኒውሮሰርጀን ምክርም አግኝቻለሁ።
ብዙዎቹ እኔ ላለሁበት ሁኔታ ራሴን ሳልስት የሚካሄድ ቀዶ ሕክምና የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ነግረውኛል። ሕክምናው በሀገር ውስጥ ያለ ቢሆንም በቀዶ ህክምናው ወቅት የspeech capability ክትትሉ ከማሽን ውጪ የሚካሄድ በመኾኑ ፍርሃቴ ከፍተኛ ኾነ። በዚህም የተለያዩ ሀገራትን አማራጮች ሳስስ ነበር። የጣልያኑ ሆስፒታል የተሻለ ሆኖ ያገኘሁት በቀዶ ህክምናው ወቅት በንግግር ችሎታዬ ላይም ሆነ በእጅና እግር እንቅስቃሴዬ ላይ እክል ቢፈጠር ወዲያውኑ የሚያሳውቅ ቴክኖሎጂ ያላቸው መሆኑና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ በመሆኑ ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ የአንጎል ዕጢው ባስከተለብኝ ከፍተኛ ተጽእኖ ምክንያት የሥራ እንቅስቃሴዬ የተገደበ በመሆኑ፣ በአግባቡ አልሠራሁም። ጥሪቴም ተመናመነ፣ ያሰብኳቸውና የሞከርኳቸው ሌሎች አማራጮችም አልሳካ አሉ። በዚህም ምክኒያት ነበር የዛሬ ዓመት አይሆንም ብዬ የገፋሁትን ሌሎችን የማስቸገር መፍትሔ አሁን የተቀበልኩት። በዚህ ሁለት ሳምንት ያገኘሁትን ፍቅር፣ የተላከልኝን መልዕክት እና የተደወሉ ስልኮችን ብዛት ሳይ ግን ለድጋፉ ብቻ ሳይሆን የሰውን ፍቅር እንዳይበት እንኳን የድጋፍ ጥሪ ጥያቄን አቀረብኩ እንድል አደረገኝ።
አሁን ከእግዚያብሔር ጋራ ተስፋ ይታየኛል። ተስፋዬ እውን እንደሚሆን ደግሞ እምነት አለኝ። በሁለት ሳምንት ውስጥ በተስፋ እንድጠነክር ላደረጋችሁኝ ሁሉ እግዚያብሔር በሚያስፈልጋችሁ ይድረስላችሁ። Addis Chekol
➤GoFundme (ጎ ፈንድ ሚ)፡- https://shorturl.at/YHOSA
አዲስ ቸኮል አለነ
➤የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፡- 1000061095989
➤ዳሽን ባንክ:- 5009778150021
➤አቢሲኒያ:- 225994951
➤አዋሽ:- 013200542570900
Let’s Help Save the Life of Journalist Addis Chekol ! Addis Cheko… Selamawit Telahun needs your support for Save Addis Chekol: Urgent Brain Surgery Needed