06/23/2026
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=122114168529280268&id=61588408056047&mibextid=WC7FNe
ክቡራትና ክቡራን የሶሮ 01 ምርጫ ክልል ነዋሪዎች፣ የተከበራችሁ ደጋፊዎቼ እና መላው የዲሞክራሲ ወዳጆች፤ በመጀመሪያ፣ ካለፈው 7ኛ ሀገራዊ የምርጫ ሂደት ጀምሮ ለእውነት፣ ለፍትሕ እና ለሕዝባችን ድምፅ መከበር ስትሉ ላሳያችሁት ጽናት፣ ትዕግሥትና ተስፋ ያልቆረጠ አንድነት ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
እኛ ወደዚህ የፖለቲካ ውድድር ስንገባ የሕዝባችንን እውነተኛ ፍላጎትና ድምፅ በቅንነት ለማገልገል እንጂ፣ የሕግ ጥሰቶችን እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄዶችን ለማስተናገድ አይደለም። ካለፈው የምርጫ ሂደት ጋር ተያይዞ በሶሮ 01 የምርጫ ክልል የተፈጸሙት የሕግ ጥሰቶች የሕዝባችንን ነፃ ምርጫና ሉዓላዊነት የሚጋፉ ነበሩ። እኛም ይህንን ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ድርጊት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ ለመታገል ቃል ገብተን ነበር።
የተከበራችሁ ወገኖቼ፤ ዛሬ ያደረግነው ሕጋዊ ትግል እና ያቀረብነው አቤቱታ ፍሬ አፍርቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረቡትን ክሶችና ማስረጃዎች በዝርዝር መርምሮ፣ በሶሮ 01 የምርጫ ክልል የተካሄደው ምርጫ የሕግ ጥሰት የተፈጸመበት መሆኑን በማረጋገጥ ምርጫው ተሰርዞ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ በ14/10/2018ዓ.ም የመጨረሻ ውሳኔውን አስተላልፏል።
ይህ ውሳኔ የዶክተር ሀብታሙ ታምራት ብቻ ሳይሆን፣ የእናንተ የሶሮ 01 መራጮች የጽናት ውጤት ነው! ይህ ውሳኔ በሀገራችን የሕግ የበላይነትና የሕዝብ ድምፅ በቀልድ እንደማይታለፍ ያሳየ ትልቅ የዲሞክራሲ ድል ነው። ፍትሕ ዘግይታም ቢሆን መምጣቷን ያረጋገጠ ክስተት ነው።
የተከበራችሁ የሶሮ 01 ነዋሪዎች፤
አሁን ዋናው እና ወሳኙ ምዕራፍ ተጀምሯል። የምርጫ ቦርድ ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑ የሰጠን ትልቅ ዕድል ነው። ይህ ዕድል እውነተኛ ድምፃችንን ያለምንም ፍርሃትና ተፅዕኖ በካርዳችን የምናስመሰክርበት ወሳኝ ወቅት ነው።
ስለሆነም፦ በቀጣይ በሚወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሁላችንም በነቂስ ወጥተን የምርጫ ካርዳችንን በመያዝ ለድጋሚ ምርጫው እንድንዘጋጅ፤
ይህ የድጋሚ ምርጫ ሂደት ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የሕግ የበላይነት የተከበረበት እንዲሆን ሁላችንም እንደ ሁልጊዜው በንቃትና በጨዋነት እንድንጠብቅ፤ የጀመርነውን የለውጥና የልማት ጉዞ በድጋሚ ምርጫው ላይ በምናሳየው ጠንካራ ተሳትፎ እንድንደግም ጥሪዬን አቀርባለሁ።
እውነት እና የሕዝብ ፍላጎት ሁልጊዜም ያሸንፋሉ! ፍትሕ ለሶሮ 01 ሕዝብ በምልዓት ትረጋገጣለች።
ስለነበረን ጽናት ሁሉ እግዚአብሔር ያክብርልኝ!
ቀጣዩ ጊዜ የጋራ ድላችንን የምናበስርበት ይሆናል!
ዶ/ር ሀብታሙ ታምራት ደሪሎ
የግል እጩ ተወዳዳሪ
Abiy Ahmed Ali
National Election Board of Ethiopia NEBE የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
Prosperity Party - ብልፅግና