11/17/2025
የ 30% የነዳጅ ግብር ተግባራዊ ሊደረግ ነው!!
በነዳጅ ምርቶች ላይ የተጣለዉ አጠቃላይ ግብር በቀጣይ ወር ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለፀ
የኢትዮጵያ መንግሥት ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ ለማስወገድ ከሚወስዳቸው ሰፋፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አንዱ የሆነው አዲስ የግብር አወቃቀር ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ተግባራዊ ሊሆን ነው።
ይህ አዲስ እርምጃ በነዳጅ ምርቶች ላይ 15% ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እና 15% ኤክሳይዝ ቀረጥን ያካተተ አጠቃላይ 30% ታክስ መጣል ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከአንድ ወር በኋላ ታክሱን መሰብሰብ ይጀምራል።
በአዲሱ መመሪያ መሠረት፣ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቱ የተሰበሰበውን ግብር በሙሉ ለገቢዎች ሚኒስቴር ማስገባት ግዴታው ሲሆን፣ መንግሥት በዚህም እስከ ታኅሣሥ 2018 ዓ.ም. ድረስ ለቤንዚንና ናፍጣ መሸጫ ዋጋዎች ሁሉንም ህጋዊ የግብር መጠን ጨምሮ ሙሉ ወጪን የመሸፈን ግብ ላይ ለመድረስ አቅዷል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ከአዲሱ በጀት ዓመት ጀምሮ በነዳጅ ምርቶች ላይ አጠቃላይ 30 በመቶ ግብር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሊያደርግ ማቀዱን ካፒታል ጋዜጣ ከሁለት ወራት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
ሚኒስትሩ መስከረም 2018 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ባቀረቡት አጠቃላይ የዜጎች በጀት ዉስጥ፣ በተያዘው በጀት ዓመት ተግባራዊ የሚደረጉ የግብር አይነቶችን በዝርዝር አስቀምጠው ነበር።
(ካፒታል)