07/01/2025
የጋዜጠኛ ንጉሴ ወልደማርያም ስርዓተ ቀብር
ጋዜጠኛ ንጉሴ ወልደማርያም ከእናቱ ከወይዘሮ ፈለቀች እና ከአባቱ መምሬ ወልደማርያም ህዳር 2 ቀን 1948 ዓ.ም. (November 12, 1955) በአዲስ አበባ ባእታ ማርያም አካባቢ ተወለደ። ንጉሴ ወልደማርያም የአንደኛ እና የሁለተኛ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በማድረግ አጠናቋል። ከዝያም በያሬድ ሙዚቃ ቤት ትምህርቱን ተከታትሎ አጠናቋል። በማስታወቂያ ሚንስቴር በዜና ክፍል እና በተለያዩ ቦታዎችም ሰርቷል። ጋዜጠኛ ንጉሴ ወልደማርያም በእድገት በህብረት ዘመቻ በነበረበት ግዜ መሄዴ ነው ዘመቻን እና በወሎ ረሀብ በድርቁ ግዜ ወሎ ተርቦ እንደዝያ ሲያልቅ የሚለውን ዜማ በግዜው የተጫወተ፣ የብዙ ባለሙያ ባለቤት ነበር። ከዝያም ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ከመጣም በኋላ፣ ከጓደኞቹ ጋር የአንድ ኢትዮጵያ ሬድዬ በመመስረት እና በኋላም በግሉ የሀገር ፍቅር ሬድዮን መስርቶ ሬዲዮኑን እስካቆመበት ድረስ ለሚወዱትም፣ለሚጠሉትም በየሳምንቱ በጉጉት እየተጠበቁ ለህዝቡ ያገለገለ ታዋቂ ጋዜጠኛ ነበር።
በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ሀገር ፍቅር ሬዲዮን በመክፈት ለብዙ ጊዜ በጋዜጠኛነት ሲያገለግል የነበረው ጋዜጠኛ ንጉሤ ወልደማርያም ባደረበት ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ ሰኔ 20፣ 2017 ዓ.ም. (June 27, 2025) በተወለደ በ69 ዓመቱ ከዚህ ዓለም አርፏል። ጋዜጠኛ ንጉሴ ባለትዳር እና የ2 ልጆች አባት ነበረ።
የስርዓተ ፀሎት ፍትሃት ማክሰኞ፣ Tuesday, July 1, 2025, ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት (8:00 A.M.) ጀምሮ በርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን (1350 Buchanan St, NW, Washington DC) ከተደረገለት በኋላ ሥርዓተ ቀብሩ በ13472 Poplar Hill Rd, Waldorf, MD 20601 በሚገኘው በHeritage Memorial Cemetery, ይፈፀማል።
በጋዜጠኛ ንጉሤ ወልደማርያም ሞት የተሰማን ሀዘን እጅግ በጣም ጥልቅ ነው።
እግዚአብሔር ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹና ለአፍቃሪዎቹ ጽናቱን ይስጥልን። ነፍሱን ይማርልን፣ በገነትም ያኑርልን!!!