10/07/2025
🚨 አስደንጋጭ ዜና!
ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ለመዝረፍ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ!
በጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ፣ በሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተከሰተው አስከፊ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ከተሰበሰበው የድጋፍ ገንዘብ ላይ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ለመዝረፍ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አስታወቀ።
* አደጋው በደረሰባቸው ወገኖች ህይወትና ችግር ለመበልጸግ ያሰቡት ተጠርጣሪዎች፣ ለተጎጂዎች የተሰበሰበውን 60,276,383 ብር ከጎፋ ዞን አደጋ ስጋት አካውንት ለመውሰድ ሞክረዋል።
* ገንዘቡን ለመዝረፍም ቀደም ሲል ቮይድ በተደረገ የቼክ ቁጥር (42221123) አስመስለው በማሳተም ሙከራ አድርገዋል።
* የወንጀል ሙከራው የተጋለጠው ከአዲስ አበባ ንግድ ባንክ ሸገር ቅርንጫፍ ለጎፋ ዞን አስተዳደር በተደረገ ፈጣን ጥቆማ ምክንያት ነው።
* በጥቆማው መሠረትም ከአዲስ አበባና ከክልል ፖሊስ ጋር በመተባበር፣ ገንዘቡ ሳይወጣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል።
የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን፣ ሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የለገሰውን ድጋፍ 'ወደ ኪሴ ገብቶ ካልበለጸግኩ' በሚል አስተሳሰብ የተጠመዱ አካላት ያሰቡት "አስነዋሪና ስብዕና የጎደለው ተግባር" አለመሳካቱን ገልጿል።
⚠️ ማስጠንቀቂያ ለመገናኛ ብዙኃንና ለሕብረተሰቡ:
* ሐሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ሕዝብን የሚያወዛግብ መረጃ ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ ተጠይቋል።
* ሕብረተሰቡም ትክክለኛና ተጨባጭ መረጃን ከመንግሥት ምንጮች ብቻ እንዲከታተል አሳስቧል።
የምርመራው ሂደት ሲጣራ ተጨማሪ መረጃ እንደሚሰጥም ተገልጿል።