12/29/2025
በስእሏ ፊት ስቆም. . .
ሰማይና ምድርን የፈጠረ የሰማያዊ ንጉሥ የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤቴ ሆይ! መተዳደፍ በበዛበት ዓለም ስኖር ንጽሕናዋን እንዳላሳጣት ነፍሴን በአንቺ ዘንድ አኖራታለሁ፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም በላከው ጊዜ ማረፊያ ያደረገው አንቺን ነውና ካንቺ የከበረ ቦታ ለነፍሴ ስለማላገኝላት በአንቺ ዘንድ አኖራታለሁ።
የአብ ሙሽራ እመ አምላክ ሆይ! ወደ አንቺ እጆቼን ዘርግቼ ጸሎቴን አደርሳለሁ፤
ዓይኖቼን ቀና አድርጌ ልመናዬን አቀርባለሁ፤ “የልብሱን ጫፍ የዳሰስሁ እንደሆነ እድናለሁ”
ብላ የተመኘችው ሴት ልብሱን ዳሳ ተፈወሰች፤ እኔ ግን አማኑኤል የሥጋን ልብስነት ካንቺ የለበሰብሽ፣ ከለበሰው ልብስ ይልቅ የከበርሽ እና ክርስቶስ ባሕርይሽን የተካፈለሽ መሆኑን አውቄ እጆቼን ለጸሎት ወደ አንቺ እዘረጋለሁ።
የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆንሽ መመኪያዬ ክብሬ ድንግል ሆይ! ስምሽን በጉባኤ ዐውጃለሁ፤ በምስጋና ጊዜም እጠራሻለሁ፤ የአንቺ ምሳሌ የሆነውን ማዕጠንት ይዞ አሮን በወገኖቹ መካከል በተመላለሰ ጊዜ የሆነውን አውቃለሁ፤ ሕዝቡን ከደዌአቸው የፈወሳቸው ያንቺ ምሳሌ ከሆነው የወርቅ ማዕጠንት የሚወጣው የዕጣኑ መዓዛ ነው፤ እኔ ግን ከአሮን ማዕጠንት ይልቅ የከበርሺ አንቺን ይዤ በሕዝቡ መካከል እገባለሁ።
የጻድቃን እናት ሆይ! የኃጢአት ማዕበል እንዳይገፋኝ ወደ አንቺ እጠጋለሁ፤ ከሰማይ የቊጣ ዝናም በዘነመ ጊዜ ወደ መርከብ ገብቶ የዳነውን ኖኅን አስታውሳለሁ፤ ከመርከቧ ይልቅ አንቺ እንደምትበልጪም አውቃለሁ።
ስለዚህም የልጅሽን ምሕረት እስከማገኝ ድረስ በአንቺ ውስጥ ሰውነቴን ከሰይጣን እሰውራታለሁ። ድንግልናሽን መቅዘፊያ አድርጌ ከርኩስቴ እሻገርበታለሁ።
ንጽሕናሽን ልብስ አድርጌ ከኃጢአት ብርድ እድንበታለሁ።
የሔዋን የሚጎዳ ማሰሪያዋ በአንቺ የተቆረጠላት ንጽሕት ቅድስት ሆይ! ቤተ ክርስቲያን አንቺን ታመሰግንሻለች፤ በልጅሽ ጸዳለ ብርሃን ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ወጥታለችና።
በአንቺ ደስ ትሰኛለች፤ ዓለሙን ሁሉ የሚያጣፍጠውን የሕይወት ግንድ ይዘሽ ተገኝተሻልና።
ቤተ ክርስቲያን በአንቺ ትደነቃለች፤ አንበሳን የታቀፈች ጊደር፣ እሳትን የታቀፈች የሰው ዘር፣ ከሰማይ የምትበልጥ ምድራዊት፣ መለኮትን በሥጋ የወሰነች፣ ጥበትን ከስፋት ጋር አስተባብራ የያዘች ካንቺ በቀር ሌላ ሴት የለችምና።
ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው የሆንሽ እመብርሃን ሆይ! ሰይጣን ኃጢአቴን እያሳሰበ ተስፋ ሊያስቆርጠኝ ሲሞክር የማሸንፈው ስምሽን ለጠራ መታሰቢያሽን ላደረገ ምሕረትን እንደሚያደርግ ልጅሽ የገባልሽን ኪዳንሽን አስቤ ነው።
ኃጢአቴ በዝቶ ከልጅሽ መንግሥት እንዳያሳድደኝ በቃል ኪዳንሽ ተማጽኛለሁ።
ልጅሽ ከጌርጌሴኖን ተመልሶ ከመርከብ ሲወርድ ያገኘውን ሽባ ሰው የፈወሰው የተሸከሙትን ሰዎች እምነት አይቶ ነው ማቴ. 9፥2።
እኔንም ያንቺን እምነት አይቶ ይማረኝ! ንጽሕናሽን አይቶ ከርኩሰቴ ያንጻኝ!
ዓለሙን ሁሉ የሚያጣፍጠውን ጨው ይዘሽ የተገኘሸ አዲሷ የኤልሳዕ ማሰሮ አንቺ እያለሽልኝ ነፍሴ በኃጢአት ምሬት ተሞልታ መኖሯ ለምንድነው? ንጽሕት ጽዋዕ የወርቅ መቅጃ የተባልሽ ድንግል ሆይ! በአንቺ የተቀዳውን የሕይወት ውኃ ጠጥታ ነፍሴ ትዘምራለች።
የኤልሳዕ በረከት ለኢያሪኮ ነው ያንቺ በረከት ደግሞ በእኔ ላይ ይሁን።
የኤልያስ መሶብ የተባልሽ አማናዊት የመና ሙዳይ እመ አምላክ ሆይ! ዓለሙ ሁሉ በልቶት የዳነበት የሕይወት እንጀራ የተገኘው ካንቺ ነው።
የምንበላውን ያፈራሽልን የምንጠጣውን ያስገኘሽልን አንቺን የማያመሰግን ቢኖር የልጅሽ የመለኮቱ ብርሃን ያላገኘው ነው።
መኖሪያው ጨለማ ነው።
መንገዱ ዳጥና ጨለማ የሞላበት ነው።
ሰውነቱ የመለኮትን እስትንፋስ ያላገኘች ሸክላ ናት።
የፀሐየ ጽድቅ መውጫ ምሥራቅ፣ የብርሃን ደጃፍ ጸዳለ መብረቅ፣ ሐረገ ወይን እንተ በምድር፣ አዕጹቂሃ በሰማይ ዘይነብር፣ የአብ ጥበቡ ያረፈብሽ፣ የወልድ አካሉ ያደረብሽ፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብር የተገለጠብሽ ቢጸ ሱራፌል፣ መንበረ ልዑል፣ እመ አዶናይ እመቤቴ! እንደ ጴጥሮስ ጥላሽን ጣይብኝ! እንደ ጳውሎስ ሰበንሽን አስነኪኝ! ያኔ ድኜ ወደ ልጅሽ መንግሥት ከሚገቡት ጋር እጨመራለሁ።
ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነ!
እግዝእትነ ማርያም ትምክሕተ ዘመድነ!
ዕፀ መስቀሉ ምርጉዝነ!
አሜን!