12/24/2025
"በኢታንግ ልዩ ወረዳ ዛሬ ንጋት 11 ሰዓት በጀመረው ተኩስ ከ30 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። የሞቱት ህፃናትም በርካታ ናቸው። የአጎቴ ልጆች የት እንዳሉ አይታቅም። ቤታቸው ተቃጥሏል" - ነዋሪዎችና ቤተሰብ
➡️ "ሥራ እየሰራን ነው፤ ስንጨርስ እንነግራችኋለን"- የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ
በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ተርፋም ቀበሌ ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ/ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በተከፈተ ተኩስ "ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን" ነዋሪዎችና የዓይን እማኝ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።
በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ባለፉት ሳምንታት በጸጥታ ችግር የንጹሐን ህይወት መቀጠፉን፣ ተጎጅዎች የህክምና አገልግሎት እንዳላገኙ ነዋሪዎች፣ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ በኢታንግ ልዩ ወረዳ "በርካቶች ተገድለዋል" ተብሏል።
የአካባቢው ነዋሪዎችና አንድ የዓይን እማኝ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ "በኢታንግ ልዩ ወረዳ ዛሬ ንጋት 11 ሰዓት በጀመረው ተኩስ ከ30 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። የሞቱት ህፃናትም በርካታ ናቸው" ብለዋል።
በወረዳው ተርፋም ቀበሌ የተኩል ልውውጥ ሲደረግ መዋሉን በመግለጽ፣ "ሁኔታው ከበድ እያለብን ነው" የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ በርካታ ሰዎች በጥይት ተመትነው እንደቆሰሉ፣ ንጋት ላይ ሰዎች በተኙበት ቤት የማቃጠል ድርጊት እንደተፈጸመ አስረድተዋል።
ከቦታው ሆነው የተኩሱን ሁኔታ በቅርብ ርቀት ሲከታተሉ የነበሩ አንድ የዓይን እማኝ የክልሉ ነዋሪ፣ "የአንድ፣ የሁለት ዓመት ህፃናት" ጨምር ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል። "የኔም የአጎቴ ልጆች የት እንዳሉ አይታቅም። ቤታቸው ተቃጥሏል። ልጆች፣ አረጋውያን፣ ወጣቶችም ተገድለዋል" ሲሉ ገልጸው፣ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ በአንክሮ አሳስበዋል።
"ቤቶች ተቃጥለዋል፤ በቃጠሎና በጥይት ህይወታቸው ያረፈው በርካታ ናቸው። በቦንብ የተመቱ ነዋሪዎችም አሉ" የሚሉት የዓይን እማኝ፣ "ከደቡብ ሱዳን የገቡ ሰዎች በተኩሱ ሲሳተፉ ተስተውለዋል" ሲሉ አክለዋል።
የጸጥታ ችግሩ በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው ቲክቫህ ኢትዮጵያ የጠየቃቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ፣ " የጸጥታ አካላት ጋር ደውሉ ስብሰባ ላይ ነኝ" ያሉ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃላፊው ስልክ እንዳላነሱ ስንነግራቸውም፣ "ሥራ እየሰራን ነው፤ ስንጨርስ እንነግራችኋለን " የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ለጊዜው ስልክ ያላነሱ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስት በበኩሉ፣ የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ "የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው የክልሉ አካባቢዎች" "ከጸጥታ አካላት ውጭ የሰውና የተሽከርካሪ" የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን አስታውቋል።
በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች "በአኘዋክና ኑዌር ብሔረሰቦች መካከል" በተለያዩ ጊዚያቶች "ግጭት" ሲነሳ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፣ ከአመት በፊት ቆሞ እንደነበር አሁን ደግሞ ማገርሸቱን፣ ችግሩን ለማስቆምም እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሽኔ አስቲን ከሳምንት በፊት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መግለጻቸው ይታወሳል።
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በበኩሉ፣ ችግሩን ለማስቆም እየተሰራ መሆኑን፣ 18 ተጠርጣሪዎች እንደተያዙ ከሳምንት በፊት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ደግሞ ዛሬ በኢታንግ ልዩ ወረዳ የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገ ገልጸው፣ "በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ የአኙዋክና ኑዌር ብሔረሰቦች" እንዳሉ፣ በዛሬ ተኩስም "ከደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂዎች" እንተሳተፉ እየተናገሩ ናቸው።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ