21/07/2025
የምርመራ ዘገባ (ጥቆማ)
ማለዳ ሚዲያ
******
በፕረዝደንቱ ወንድም እና ሌሎች ባለ ስልጣናት መሪነት የተነጠቀው የቀይ መስቀል ማህበር ቤትና ሰፊ መሬት
**********
ነገሩ እንዲህ ነው …
ለማለዳ ሚዲያ አቶ ቸሩ ሌዳሞ የተባሉ ግለሰብ (የሲዳማ ክልል ፕረዝደንት አቶ ደስታ ሌዳሞ ወንድም) በሃዋሳ ከተማ በተለምዶ 05 ሰፈር 7 ላውንጅ ገባ ብሎ የሚገኝ አምስት ሺ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚገኝ ቤት በተጭበረበረ መንገድ በመውሰድ ለአቶ ይድነቃቸው አስፋው ( የእንጆሪ ላውንጅ ባለቤት) ከሃያ ሶስት ሚልየን ብር በላይ በሆነ ገንዘን መሸጣቸውን መረጃ ይደርሳል።
መረጃው የደረሰው ሚዲያችንም ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረት የጥቆማውን ትክክለኛነት የሚያመላክቱ የሰነድና የሰው ማስረጃ አግኝቷል።
*****
ከታች በታይፕራይተር ከተፃፈዉ ደብዳቤ መረዳት እንደሚቻለው ባለይዞታዋ ወይዘሮ ኒሻን ቤቱንና ግቢውን አስይዘው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደሩትን 27,314.32 ብር ዕዳ መመለስ ባለመቻላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐዋሳ ቅርንጫፍ ሀራጅ አውጥቶ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሲዳማ ዞን ቅ/ጽ/ቤት 27,314.32 ብር በመክፈል ቤቱንና ቦታውን የግሉ አድርጓል።
ግዢዉን ተከትሎ ቀይ መስቀል ማህበር ቦታው ርክክብ እንዲደረግለት ለባንኩ እና ለሐዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ደብዳቤ ፅፎ ጠይቋል። [በታይፕራይተር የተፃፈ ደብዳቤ በመመልከት መረዳት ይቻላል]
ይሁን እንጂ ቅ/ጽ/ቤቱ የስም ዝውውርና ሳይት ፕላን እንዲሠራለት ተደጋጋሚ ጥያቄ ለሐዋሳ ከተማ ቢያቀርብም በየወቅቱ የቅ/ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጆች እየተቀያየሩ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሐዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ጉዳዩን እያጎተቱ ይዞታው ከወ/ሮ ኒሻን ወደ ሲዳማ ዞን ቀይ መስቀል ማህበር ስም ሳይዛወርና የሳይት ፕላንም ሳይሠራ ለዘመናት መቆየቱን ያገኘናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
በ2015 ዓ.ም የመሬት ምዝገባ በካደስትራል ሲጀመር ቦታው ምንም እንኳ ለረጅም ዓመታት በቀይ መስቀል ማህበር እጅ የቆየ ቢሆንም ( መጀመሪያ በክራይ መልክ ከዚያ በግዢ ) ሕጋዊ ፕላንና ሰነድ እንደሌለው በሐዋሳ ከተማ ሐይቅ ዳር ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ይደርስበታል።
ውስብስቡ የመሬት ንጥቂያ ሥራ እዚህ ጋ ይጀምራል።
የሐይቅ ዳር ክፍለ ከተማ ከዋና ከተማ ማዘጋጀ ቤት ጋር በመተባበር የሲዳማ ቀይ መስቀል ማህበር ቅ/ጽ/ቤት ይዞታዬ ነው ሰለሚለው ቦታ ሕጋዊ ፕላን እንዲያቀርብ በደብዳቤ ይጠየቃል። የቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም በእጁ ያሉትን መረጃዎችና ማስረጃዎች ይዞ ይቀርባል። ሆኖም በሐይቅ ዳር ክፍለ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ይዞታው የቀይ መስቀል ማህበር ቅ/ጽ/ቤቱ አለመሆኑ ይነገረዋል። በዚህ ምክንያት ብዙ ጭቅጭቅ ተነስቶ በቀድሞ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕ ፀጋዬ ቱኬ አማካኝነት ንብረቱ በቀይ መስቀል ማህብር እጅ እንዲቆይ ይደረጋል።
የአሁን የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ ወደ ኃላፊነት ከመጣ ቦኋላ ቦታው በወ/ሮ ፀዳል ውድነህ ስም የሳይት ፕላን ፎርጅድ ካርታም ተዘጋጅቶለት፣ የ15 ዓመት ውዝፍ ግብር በማትታወቅ ነገር ግን ሕጋዊ ውክልና ሰጥታለች በተባለችው በወ/ሮ ፀዳል ውድነህ ስም እንዲከፈል ይደረጋል።
በወቅቱ የሲዳማ ክልል ቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ ጽ/ቤትና የቦርድ አባላት ፦
1. አቶ ተሰማ ዲማ (ሰብሳቢ)፣
2. ዶ.ር አራርሶ ገረመው (አቃቤ ንዋይ)፣
3. አቶ ዮሐንስ ላታሞ (ፀሐፊ)፣
4. አቶ አክሊሉ አዱላ (አባል)፣
5. ፓስተር ጌቱ አያለው (አባል) ጉዳዩን ከርዕሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ በተዋረድ ለሚለመለከተው አካል ሁሉ ቢያሳውቁም ሰሚ ሳያገኙ ቀሩ።
ከዚያ በኋላ የመሬት ንጥቂያ ሴራ ዋና አቀነባባሪ ናቸው የተባሉት አቶ ቸሩ ሌዳሞ (የአቶ ደስታ ሌዳሞ ወንድም) በወቅቱ በአቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ ተባባሪነት ልዩ ኃይል ይዘው ወደ ማህበሩ ፅህፈት ቤት በማምራት በግቢው የሚገኘውን የቡና ተክልና ሙዝ አውድመው፣ የቅ/ጽ/ቤቱ ሠራተኞች ላይ ዝተው፣ የቦርድ አባላቱን አስፈራርተው ግቢውን እንዲለቁ ካደረጉ በኋላ በወ/ሮ ፀዳለ ስም በተዘጋጀው ውክልና ስም ከ 23 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ገንዘብ ለአቶ ይድነቃቸው አስፋው (የእንጆሪ ላውንጅ ባለቤት) እንደተሸጠ በማለዳ ምርመራ ተረጋግጧል።
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ቢወስደውም የፍትህ ሥርዓቱ በርዕሰ መስተዳድሩ ፍላጎት የተተበተበ በመሆኑ ከሲዳማ ክልል ፍትህ ፈፅሞ ልያገኝ ባለመቻሉ አቤቱታውን ወደ ቀይ መስቀል ማህበር የበላይ ጠባቂ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ ይገኛል።
መንግሥት የህዝብ ተቋማት የበላይ ጠባቂ እንደ መሆኑ ለእነኚህ ተቋማት መወገን ሲገባው በግለሰቦች ስም የማጭበርበሪያ ሰነድ በማዘጋጀት የተቋም መሬት ነጥቆ እስከመሸጥ ድረስ የደረሰ መሆኑን ከታች የተያያዙ ማስረጃዎችን ብቻ በማየት መረዳት ይቻላል።
በዚህ ዙሪያ የበለጠ መረጃ የሚሹ የሚዲያም ሆኑ ሌሎች ተቋማት ካሉ ማለዳ ሚዲያ የበለጠ መረጃ በመስጠት የሚተባበር መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።
ማለዳ ሚዲያ