12/27/2025
#እንሰት
--------------
የእንስት ምርቶችን(ቡላ:ቆጮ:ቃጫ) የማዘጋጀት ሂደት በዘመናዊ ሳይንስና ተክኖሎጂ የታገዘ ባለመሆኑ ሥራዉ አስቸጋሪና ከባድ ነዉ። እንሰትን ከመፋቅ ጀምሮ፣ ጨምቆ እንዲሁም ቆሮጦ ቂጣ እስከመጋገር ድረስ ያሉ ሂደቶች በባህላዊ መንገድ የሚከወን በመሆኑ እናቶች ላይ የሚያደርሰዉ ድካም እና የስራ ጫና ከባድ በመሆኑ ሁሌም ያሳስባል።
በተወሰነ መልኩ የእንሰት ተዋጽኦ ማምረቻ መሳሪያዎችን ከባህላዊዉ በማሻሻል አዘምኖ ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ የተሞከረ ቢሆንም መሳሪያዎቹ እምብዛም ችግር ፈቺ ባለመሆናቸዉ ዛሬም ነባሩን ቁሶች ለመጠቀም ተገዷል። ይህ ደግሞ ሥራዉን ጉልበት ጨራሽ አድካሚ ከማድረግ አልፎ በቆጮ ምርት ጥራት፣ ዋጋ እና በቆይታ ጊዜ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እሙን ነዉ።
ከአድካሚዉ እንሰትን ፍቆ ከማጠናቀቅ ወዲያ ያለዉ ጭንቀት ደግሞ የተፋቀዉን በባክቴሪያ አማካይነት ለማብላላት (fermentation) የሚወስደዉ ረጅም ጊዜ ነዉ። በባህላዊ መንገድ ለማብላላት የሚጠቀሙት እርሾ( 'ጋማ') ፍቅፋቂዉን አብላልቶ ዝግጁ ለማድረግ ጊዜ ከመፍጀቱ ባሻገር በጥቃቅን ተህዋሲያን (microbes) መካከል ለአልሚ ምግቦች(nutrients) ና ለኦክሲጅን ሽሚያ መኖሩ፤ በዋናነት ደግሞ መጥፎ የቆጮ ጠረን መፍጠር፣ በተመጋቢዉ ዝቅተኛ ቅቡልነት እንዲኖረዉ ማድረግና አስፈላጊ የምግብ ንጥረ ነገሮች እንዲቀንሱ ያደርጋል።
እንግዲህ ወንድማችን Melesse Tadesse የምርምር ስራዉን እንዲሰራ ምክንያት የሆነዉ እላይ እንደጠቀስኩት በማላላት ሂደት የሚፈጀዉን ጊዜ በማሳጠር፣ የምርት ጥራቱ የተጠበቀ የተሻለ የምግብ ንጥረነገር ያለዉ ቆጮ እንዴት ማምረት እንደሚቻል የሚያትት ነዉ።
ለዚህም የተፋቀዉን እንሰት ለማብላላት የሚጠቅሙ ተሕዋሲያንን ለይቶ በማዉጣት በማብላላት ላይ የሚኖራቸዉን ሚና በመገምገም ዉጤቱን ከባህላዊ የማብላላት ሂደት ጋር በንጽጽሮሽ ለማስቀመጥ ሞክሯል።
በመጨረሻም የምርምር ግኝቱ(ዉጤቱ) እንደሚያሳየን በሳይንሳዊ መንገድ የተደረገዉ የማብላላት ሂደት፦
1ኛ በጣም አጭርና በ15 ቀን ተብላልቶ ለምግብነት ሊዉል የሚችል ቆጮ ማግኘት መቻሉን፣
2 የተሻለ ጠረን ያለዉ፡ በተመጋቢዉ የተሻለ ቅቡልነት ያለዉ ቆጮ ማግኘት መቻሉ፣
3 የምግብ ንጥረ ነገር ይዘታቸዉ ከባህላዊዉ መንገድ ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ፕሮቲን ይዘት ያለዉ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ዝርዝር የምርምር ሂደቱን፣ ዉጤትና ሪኮሜንዴሽኑን መመልከት ለሚፈልግ የሥራዉ ባለቤት( Meles Tadesse )ማግኘት ይችላል። ተመራማሪ የሆናችሁ ተጨማሪ ተዛማች ሥራዎችን ለመስራት የምትፈልጉ Contact ብታደርጉ።
Badege. w Feb 26/2022