07/24/2025
ብዝኃነትን ከእምቅ የተፈጥሮ ሀብት ጋር ያጣመረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል
*************
ኅዳር 14 ቀን 2014 ዓ.ም የተመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በድንቅ ተፈጥሮ የታደለ እና በርካታ ብሔሮች የሚገኙበት የትንሿ ኢትዮጵያ አምሳል ነው።
ከፋ፣ ሸካ፣ ኮንታ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ እና ምዕራብ ኦሞ በክልሉ የሚገኙ ዞኖች ሲሆኑ፣ በእነዚህ ዞኖች የሚገኙ ብሔሮች የኢትዮጵያ ጌጦች ናቸው።
በእምቅ ተፈጥሮ ሀብቱ የሚታወቀው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የታላላቅ የኃይል ማመንጫ ግድቦች እና የቱሪስት መዳረሻ ነው።
በዳውሮ እና በኮንታ መካከል የሚገኘው እና በርካታ አጥቢ የዱር እንስሳትን በውስጡ የያዘው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ያለው በዚሁ ክልል ሲሆን፣ ፓርኩ በውስጡ ከያዛቸው እንስሳት መካከልም የአፍሪካ የዝሆን፣ ጎሽ፣ ከርከሮ፣ ሳላ እና እንደ አጋዘን ያሉ የዱር እንስሳት እንዲሁም ብርቅዬ የወፍ ዝርያዎች ይገኛሉ።
በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ሀብት በጥቅም ላይ ለማዋል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ታላቁ የሃላላ ግንብን ተተንተርሶ የተገነባው የሃላላ ኬላ እና የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ የሚገኙት በዚሁ አስደናቂ ክልል ነው።
የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በክልሉ የሚገኝ ሌላው የኢትዮጵያ በረከት ሲሆን፣ 75 አጥቢ እንስሳትን እና 325 የአዕዋፍ ዓይነቶችን እንደያዘ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ፣ ውድንቢዎች፣ የመጋላ ቆርኪ፣ ሳላዎች፣ የሜዳ ፍየሎች እና ሌሎም አጥቢዎች የሚገኙበት የክልሉ በረከት ነው።
ጊቤ አና ኦሞ ወንዞችን ወደ ቱርካና ሀይቅ የሚሸኘው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከግልገል ጊቤ በሚያመነጨው ኃይል ኢትዮጵያን እያበራ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀጣይ የኢትዮጵያ የልማት አቅም የሆኑት የኦሞ እና ጎጀብ ወንዞችን በጉያው ይዟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቅርብ ክትትል የሚያደርጉበት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ ግዙፍ የሆነው ኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ መገኛ የሆነው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ብርሃን መፈንጠቂያ ነው።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን "ኢቢሲ ወደ ይዘት" በሚለው እንቅስቃሴው ተጨማሪ የይዘት ምንጭ የሆነውን የታርጫ ስቱዲዮ በዚህ አስደናቂ ክልል ሥራ አስጀምሯል።
ስቱዲዮው የክልሉን ብዝኃ እና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለመላው ኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ የሚሠራውን ሥራ በእጅጉ የሚያግዝ ይሆናል።
#ታርጫ #ኢትዮጵያ #ዳውሮ