07/26/2025
🔻ህዝበኝነት ወይንስ መርህ?!
~~~~~~~~~
"populist" ወይንም "ህዝበኛ" የሆኑ ፖለቲከኞች በሁሉም አለም አሉ፡፡ ከብዙ መገለጫዎቻቸው በጥቂቱና በአጭሩ ወገንተኝነታቸው ለመርህና ለተመሳሳይ ሚዛን ሳይሆን ሕዝብን የሚያስቀድሙና ሁሉንም ለህዝብ የሚያደርጉ መስለው መታየትን ይወዳሉ፡፡ ከህዝብ ግብረመልስ የማያሰጣቸው ከሆነ ግዴታቸዉም ቢሆን አያደርጉትም>>ይልቅ የህዝብን ሥስ ልብ በመፈለግ ትኩረት የሚያሰጣቸው ሆኖ ከተገኘ ከመርህ ጋር ቢጋጭም ከማድረግ አይመለሱም፡፡ ምንም መርህን የሚቃረን ቢሆን እንኳ ህዝቡ ትኩረት ይሰጣቸዋል ወይንም ክብር ይሰጣቸዋል በሚሉት ጉዳዮች ላይ መገኘትን ያዘወትራሉ፡፡ ይህ ማለት አሁን አሁን ተዉት እንጂ ጠ/ሚ አብይ አህመድ populist ወይንም ህዝበኛ በነበሩበት የመጀመርያዎቹ አመታት ስልጣናቸው ወቅት የእያንዳንዱን ዜጋ ለቅሶ ካልደረስኩ፣ የህዝቡን ሰርግ ተገኝቴ ካልባረኩ ወይንም ካልበላሁ, አልያም በየመንገዱ ላይ ከሰዉ ጋር ፎቶ ካልተነሳሁ ወዘተ እያሉ በህዝቡ መሃል ለመታየት ሲጥሩ እንደነበረው ማለት ነው፡፡ ያንን ያደርጉ የነበረው ህዝብን የመውደድ መርህ ኖሯቸው ሳይሆን መስለው በመታየት ህዝበኝነታቸዉን ማጉላት ስለነበረባቸው ነው፡፡ ያ አካሄድ መርሃዊ ስላልነበረ አሁን ሲያደርጉት አይስተዋሉም፡፡
ለቁልቢ ገብሬል ክብረ በአል ወደ ድሬዳዋ ያቀኑትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሊቃነ ፓፓሳትን የድሬዳዋው ከንቲባ ራሳቸው ተቀብለው፣ በራሳቸው መኪና ጭነው ከመዉሰዳቸዉም በላይ ቪድዮዎ ቆረጥ እያደረጉ እያዩ ቆመው እየመረቁና እያበረታቱ ቴምርና ዉሃ ሲያከፋፍሉ የተቀረጹትን ቪድዮዎ በማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተዘዋወረ ብዙ ጭብጨባና ሙገሳ አስገኝቶላቸዋል፡፡
ብዙዎች ታድያ "ይህ ምን ችግር አለው? እንዴትስ ህዝበኛ ያሰኛቸዋል?" እያላችሁ ይሆናል፡፡ በመሰረቱ ይህ ብዙ አይገርምም! በተለይ ሙስሊም በዝ በሆኑ የሃገራችን ክፍሎች እንዲህ አይነቱን ነገር ማየት የተለመደ ፣ ወይንም የሚጠበቅ ፣አልያም ግድ የሆነ የሚመስልባቸው ብዙ አጋጣሚዎችን አይተናል፡፡ በርግጥም ለመከባበርና ለመቀራረብ ሁሌም ምሳሌ የምናደርገው ክርስትያን በዝ የሆነዉን የሰሜኑን የሃገራችንን ክፍል ሳይሆን ሙስሊም በዝ የሆኑትን የደቡብ, የደቡብ ምእራብና፣ የምስራቅ የሃገራችንን ክፍሎች ነው፡፡ ይህ ድርጊት የሚገርመው የሙስሊሙ መሪዎችን የትግራይ አልያም የአማራ ክልል መሪዎች ተቀብለው በዚህ መልክ ቢያስተናግዱ ነበር እንጂ ያኛው የሚጠበቅ ነው፡፡
ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ የድሬዳዋ ከንቲባም ሆነ የሙስሊም በዝ ክልሎች ፕሬዝዳንቶችና ባለስልጣኖቻቸው ተመሳሳይ ድርጊቶችን የሚፈጽሙት በመከባበር መርህ ስለሚያምኑ ሳይሆን የራሳቸዉን ቆዳ ለማዋደድ ህዝበኛ ወይንም populist ሆነው ነው፡፡ ለዚህም ሌላው ማሳያ ያኔ ህዝበኛ ሳሉ ቀጣዩ ንጉሳችን ሲባሉ የነበሩት የሶማሌ ክልሉ ሙስጠፌን ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰዎች እዉነት በመከባበር መርህ የሚያምኑ ቢሆኑ ኖሮ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍሎችም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ከተሞችና ገጠሮች በተቃራኒው የሚጣሱ የሃይማኖት ጭቆናዎች እንቅልፍ የሚነሷቸዉና የሚረብሻቸው ስለሚሆኑ እንዲሁም ከመርሃቸው ጋር ስለሚጋጭ በፍጹም ሊቀበሉት የማይችሉት ጉዳይ በመሆኑ ያላቸዉን ስልጣንና ግንኙነት ተጠቅመው የክልል መሪዎችንና አስተዳደሮችን በመወትወት እንዲስተካከል ሲሰሩ እናያቸው ነበር፡፡
ከዚህም አልፎ በተለይ በአክሱምና በላሊበላ ሙስሊሙ የሃይማኖትም ሆነ የዜግነት መብቱን በመቀማት ዋነኛ ሚና ያላትን ቤተክህነት ፓፓሳት እግር ስመው ከተቀበሉ በኋላ ዉሃና ቴምር ሰጥተው ወይንም ቤተክርስትያን አድሰዉና አሸብርቀው ከማስረከብና ከመሸኘት ባሻገር ሙስሊሙን "መስጂድ አትሰራም ፣ የቀብር ቦታ አይገባህም ወዘተ" እያሉ ለዘመናት የመጨቆንና የማንገላታት መሰረቱ ቤተክህነታዊ ስለሆነ ይህንን ስህተት በማረቅ የተሻለ መከባበር እንዲኖር የአቋም ለዉጥ እንዲያመጡ በማግባባት ሚናቸዉን ይወጡ ነበር፡፡ የህዝበኝነት ሳይሆን የመርህ ቢሆን ኖሮ ታዳጊ ሴት ተማሪዎች በሂጃባቸው ሰበብ ትምህርት ሲከለከሉ ድምጻቸዉን በሰማን ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ለማድረግ ፕሮቶኮላቸው የማይፈቅደዉና ሌላኛዉን ለማድረግ የሚችሉት ጉዳዩ የመርህ ሳይሆን የህዝበኝነት ስለሆነ ነው፡፡
ጉዳዩ ሃይማኖትን የማክበር, የመቻቻል ምሳሌ የመሆን ቢሆን ኖሮ አክሱምን፣ ላሊበላንና እንዲሁም ሌሎች የጭቆናና የአፓርታይድ መናኸርያ የሆኑ ከተሞችን በመጎብኘት ሙስሊሙ ያለበትን ሁኔታ በተጨባጭ ባዩ ነበር፡፡ እናም ይህ የሙስሊም በዝ ከተሞች ባለስልጣናት የሚያሳዩት የተለየ አካሄድ ጥሩ ቢሆንም መሰረቱ ግን በእኔ ግምት ትኩረት ፈላጊነት populism (ህዝበኝነት) አልያም የበታችነት ስሜት ነው ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የህዝበኝነት አባዜ ከሌሎች ይልቅ በሙስሊሙ ባለስልጣናት፣ ምሁራንና ኤሊቶች ላይ በስፋት ይታያል ለማለት ነው:: ይሄው ነው!
*** የእርሶስ ምልከታ ምን ያለ ነው? ይጻፉና እስኪ እንየው!
ለተጨማሪ መረጃ ቴሌግራማችንን ተቀላቀሉ
https://t.me/RNZeroFive